Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከበልግ እስከ ክረምት የዘለቀው ጎርፍ

ከበልግ እስከ ክረምት የዘለቀው ጎርፍ

ቀን:

ክረምት በገባ ቁጥር አዲስ አበባን ከሚፈትኗት ችግሮች መካከል የጎርፍ አደጋ ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም ችግሩን ለመቅረፍ ቀጣይነት ያለውና መሠረታዊ ሥራዎች ባለመሠራታቸው ችግሩ ዛሬም ድረስ ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡

በ2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀርመን አደባባይ በጉድ ሳማሪታን ግቢ ውስጥ የገባ ጎርፍ፣ በአንድ ጊዜ የስምንት ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የጎርፍ አደጋ፣ ለከተማዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ከባድ ተብሎ የተመዘገበ ነው፡፡

የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህንን ተከትሎ በአዲስ አበባ መሰል አደጋዎች እንዳያጋጥሙ ተቋሙን ጨምሮ ስምንት የዘርፉ ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት መጀመራቸው ችግሩን ባያስቀረውም፣ ከቀደመው ጊዜ አደጋውን ለመቀነስ አስችሏል፡፡

ለኮሚሽኑ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት፣ ተጋላጭ ቦታዎችን በመለየት የአደጋ ሥጋት መጠን ዳሰሳ ተሠርቶ የመፍትሔ ሐሳቦችን ሲያመላክቱ መቆየታቸውን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል፡፡

እስካሁን የጎርፍ ጉዳይ በሚዲያው የሚነሳውና ተቋማትም ችግሩን ለመቅረፍ መንቀሳቀስ የሚጀምሩት ክረምቱ ጠጋ ሲል እንደነበር፣ ይህ ትክክል አይደለም በሚል ዘንድሮ በጥቅምት ወር ዳሰሳ ተሠርቶ በአዲስ አበባ 168 ቦታዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ተብለው መለየታቸውን አክለዋል፡፡

ቦታዎቹን ከመለየት ባለፈ ምክረ ሐሳብ መስጠታቸውን፣ በዚህም ከቦታ መነሳት ያለባቸው እንዲነሱ፣ የአደጋ ማቅለያ ሥራዎች እንዲሠሩ፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች  በበቂና በጥራት በሌሉባቸው ሥፍራዎች ማስተካከያ እንዲደረግ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር ለሚሠሩ ተቋማት መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት ተቋማቱ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙና በተለይ አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል ተብለው በተለዩ 58 ቦታዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከቦታው እንዲነሱ፣ የድጋፍ ግንብ የሚያስፈልጋቸው እንዲሠራላቸው እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የቱንም ያህል ቢሠራ አደጋውን ዜሮ ማድረግ ስላልተቻለ አደጋው እየተከሰተ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ በተለይም በወንዝ አካባቢ አደጋዎች  መከሰታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የተሠሩ ሥራዎች በየሳምንቱ  እንደሚገመገሙ፣ በቀጣይ ክረምትም በጎርፍ ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡

በበልግ ዝናብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ማንጎ ሠፈር ያጋጠመው የጎርፍ አደጋ፣ ለአደጋ ተጋላጭ ተብለው ከተለዩት መሀል ሲሆን፣ በስፍራው በዘልማድ የጨረቃ ቤት ተብለው የሚጠሩትና በአግባቡ ያልተሠሩ ቤቶች ተንደው የአራት ሰዎች ሕይወት ያለፈበትን ክስተት አስታውሰዋል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 32 ቀበሌ እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ እናት ከሁለት ልጆቿ ጋር የሞችበት የጎርፍ አደጋም፣ ተጋላጭ ተብሎ የተለየ ነው፡፡

አስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉት ውጭ አዳዲስ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችም አጋጥመዋል፡፡

ችግሩን ለማቅለል እየተወሰዱ ካሉ ዕርምጃዎች ነዋሪዎችን ከአካባቢው ማንሳት ይገኝበታል፡፡ አቶ ንጋቱ እንደሚሉት፣ አልፎ አልፎ ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ ሥፍራዎች  የተነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተመልሰው ይሠፍራሉ፡፡ ቦታው በአብዛኛው ሕገወጥ ስለሚሆን ቦታው ይፀናልናል በሚል ጉጉትና ፍላጎት ከተነሱ በኋላ ቦታው ላይ ተመልሰው ስለሚመጡ ለአደጋ እየተጋለጡም ነው፡፡

በተቋማቸው በኩል ነዋሪዎች ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ ሥፍራዎች መነሳት አለባቸው ብለው ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ መሠረት፣ አብዛኞቹ መነሳታቸውንና እየተነሱ መሆኑን፣ ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ ዝግ ስለሆኑ ነዋሪዎችን ወደዚያ ማዘዋወር መጀመሩን፣ በሕጋዊ ወይም በቀበሌ ቤት ለሚኖሩ ምትክ ኮንዶሚኒየም ወይም ምትክ የቀበሌ ቤት የተሰጣቸው እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

አልፎ አልፎ ከሕጋዊነት ጋር ተያይዞ ‹ቦታችንን እናጣለን› የሚል ሥጋት ያላቸው ለመነሳት ፈቃደኛ እንደማይሆኑ በመግለጽም፣ ‹‹በእኛ በኩል ሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ያልሆኑ ሰዎች በቦታው ላይ ለመቀመጥ በሕይወት መኖር አለባቸው ብለን ስለምናምን  የማሳመን ሥራ እንሠራለን፣ ፈቃደኛ ያልሆኑትን አስገድደንም ቢሆን ከቦታው የሚነሱበት ሁኔታ ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡

ከወንዝ ዳርቻ ከሚኖሩ ማኅበረሰቦች በተጨማሪ በየዋና መንገዱ የሚንጣለለው ጎርፍም የከተማዋ ችግር ነው፡፡

ለአዲስ አበባ የሚመጥን የፍሳሽ ማስወገጃ ማስተር ፕላን አለመኖርና ቀደም ሲል ያሉት የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች በወቅቱ የነበረችውን አዲስ አበባ መሠረት አድርገው የተሠሩ መሆናቸው፣ ያሉትም ቢሆን በደረቅ ቆሻሻዎች የሚዘጉ በመሆኑ ዝናብ በጣለ ቁጥር ጎርፍ መሄጃ እያጣ ሰዎችንም ተሽከርካሪዎችንም ያውካል፡፡

ይህንን ተከትሎ ኮሚሽኑ ተጨማሪ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች እንዲሠሩ፣ ያሉትም በቋሚነት በሳምንት አንዴ እንዲፀዱ በሰጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት የማፅዳት ሥራው ተጀምሯል ብለዋል፡፡

በከተማው አንዳንድ ቦታዎች የፍሳሽ ማስተላለፊያ ጉድጓዶች (ማንሆሎች) ክዳናቸው ተነስቶ በውኃ የሚሸፈኑበት ሁኔታ በመኖሩ፣ ዓይነ ሥውራንም ሆኑ ዓይናማ ጉድጓድ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት አጋጣሚ ስለሚኖር ጉድጓዶች እንዲከደኑ ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋር እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በችግሩ እየተጠቁ ያሉት ታዳጊዎች መሆናቸውን፣ ትምህርት በመዘጋቱ ልጆች ቤት በሚውሉበት ጊዜ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው፣ በተለይ ወንዝ አካባቢ የሚኖሩ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ለጨዋታ ብለው ለቀው የጎርፍ ሰለባ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...