Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አስተዳደሩ ያወጣውን የመሬት ሊዝ ጨረታ ያሸነፉ ከ150 በላይ ተጫራቾች ውል ፈጸሙ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግንቦት ወር ይፋ ባደረገው የመሬት ሊዝ ጨረታ፣ አንደኛ የወጡና ሁለተኛ ሆነው ያሸነፉ ተጫራቾችን ጨምሮ፣ ከ150 በላይ የሚሆኑ አሸናፊዎች የመሬት ሊዝ ውል መዋዋላቸው ታወቀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ሊዝ ጨረታውን ተወዳድረው በአንደኛ ደረጃ ካሸነፉ 287 ተጫራቾች መካከል 156 ያህሉ አሸናፊዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ቀርበው የሊዝ ውሉን ባለመዋዋላቸው፣ ሁለተኛ የወጡ ተጫራቾች አንደኛ የወጡ ተጫራቾች ያቀረቡትን ዋጋ ከፍለው የሊዝ ውል እንዲዋዋሉ ከዚህ ቀደም ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ሪፖርተር የመሬት ሊዝ ጨረታው ውጤት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የመሬት ልማትና አስተዳደር ሠራተኛ፣ በሊዝ ጨረታ አሸናፊ ሆነው ባልቀረቡ ተጫራቾች ምትክ ዕድል ከተሰጣቸው ሁለተኛ ተጫራቾች 15 ያህሉ ቀርበው ውል መዋዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ ሦስት ያህሉ ደግሞ እንደሚዋዋሉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመሬት ሊዝ ጨረታውን በተቀመጠው የጊዜ ቀነ ገደብ ቀርበው ውል የተዋዋሉ 135 የአንደኛ ደረጃ አሸናፊዎችን ጨምሮ በድምሩ ከ150 በላይ አሸናፊዎች ቀርበው ውል እንደተዋዋሉ፣ ሁሉም አሸናፊዎች ወደ ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች አገልግሎት እንዲያገኙ መላካቸውን፣ እንዲሁም ክፍላተ ከተሞቹ ወሰኑን እያስከበሩ አሸናፊዎቹ ቦታው በሚፈቅደው መሠረት ወደ ግንባታ እንዲገቡ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡

የተረፉ ቦታዎች ካሉ ወደፊት በሚወጣ የሊዝ ጨረታ ታሳቢ ተደርጎ በድጋሚ እንደሚቀርቡ፣ የሥራ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ አክለውም ጨረታው መቼ ይደረጋል የሚለውን አሁን መግለጽ እንደማይቻልና ቦታዎቹ መዘጋጀታቸው እርግጠኛ መሆኑ ሲረጋገጥ የሚወጣ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሊዝ ጨረታ እንዲተላለፉ የተዘጋጁት 297 ይዞታዎች በአጠቃላይ 143 ሺሕ ካሬ ሜትር (14.3 ሔክታር) ሲሆኑ፣ ይዞታዎቹ በአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች የሚገኙና ለተለያዩ አገልግሎቶች የተዘጋጁ የልማት ቦታዎችን መሆናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ከግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በይፋ ተከፍቶ አሸናፊዎቹ የተለየው የአንደኛው ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ አሸናፊዎች ስም ዝርዝር ባለፈው ወር ይፋ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ በዚህ ጨረታ ዝቅተኛ ዋጋ የተመዘገበው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሲሆን፣ ይህም በካሬ ሜትር 20 ሺሕ ብር እንደሆነ፣ ከፍተኛው ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ መሆኑ ተጠቁሞ ይህም በካሬ ሜትር 414 ሺሕ ብር እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቆ ነበር፡፡

የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮው በሊዝ ጨረታ አሸናፊ ሆነው ባልቀረቡ ተጫራቾች ምትክ ዕድል የተሰጣቸው ሁለተኛ ተጫራቾች፣ በተሰጠው ዕድል የማይጠቀሙ ከሆነ ጨረታው ተሰርዞ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ ሊገባ እንደሚችል ከዚህ ቀደም መገለጹ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል በሊዝ ጨረታው ተሳትፈው ሁለተኛ ደረጃ አሸናፊ ዝርዝር ውስጥ መካተታቸውን የገለጹ አስተያየት ሰጪዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሁለተኛ አሸናፊዎች በሰጡት ዋጋ ውል እንዲዋዋሉ የመከራከሪያ ሐሳብ ቢያቀርቡም የከተማ አስተዳደሩ ጉዳዩ በመመርያ የተገለጸና አይሆንም የሚል አቋም ይዟል ሲሉ አስታውቀው ነበር፡፡

አንደኛ አሸናፊዎች ባቀረቡት ዋጋ መዋዋል አዳጋች እንደሆነ፣ አሸናፊዎቹ ያቀረቡት ዋጋ የመሬት ሊዝ ጨረታው ከረዥም ጊዜ በኋላ የወጣ በመሆኑ በሽሚያ የተደረገና ምናልባት አዋጪ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ ቢያንስ ግማሽ ያህሉ አንደኛ አሸናፊዎችም ይካፈሉበት ነበር ሲሉ አስተያየት አቅራቢዎቹ በወቅቱ ማስረዳታቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች