Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበ674 የታክስ ይግባኝ መዛግብት ላይ ውሳኔ ተሰጠ

በ674 የታክስ ይግባኝ መዛግብት ላይ ውሳኔ ተሰጠ

ቀን:

የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በ674 የይግባኝ መዛግብት ላይ ውሳኔ መስጠቱን አስታወቀ፡፡ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሆነውና በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት በሚጣሉ የታክስ ውሳኔዎች፣ የታክስ ከፋይ ኅብረተሰብ የሚያቀርባቸው ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን መርምሮ ውሳኔ የሚሰጠው ኮሚሽኑ፣ ይህንን ያስታወቀው ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት 991 መዛግብት እንደቀረቡለትና በ677 መዛግብት ለውሳኔ ተቀጥረው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በ674 መዛግብት ላይ ውሳኔ መስጠቱን አብራርቷል፡፡ ውሳኔ የተላለፈባቸው መዛግበት 3.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው አስታውቀዋል፡፡

ውሳኔ ከተሰጠባቸው መዛግብት ውስጥ 444 ያህሉ የጉምሩክ ሲሆኑ፣ የተቀሩት 230 መዛግብት ደግሞ ከገቢዎች የቀረቡ ናቸው ተብሏል፡፡ ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ ከተቋቋመበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2015 በጀት ዓመት ድረስ ከ3,854 መዛግብት ውስጥ ለ3,684 መዛግብት ውሳኔ ሰጥቼያለሁ ሲል አስታውቋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ ቅሬታዎችን እየተቀበለ ቆይቷል፡፡ አስካሁን 14.4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መዛግብትን ተመልክቶ ውሳኔ ሰጥቷል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ሲደራጅ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ደረጃ ሆኖ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ የሚያያቸው መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል።

በተጠናናቀው የበጀት ዓመት ከኮሚሽኑ ለይግባኝ የቀረቡ ወይም ‹‹ቅሬታ አለን፣ በውሳኔያችሁ አልረካንም›› ብለው ከገቢዎችና ከጉምሩክ ይግባኝ ከተጠቀባቸው 397 መዛግብት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የከፍተኛ ፍርድ ቤት መርምሮ ያስቀርባሉ ብሎ ወደ ኮሚሽኑ የመለሳቸው መዛግብት 47 መሆናቸው ታውቋል። ከቀረበው ቅሬታ አንፃር የተመለሱት ቁጥራቸው አነስተኛ መሆን ለኮሚሽኑ ውሳኔዎች ጥራት አመላካች ነው ተብሏል።

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ የአንድ መዝገብ የቆይታ ጊዜ 120 ቀን (አራት ወር) የሚል ድንጋጌ የሠፈረ ቢሆንም፣ ነገር ግን መዝገቡ ውስብስብ ከሆነ የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት በሁለት ወራት ሊያራዝመው እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይሁንና ጉዳዩ በገንዘብ ላይ የተመሠረተና የሒሳብ ግንዛቤና ዕውቀት ያላቸው ሰዎች የሚከራከሩበት ስለሆነና ከኮሚሽኑ ዳኞችም አብዛኞቹ የሕግ ባለሙያዎች እንጂ ከአካውንቲንግ ጋር የተዛመደ የትምህርት ዝግጅት ስለሌላቸው መዛግብት እንደሚዘገዩ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ምዝገባ የሚያደርጉ ተገልጋዮች በአካል ቀርበው እንዲመዘገቡ ይጠበቅባቸው እንደነበረ፣ በአሁኑ ወቅት የኦንላይን ምዝገባ አሠራር ተዘርግቶ ይህንንም የማስተዋወቅ ሥራ ከማከናወን ባሻገር እየተሠራበት መሆኑን፣ ነገር ግን መዛግብትን በፍጥነት ለማውጣትና ጥራት ያለው ውሳኔ ለመስጠት ኮሚሽኑ ዘወትር ግምገማ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን የፕላንና ለውጥ ማስተባበሪያ ዋና ዳይሬክተር አቶ እዮብ ዓለማየሁ እንደገለጹት፣ የተቋሙ ዋነኛ ዓላማ የታክስና የጉምሩክ ቅሬታዎችን ተቀብሎ በሕግና በአሠራር መርምሮ ውሳኔ መስጠት ነው።

 ከመዝገብ አፈጻጸም አንፃር በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 776 መዝገቦች ቀርበው 746 መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸው፣ የኮሚሽኑን ተልዕኮ ውጤታማነት የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።

የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በገቢዎች ሚኒስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን ላይ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች መጀመሪያ ቅሬታቸውን ለተቋማቱ አቅርበው ምላሽ ካላገኙ፣ በይግባኝ ቅሬታቸውን ተቀብሎ ውሳኔ እንዲሰጥ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ተቋቁሞ በ2011 ዓ.ም. ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...