Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥት ያልታረመ አካሄድ መከላከያ ሠራዊትን አላስፈላጊ መስዋዕትነት እያስከፈለው መሆኑን ኢዜማ ገለጸ

የመንግሥት ያልታረመ አካሄድ መከላከያ ሠራዊትን አላስፈላጊ መስዋዕትነት እያስከፈለው መሆኑን ኢዜማ ገለጸ

ቀን:

  • በዘውግ መታጠቅና የሽምቅ ውጊያ ማድረግ ትርፉ አገራዊ ኪሳራ ነው ብሏል

መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት እንዲቀር የወሰነው ውሳኔ በሁሉም ክልሎች በወጥነት አለመተግበሩና ይፋ ያደረገበት መንገድና አቀራረብ፣ የመከላከያ ሠራዊቱን ለአላስፈላጊ መስዋዕትነት እየዳረገው ነው ሲል፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ገለጸ፡፡

ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት እንዲቀር የወሰነውን ውሳኔ በሁሉም ክልሎች በወጥነት አለመተግበሩና ውሳኔውንም ይፋ ያደረገበት የተዝረከረከ የኮሙዩኒኬሽን አቀራረብ፣ መከላከያ ሠራዊቱ ለተጨማሪ ጥቃት እንዲጋለጥ በር ከፍቷል፡፡

‹‹በመንግሥት በኩል ያለው ያልታረመ አካሄድ መከላከያ ሠራዊትን ለአላስፈላጊ መስዋዕትነት እያደረገው እንደሆነው ሁሉ፣ በሌሎች ክልሎች ሲደረግ እንደነበረው ከጥቂት ወራት ወዲህ ደግሞ በአማራ ክልል የአገር መከላከያ ሠራዊትን በጠላትነት ፈርጆ ጦርነት የመግጠም አክሳሪ የፖለቲካ ጨዋታ ተንሰራፍቷል፤›› ሲል ኢዜማ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በአንድ በኩል በመንግሥት ኃላፊዎች እንዝላልነትና ደባ፣ በሌላ በኩል በዘውግ ማኅበረሰብ ስም በተደራጁ ታጣቂዎች፣ በሁለት በኩል ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ተረድቼያለሁ ሲል ኢዜማ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ኢዜማ አክሎም መንግሥት በውስጡ ባለው ያልጠራ የፖለቲካ መስመር፣ በገዥው ፓርቲ አመራሮችና አባላት መካከል በሚፈጠር ሽኩቻ፣ ጊዜያዊ የፖለቲካ ግብን ለማሳካት በማሰብ፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱን ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ለፖለቲካዊ ፍላጎት ማሳኪያ በመጠቀም፣ ሠራዊቱ ተቋማዊና ሙያዊ ነፃነቱን አክብሮ አገር እንዳይጠብቅ አፍራሽ ሚና የመጫወት አባዜ እየተስተዋለ ነው ብሏል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የፀጥታ ችግር በሚደርስባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ አለመድረሱ፣ ፈጥኖ ለመድረስ መንገድ ከጀመረ በኋላ ደግሞ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎች እንዲሰወሩ ወይም የደፈጣ ውጊያ እንዲያደርሱ መረጃ የመስጠት ተግባራት መኖራቸው፣ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ መከላከያ ሠራዊቱን አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዲከፍል የሚያደርጉ ድርጊት ለመኖራቸው ማሳያ ነው ሲል ኢዜማ አብራርቷል፡፡

መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱ የተቋቋመለትን ሕዝባዊ ዓላማ እንዲያሳካ እንቅፋት ከሚፈጥሩ ውሳኔዎች፣ የፖለቲካ ደባዎች፣ ሽኩቻዎችና ዝርክርክ አሠራሮች እንዲቆጠብ ኢዜማ አሳስቧል፡፡

መንግሥት ልዩነቶች በሰላም የሚፈቱበትን የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ ተግባራዊ እንዲያደርግ የጠየቀው ኢዜማ፣ ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን በደሎችና ሥጋቶች በሚገባ አዳምጦ ተገቢውን መልስ በአስቸኳይ በመስጠት የንፁኃን ዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲያደረጋግጥ ጠይቋል፡፡

ኤዜማ በሌላ በኩል በፋኖነት የተደራጁ የኢትዮጵያ ልጆች ቀኝ ገዥዎችን አንበርክከው ነፃ አገር ማስረከባቸውን፣ የዚህ መንፈስ ወራሾች የሆኑ ጀግኖችም በፋኖ ስም ተደራጅተው በተለይም የሕወሓትን የሽብር ወረራ በግንባር ቀደምትነት ማክሸፋቸውን፣ የአገር ጠበቃነታቸውንም በተግባር ማስመስከራቸውን፣ ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋርም ለክቡር ዓላማ በአንድ ጉድጓድ መቀበራቸውን አስታውሷል፡፡

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋራ ወርቃማ ገድል የፈጸሙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና በፋኖ ስም የተደራጁ ታጣቂዎች እርስ በርስ እየተታኮሱ መሆናቸውን ኢዜማ በመግለጫው ገልጿል፡፡

አክሎም ይህ አሳዛኝ ሁኔታ የተፈጠረው በመንግሥት እንዝህላልነት ብቻ እንዳልሆነ፣ የመከላከያ ሠራዊቱን የአንድ ዘውግና ፓርቲ ጠበቃ ብቻ አድርጎ በመሳል የሚደረጉ ቅስቀሳዎች፣ የፋኖ አደረጃጀትን ከመሠረታዊ ምንነቱ ነጥሎ የአንድ ዘውግ ማኅበረሰብ መብት አስጠባቂ ብቻ የማድረግ እንቅስቃሴና በፋኖ አደረጃጀት የመከላከያ ሠራዊቱ ለጥቃት እንዲጋለጥ እያደረገው እንደሆነ ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል ብሏል፡፡

በዘውግ ማኅበረሰብ መብት አስጠባቂነት ስም ተደራጅቶ መታጠቅና የሽምቅ ውጊያ ማድረግ ትርፉ አገራዊ ኪሳራ ከማወራረድ ያለፈ እንደማይሆን፣ ኢዜማ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

‹‹በአገራችን ታሪክ በተደጋጋሚ እንደታዘብነው በኤርትራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብ አካባቢዎች በዘውግ ማኅበረሰብ ስም የተደራጁ ታጣቂዎች ማኅበራዊ መቃቃር ከመፍጠር ሕዝብን ከማጎሳቆልና የዘር ፖለቲካ ጡዘትን ከማክረር የዘለለ ሚና አልነበራቸውም፤›› ያለው ኢዜማ፣ በዚሁ መንገድ ወደፊትም መፍትሔ ይመጣል ብሎ ማሰብ በተመሳሳይ መንገድ የተለየ ውጤት መጠበቅ ነው ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...