Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበትግራይና በአፋር ክልሎች የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነገረ

በትግራይና በአፋር ክልሎች የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነገረ

ቀን:

በዳንኤል ንጉሤ

በትግራይና በአፋር ክልሎች ከሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የአንበጣ መንጋ በቦቆሎና በማሽላ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተነገረ።

የአንበጣ መንጋ በክልሉ ስድስት ወረዳዎች ማለትም አብአላ፣ ኤርኮዴ፣ አዲሀረመሊ፣ አሳንጎላ፣ ሙርጋና ደሙም እስከ ሁለት መቶ ሔክታር የሚያህል መሬት ላይ የነበረ የበቆሎና የማሽላ ሰብል ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የአፋር ክልል ወሳኝ ኩነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ዓሊ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የክልሉ አስተዳደር የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ለፌዴራል መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ቢያቀርብም፣ እስካሁን ምንም ምላሽ እንዳልተሰጠው ገልጸዋል፡፡ አክለውም የአንበጣ መንጋ የሚከሰትባቸው የአፋርና የትግራይ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች በመሆኑና ከትግራይ ክልል ጋር አብሮ መሥራት ስላልተቻለ አደጋውን በኅብረት መከላከል አጋጣሚ አልተቻለም ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሐምሌ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ የአንበጣ መንጋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክልሉ ሥጋት እየፈጠረ በመሆኑ፣ ችግሩን ለመከላከልና ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት ጉዳዩን የሚከታተል በካቢኔ ሴክሪቴሪያት የሚመራ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን ምንጮች ገልጸዋል።

‹‹የአፋር አርሶ አደሮች የተለያዩ ጥያቄዎች አቅርበዋል፤›› ያሉት አቶ ሁሴን፣ ከጥያቄዎቻቸውም ውስጥ በዋነኝነት የፀረ ተባይ መድኃኒት ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ አያይዘውም አካባቢያቸው በተደጋጋሚ የአንበጣ ጥቃት ስለሚደርስበት የተለየ ትኩረት እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

‹‹የትግራይና የአፋር ክልሎች አርሶ አደሮች በዋናነት በበቆሎና በማሽላ ምርቶች  የሚተዳደሩ ሲሆን፣ እነዚህ ሰብሎች ለምግብ ዋስትናና ለክልሎቹ አርሶ አደሮች መተዳደሪያ አስፈላጊ ናቸው፤›› ያሉት አቶ ሁሴን፣ ይህ አደጋ በመከሰቱ በአርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አስከትሏል ብለዋል። አክለውም በአፋር ክልል የአንበጣ መንጋ ያደረሰው ጉዳት በአንፃራዊነት ከዚህ ቀደም ከደረሰው ጉዳት ያነሰ ቢሆንም፣ አሁንም በአርሶ አደሩ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የፌዴራል መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፣ በአፋርና በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ወረዳዎች፣ የአንበጣን መንጋ ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት አብረው ባለመሥራታቸው ያጋጠሙትን ፈተናዎች አባብሶታል ብሏል። በሁለቱ ክልሎች መካከል የሥራ ግንኙነት ባለመኖሩ፣ የአንበጣ መንጋን ሥርጭት ለመቆጣጠርና የሰብል ውድመትን ለመቀነስ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ የአፋር ክልል ወሳኝ ኩነት ኃላፊ አቶ ሁሴን ጠቁመዋል።

አያይዘውም በአፋር ክልል በተደጋጋሚ የአንበጣ መንጋ ወረራ በመከሰቱ ምክንያት የፌዴራል መንግሥት ዕገዛና ክትትል እንደሚያስፈልግና ለተጎዱ አርሶ አደሮች ወቅታዊ ዕርዳታ ለመስጠት ቀልጣፋ ምላሽ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

‹‹በአፋር ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች  አስቸኳይ ዕርዳታ ጠይቀዋል፤›› ያሉት አቶ ዓሊ፣ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ጥያቄዎች መካከል የአንበጣ መንጋውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ፀረ ተባይ አስፈላጊ ነው ብለዋል። አክለውም በየጊዜው የአንበጣ መንጋ ጥቃቶች በተደጋጋሚ በመከሰታቸው አፋጣኝ ትኩረት እንደሚጠይቅ፣ ሰብሎችን ለመጠበቅ ንቁ ዕርምጃ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል። እንዲሁም የአንበጣ መንጋ ወረራን ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት የተቀናጀ የተባይ መቆጣጠሪያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን ጨምሮ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ መስጠት አስፈላጊነትን አሳስበዋል።

‹‹የአንበጣን ወረራ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በአጭር ጊዜ ዕፎይታ ላይ ብቻ ሳይሆን ፣ ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር አለብን፤›› ያሉት አቶ ዓሊ፣ መንግሥት ይህንን የሚከታተል ግብረ ኃይል በማቋቋም ተደጋጋሚ ችግሮች ለመፍታት ሥልቶችን መቀየስ አለበት ብለዋል፡፡ የአንበጣ ባህሪንና ፍልሰት ሁኔታ የሚያመላክቱ ሥነ ምኅዳራዊ ሁኔታዎች ላይ ጥናት ማድረግ፣ እንዲሁም መንጋዎችን በፍጥነት ለማወቅና ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ማዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ ዓሊ ሌላው የመፍትሔ ሐሳብ ያሉት በትግራይና በአፋር ክልሎች በየጊዜው የሚከሰተው የአንበጣ ወረራ መጠን በመገንዘብ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከአጋሮች ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቅ ነው፡፡ ይህ ትብብር የአንበጣ መንጋ ሥጋትን ለማስወገድ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ በማግኘት አገሪቱ ያላትን አቅም ማጠናከር አለባት ብለዋል። ሀብትና ዕውቀትን በማሰባሰብ የአንበጣ መንጋ ተፅዕኖን ለመቅረፍና ተጋላጭ የግብርና ማኅበረሰቦችን ለመጠበቅ በጋራ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል። 

አቶ ዓሊ እንዳሉት፣ በትግራይና አፋር ክልሎች የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለው ውድመት በዚሁ ከቀጠለ፣ በአርሶ አደሮችና በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ፀረ ተባይ መድኃኒቶችንና ግብዓቶችን ወዲያውኑ ማቅረብን ጨምሮ፣ ድጋፍ ለመስጠት አስቸኳይ ዕርምጃ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን መራራቅ በማጥበብ ውጤታማ የመከላከያ ዕርምጃዎችንና የቀውስ መላሽ ዘዴዎችን ለማጠናከር በጋራ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...