በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞች ባደራጇቸው ግለሰቦች አማካይነት፣ በጉራጌ ዞን ንፁኃን ዜጎች እየተገደሉ መሆናቸውን፣ የጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ በጉራጌ ዞን በምሥራቅ መስቃንና ማረቆ አካባቢ ዳግመኛ ባገረሸ ግጭት፣ በተከታታይ ቀናት የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው መግለጫ እንደሚያመለክተው ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በበቼ ቀበሌ ሁለት ተማሪዎችን ጨምሮ አራት ሰዎች፣ ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በእንሴኖ ኡስሜ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጋሮሬ ተብሎ በሚጠራ መንደር ሁለት ሰዎች፣ ሐምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. አንድ ሰው፣ ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም አንድ ሰው ተገድለዋል፡፡
በተጨማሪም ሐምሌ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በዲዳ ቀበሌ ወደ ገበያ ሲሄዱ በነበሩ ሰዎች ላይ በተከፈተ የተኩስ እሩምታ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን፣ በእነዚህ ጥቂት ቀናት ብቻ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18 መድረሱን ፓርቲው ገልጿል፡፡
የፓርቲውን መግለጫ በተመለከተ ሪፖርተር ከመንግሥት አካላት መረጃ ለመጠየቅ የዞኑን አስተዳዳሪ፣ የፀጥታ ኃላፊውንና የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊውን በተደጋጋሚ ቢደውልም ስልካቸው እየጠራ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡
የጎጎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጀሚል ሳኒ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ የሚያሳየው ለዘብተኛ አቋም ውስጡ ያልጠራ ነገር እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በዚሁ አካባቢ ተከስቶ በነበረ ተመሳሳይ ግጭት፣ መንግሥት ጉዳዩን ሲገመግም፣ በዚህ ችግር ተጠርጥረው ከሥልጣን የተነሱ ሰዎች እንደነበሩ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
‹‹ከሁለቱም አካባቢዎቸ ይህን ግጭት የሚደግፉ አካላት በመኖራቸው እንጂ ውጫዊ አካል እያስተባበረና እየመራ ነው የሚል እምነት የለንም፤›› የሚሉት አቶ ጀሚል፣ ‹‹በመንግሥት ሥልጣን ላይ በኃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች ሥልጣናቸውን ያለአግባብ እየተጠቀሙ ይመስለናል፤›› ብለዋል፡፡
ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ጥቃት ባይኖርም ውጥረቱ ስለመቀጠሉ የተናገሩት የፓርቲው የሥራ ኃላፊ፣ ‹‹የመንግሥት ልዩ ኃይል ተሰማርቷል፣ ነገር ግን ልዩ ኃይሉ የሚንቀሳቀሰው አስፋልቱን ይዞ በመሆኑና ወደ ውስጥ እየገባ ባለመሆኑ በእርሻ አካባቢ በተለይ ከፍ ከፍ ያለ የበቆሎ ማሳ ውስጥ እየተደበቁ ጥቃት የሚያደርሱ አካላት አሉ፤›› ብለዋል፡፡ አድፍጠው ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት በመኖራቸው ምክንያት ገጠሩ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ አሁንም ሥጋት ውስጥ እንደሆነና መንግሥትም ምንም ዓይነት ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥት አካላት ስለተፈጠረው ነገር ለሕዝቡም ለሚዲያውም መልስ አለመስጠታቸው ችግሩ ትኩረታቸውን የሳበው አለመሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከሁለቱም ወገኖች ጥቃት የሚያደርሱት ዩኒፎርም የሌላቸውና ማንነታቸውን ለማወቅ ከባድ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ በአካባቢው ትልቁ ገበያ በሚባለው ቀን ስምንት ሰዎች ገድለው ሲሄዱ የፀጥታ ተቋማቱ ምንም ዓይነት ዕርምጃ አልወሰዱም ብለዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ቢያንስ ተጠርጣሪዎችን መፈለግና በቁጥጥር ሥር ማዋል ነበረበት፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ነገር አልተሠራም፤›› ብለዋል፡፡