በአበበ ዘገየ (ፕሮፌሰር)፣ ኦክስፎርድ እንግሊዝ
‹‹ወሰን የአንድ ነገር ማብቂያ ሳይሆን፣ ድንበሩ የአንድ ነገር መጀመርያ ነው›› (ማርቲን ሄይድገር)
አፍሪካውያን ለመከለስም ለማስቀጠልም ዕድል ያለው የዳበረ የባህል ክምችት ባለቤት ናቸው፡፡ የቅኝ ግዛት ዘመን ተራ የወታደራዊ ማስገበር ብቻ ሳይሆን እውነትን የመቀየር ወይም የማስለወጥ፣ የአውሮፓውያንን የሥነ ዕውቀት፣ የሥነ ምግባርና የሥነ ውበት መለኪያዎችን በአፍሪካውያን ላይ የመጫን ሒደት ነበር፡፡ በአፍሪካውያን ነባር ሕዝቦች ውስጥ ያለው እውነት ከአውሮፓውያን ውስጥ ካለው እውነት የተለየ ነበር፡፡ እውነት ምንድነው? ብለን ጥያቄውን የጲላጦስና የኢየሱስ ጥያቄና መልስ አናደርገውም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር እናምናለን፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው የአካል ወይም ክስተት ትርጉምና ግንዛቤ በአብዛኛው በምዕራባውያን ነጽሮተ ዓለም (World View) እውነት አንፃር ነው የሚተነተነው፡፡
በአንድ ማዕከላዊ የአፍሪካ የደን መንደር ውስጥ ራስ ምታት ሕመም አይደለም፣ ሰዎች መድኃኒት ላይወስዱ የሚችሉበት አጋጣሚ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ በእንግሊዝና በቀሪው የምዕራብ ዓለም ራስ ምታት (ማይግሪን) አደገኛ ሥር ሰደድ የሚባል የሕመምነት ትርጉም አለው፡፡ ለዚህ በየወሩ ወይም በየሳምንቱ መድኃኒት የሚወስዱ ታማሚዎች አሉ፡፡ አሁን በሽታው ተመሳሳይ ቢሆን ትንታኔውና ትርጉሙ የተለየ ነው፡፡
የአፍሪካ ጥበቦች የምዕራቡ ዓለም ትርጉምና የጥብበ ዕድገት ሰለባዎችም ተጠቃሚዎችም ናቸው፡፡ የአፍሪካ ጥበብ በምዕራባዊ ቦይ ለዘመናት ፈሶ ከዚያ ሲያልፍ ከቅኝ ግዛት ትግሎች ላይ ትኩረት አድርጎ የራሱ ቃና ሳይኖረው ለዘመናት ቆይቷል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአፍሪካ የምንለው የምዕራብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በምዕራባውያን የጥበብ ሥራዎችም ውስጥ የአፍሪካን ጥበብና አስተሳሰብ እናይበታለን፡፡
ድኅረ ዘመናዊነት ጠቅላይና ጨፍላቂ የሚመስሉ ትልልቅ ትርክቶችን፣ አስተሳሰቦችንና ባህልን በሥር ነቀል ደረጃ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ ለብዝኃ ባህልና አስተሳሰብ፣ ለብዝኃ ትርክቶች ቦታ ሰጥቷል፡፡ ድኅረ ዘመናዊነት በዋናዎቹ የዓለም ትልልቅ ባህሎችና አስተሳሰቦች ተሸፍነው ያልታዩና ያልተሰሙ ድምፆችን ለብዙኃን ሕዝብና ለአካዴሚያዊ ምርምር ተደራሽ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል።
በጥንታዊ የአፍሪካ ማኅበረሰብ፣ ጎሳዎችና ተደራሽ ያልሆኑ የአፍሪካ መንደሮች ያሉ አፈታሪኮች፣ እምነቶች፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የጥበብ ሥራዎች ከመንደራቸው አልፈው ለዘመናዊ ሠዓሊዎች ለሙዚቃና ለሌሎች የጥበብ ዘርፎች መዋል የጀመሩት በቅርቡ ነው ቢባል አይጋነንም፡፡
የአፍሪካን ጥበብ ከቅኝ ግዛት በፊት ከነበሩ አምባገነኖችና ከቅኝ አገዛዝ በኋላ ከመጡ አምባገነኖች ጋር ለረዥም ጊዜ ያልተቋረጠ የትግል ታሪክ ብቻ አድርጎ ለማሳየት የሚደረጉ ሙከራዎች የተሳሳቱ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ጥበብ ከዚህ አልፎ ሌሎች ከፍ ያሉ እሴቶችን፣ ክስተቶችን፣ አስተሳሰቦችን ወዘተ እየወከለ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የአፍሪካ ጥበብ የአምባገኖችን ትግል ማሳየት የለበትም ማለት አይደለም፡፡ በሌላ አገላለጽ ስለ አፍሪካ ሥነ ጥበባትና በሚተርካቸው እውነታዎች ላይ ስንጽፍ በማርቲን ሄይድገር ግንዛቤ በአፍሪካ ሥነ ጥበባትና በእውነታው ድንበሩ ላይ አንድ ነገር መታየት የሚጀምርበት ነው፡፡ ይህ ከድንበሩ በኋላ መታየት የጀመረው በብዙ የባህል ቦታዎች የተገለጹትን የአፍሪካን ጥበብ ብዝኃነትንና እውነታዎች ነው። እንደ ባህል ብዝኃነቱ ልክ ብዙ ትልልቅና አስደማሚ የኪነ ጥበቦች ለዓለም አቀፍ መድረኮች በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ጥበብ ልዩ የሆነው የ‘ቅድመ ዘመናዊው፣ ‘ዘመናዊ’ እና ‘ድኅረ-ዘመናዊ’ መንፈስን ስላካተተ ነው።
ኢትያጵያ የቀደምት ባህል፣ ሥርዓተ መንግሥት፣ ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍና ኪነ ጥበብ ባለቤት አገር ናት፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በርካታ የባህል ገጽታዎች ያሏቸው ጎሳዎች መኖራቸው በዚህ ከፍተኛ ብዝኃነት ውስጥ ብዙ የአመለካከት፣ የፍልስፍና፣ እምነትና ባህል ክስተቶች መኖራቸው በዚሁ ልክ ለዘመናዊ የጥበብ ባለሙያዎች መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ የሥዕል ጥበባት ከአክሱም እስከ ላሊበላ ከላሊበላም እስከ ዘመናዊ ኢትዮጵያ ለረዥም ዘመን የቆየ ዕድገት አላቸው፡፡ ነገር ግን ባህላዊ፣ አመለካከታዊና ጥንታዊ አስተሳሰቦች በሥዕልና በሌሎች ጥበባት ጎልተው አልወጡም፡፡
ኢትዮጵያ አያሌ መቶ ዓመታት የተሻገረ የኪነጥበብ ታሪክ አላት። ከሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ አገኘሁ እንግዳ ድረስ ኢትዮጵያ ከቀደምት እስከ ዘመናዊ የጥበብ ባለሙያዎች ባለቤት ነች፡፡ ከዚህ አስደናቂ የአፍሪካ አገር ድንቅ አርቲስት ወርቅነህ በዙ ወጣትነቱን ዘመኑን ለጥበብ ሰጥቶ በብዙ ስኬቶች ታጅቦ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እያደረሰ ነው፡፡
መጋቢት 8 ቀን 1978 ዓ.ም. የተወለደው ወርቅነህ በዙ ካሳ አዲስ አበባ ውስጥ ነው ያደገው። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የሥዕል ፍቅር የነበረው ወርቅነህ በአንደኛ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመሣል የጥበብ ችሎታን ማሳየት ችሏል። ቤተሰቦቹ አውቶ መካኒክ እንዲሆን ሲመኙለትና ሲያበረታቱት የነበረው ወርቅነህ የጥበብ ጥሪውን በመከተል በአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ገብቶ የሥዕልና የቅርፅ ሙያን ተምሯል።
ለወርቅነህ ጥበብ ሕይወቱ፣ ፍላጎቱና ሕልሙ ነው። የሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ ሥልጠና መውሰዱ ወርቅነህ ሕልሙን ዕውን ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ክህሎቶች እንዲያዳብር ረድቶታል፡፡ ወርቅነህ በተለያዩ ጥበባዊ ቅርፆች ሞክሮ በኢትዮጵያ የሕፃናት አሻንጉሊት ፊልምና አጭር አኒሜሽን ፊልም ፈር ቀዳጅ ለመሆን በቅቷል። በፈጠራው ውስጥ የተካተቱት በተለያዩ ኅብረ ቀለማት በዘይትና በውኃ ቀለም የተቀረፁ ሥዕሎች፣ ቅርፃ ቅርፆችና የግራፊክስ ጥበብ ናቸው።
የወርቅነህ የጥበብ ሥራዎች የ13 ወራት ባለቤት አገርን በስሜን ተራሮች፣ ከገዳም እስከ ቤተ መንግሥት፣ እንዲሁም የበርካታ ኢትዮጵያውያን ጎሳዎች አስተሳሰብ፣ እምነት፣ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ ተጨምቀው የተፈጠሩ ዕይታዎችን ይዞልን መጥቷል፡፡ ወርቅነህ ሥዕሎቹን ከታሪክ ክስተትና ከአካባቢው ተነስቶ እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ በዚህ የሥዕል ፈጠራ ውስጥ በወርቅነህ ውስጥ ኢትዮጵያን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አፍሪካን እናያታለን ብንል መድፈር አይሆንም፡፡ ብዙ ሥራዎቹን በሰሜን አሜሪካ (ኒውዮርክ ከተማ፣ አሌክሳንድሪያ፣ ቨርጂኒያና ሜክሲኮ) ለማሳየት ዝግጅቱን ጨርሷል። ከአማልክቱ ጋር ማዜም (ዝማሬ) በሚልም ተሰይሟል፡፡ ይህ የጥበብ ስብስብ የአርቲስቱን የሥዕል ልምድና ከሃያ ዓመታት በላይ ያካበተውን የአስተሳሰብ ጭብጥ የሚያሳይ እንዲሁም ከፍተኛ ሙያውንና የሕይወት፣ የታሪክ ክስተት ግንዛቤውን ጨምቆ የሚያቀርብበት ትልቅ ዓውደ ርዕይ ነው፡፡
የወርቅነህ በዙ የጥበብ ሥራዎች፣ ሁሌም ልዩ፣ የኢትዮጵያን ባህል ጭብጦች – ተረቶቹን፣ ልማዶቹን፣ የመናፍስትን እምነት – ወደ ዘመናዊ ጥበብ የማሸጋገር ችሎታው እያደገ መምጣቱን ያሳያሉ። በዓውደ ርዕዩ ይዞልን የቀረበው ስብስብ ሥራዎችም በጊዜ ሒደት፣ ሥራው የበለጠ የተዋጣለት፣ የበለጠ በትርጉም አገላለጽ አድጎ መምጣቱን ያሳያሉ፡፡ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ጥንታዊ አስተሳሰቦችና ሕዝቦች መካከል ከሚታየው አካላዊ ክስተት የበለጠ የማይታዩ መናፍስቶች የሰዎችን ደስታ ጤና፣ የባህልና የኢኮኖሚ ሁኔታ እየወሰኑና እንደሚወስኑ እየታመነባቸው ለዘመናት አልፈዋል፡፡ በተጨማሪም ግሪኮቹ ሚቶሎጂ እንደሚሉት የአፍሪካ ተረቶችና አፈ ታሪኮች ለልጆች ማጫወቻና ማስፈራሪያ ከመሆን አልፈው ለትልልቅ ንግግሮች ማጠንከሪያና ማሳመሪያ ይሆናሉ፡፡ የዘመናዊ ትምህርትና አስተሳሰብ መምጣት ተከትሎ ግን የመናፍስት እምነት ብሎም መናፍስትን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፈው ተረቶች ተረስተው ወደ መቅረት እየተቃረቡ ነው፡፡ እነዚህ ጥንታዊ የመናፍስት እምነቶችን በጥንታዊ መንደሮች የሚኖሩ ተረቶችን፣ አፈ ታሪኮችን ከጥበብ አንፃር ማሳየት ለአፍሪካ ዘመናዊ ጥበብ አንዱ አካል ነው፡፡
ይህን የአፍሪካ አማልክት፣ ከአማልክቱ ጋር ዝማሬ የሚለው የወርቅነህ የሥዕል ስብስብ ስናቀርብ በታላቅ ደስታ ነው። ለዕይታ የቀረቡት ሥራዎች የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን የበለፀጉ ባህላዊ አስተሳሰቦች ማሳያዎች ናቸው። አርቲስቱ በሥዕሎቹ ውስጥ የአፍሪካን አማልክት ምንነት በችሎታ ውስብስብ በሆኑ የቀለማት ቅብ ወደ ሕይወት አምጥቷቸዋል፣ አፍ አውጥተው እንዲናገሩ አስችሏቸዋል፣ እንዲያናግሩንም ማድረግ ችሏል። እያንዳንዱ የጥበብ ውጤት ልዩ የሆነ የታሪክ ዳራ እየነገረን በየግል ምልከታችንና የማነነት ሥሪታችን ልክ ትርጉም እንድንፈልግና ሕይወታችንን ከዚህ ትርጉም ጋር እንድናቆራኝ ያደርገናል፡፡
የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ጭብጥ ዘርፈ ብዙና ጥልቅ የመሆን ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከእረኞች ተረቶች፣ እንካ ስላንቲያ እስከ አዋቂዎች ሥነ ቃል፣ ከእንቆቅልሽ ጨዋታ እስከ ልጅነት ትዝታዎች፣ ከታላቆቹ ክርስትናና እስልምና ቤተ እምነቶች እስከ ማኅበረሰባዊ ጥንታዊ እምነቶች፣ ካልተበረዘው የጥንታዊ ባህል እስከ ዘመናዊ የባህል መስተጋብር ሁሉም ለአርቲስቶች የሐሳብ ክምችት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ወርቅነህ ሥዕሎቹን ከታሪክ ክስተትና ከአካባቢው ተነስቶ እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ በዚህ የሥዕል ፈጠራ ውስጥ ልጅነቱን፣ ዕድገቱን መንደሩን፣ አገሩን ኢትዮጵያን ከአስተሳሰባዊ ግንዛቤ ወደ ተዳሳሽ ተጨባጭ ጥበብ ለውጦ ያሳየናል፡፡
በጥበብ ሥራ ላይ ከአሠርታት በላይ እንደመቆየቱ በዚህኛው ሥራው ወርቅነህ በሐሳብ አድጎ በሥዕል ክሀሎቱ ዳብሮ በዓይነቱ ለየት ያሉ የጥበብ ሥራዎችን ይዞልን ቀርቧል፡፡ በርካታ ሥዕሎቹ ለተመልካች ክፍት የሆኑ በቀለማት ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የተሰወሩ ከተለያዩ የሕይወት ጓዳ ጎድጓዳ የተጠሩ አማልክትን አፍ አውጥተው እንዲናገሩ በማድረግ የተገለጡ ትርጉሞቹን አስቀምጦባቸዋል። ከመስመር ወደ ክበባዊ አሣሣል በመሸጋገር ሙያውን እያጎለበተ እዚህ የደረሰው ወርቅነህ በሽግግር ሒደት ውስጥ የአሣሣል ጭብጦችን ከሴት ውበት፣ እናት፣ ልጅ፣ የመልአክና አማልክትን ባልተገደብ ነፃነት ባልተገደበ የቀለማት ድብልቅ ከምናብ ወደ ገሃድ ላማቅረብ ጥሯል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው abebeyeshizegeye@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡