ከተለምዷዊ የአሠራር ሥልቶች ይልቅ አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት የወጣቱን የሥራ ዕድል ፈጠራና ተጠቃሚነት ማገዝ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ከወጣቶች ጋር በተገናኘ የሚሠራቸውን ሥራዎችና በቀጣይ በትብብር ለመሥራት ስላቀዳቸው ጉዳዮች ከተለያዩ የሚዲያ አውታር ኃላፊዎች ጋር ዓርብ ሐምሌ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ባደረገው ውይይት ላይ ነው፡፡
የማስተርካርድ ፋውንዴሽን እ.ኤ.አ. 2018 ይፋ ያደረገው የአፍሪካ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፕሮጀክት በሁለት ጉዳዮች ማለትም በወጣቶች ትምህርትና በፋይናንስ አካታችነት አተኩሮ ለመሥራት የተቋቋመ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ያለው በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የተመሠረተበትን አሥረኛ ዓመት በ2016 ሲያከብር የሠራቸውን ሥራዎችን መለስ ብሎ ፈትሾ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ከተመለከታቸው ጉዳዮች ውስጥ ትልልቅ አበርክቶዎቹ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል ተብለው ከተለዩት ጉዳዮች የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር ዋነኛው መሆኑን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ የሚገኙ 30 ሚሊዮን ወጣቶችን በ2030 ሥራ እንዲያገኙ ወይም የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ አስችላለሁ በሚል የተነሳው ፋውንዴሽኑ፣ ከዚህም ውስጥ 21 ሚሊዮን ወይም 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ይሆናሉ የሚል ዕቅድ መንደፉን አስታውቋል፡፡ ከዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ለማሳካት የተቀመጠው ግብ አሥር ሚሊዮን የሚያህለው መሆኑ ተገልጿል፡፡
የታቀደውን ዕቅድ ለማሳከት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በነደፈው የአፍሪካ ወጣቶች የሥራ ዕድል ስትራቴጂ እንዴት ለ30 ሚሊዮን ወጣቶች ተደራሽ መሆን ይቻላል የሚለው ሲታሰብ፣ ከተለዩት ጉዳዮች ውስጥ በተለመደው መንገድ ሳይሆን አዳዲስ የአሠራር ሥልቶችን በመሞከር የሚለውን ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በግለሰቦች ላይ ብቻ በሚሠራው ሥራ ውጤት ስለማይመጣ በሲስተሙና በተቋማት ላይ መሥራት ሌላው ፋውንዴሽኑ የተመለከተው ጉዳይ መሆኑን ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ለማዳረስ የተፈለገውን ዕቅድ ዕውን እንዲሆን ከተለዩ ዘርፎች ግብርናና የግብርና ሥርዓት አንደኛው ሲሆን፣ ሁለተኛው ከግብርና ጋር ይተሳሰራል ተብሎ የታቀደው የአምራች ኢንዱስትሪ መሆኑን፣ እንዲሁም ዲጂታል ኢኮኖሚው ሌላኛው መሆኑን አቶ ሳሙኤል ለታዳሚያኑ አብራርተዋል፡፡
ከተገለጹት ዘርፎች በዘለቂነት የሚደግፍ የፋይናንስ ድጋፍ መዘርጋትና የክህሎት ሥልጠናዎችን መስጠትን ጎን ለጎን በማስኬድ ከ2019 ጀምሮ 950 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተፈቅዶለት ከዚህ ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነውን ለመጠቀም አብረውት ከሚሠሩት አጋሮች ጋር ስምምነቶችን መፈጸሙ፣ ከዚህም ግማሽ የሚሆነው ሥራ ላይ መዋሉን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ ዓለም አቀፍና አገራዊ ችግሮች እንደ ሌሎች ዘርፎች ያሳደሩት ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እስካሁን ግን ከታሰበው የአሥር ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ ውስጥ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ታክሏል፡፡
የተገለጹት ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው መረጃ ከማስተላለፍ ባሻገር የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ ምን ሊሠራ ይገባል? የሚለውን ለመመካከር ፋውንዴሽኑ ከሚዲያዎች ጋር ለመተዋወቅና አብሮ ለመሥራት መምረጡን የማስተካርድ ዋና ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡
በመድረኩ አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አማረ አረጋዊ የወጣቶች ጉዳይ ወቅታዊ የሆነ ጥያቄ መሆኑን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ ወጣት ከዚህ ቀደም ከነበረው ወጣት ይልቅ ብዙ ድጋፍ፣ ትምህርትና ልምድ የሚፈልግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ይህ የሚሆነው ወቅቱ ብዙ ችግር ያለበት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ወቅቱ አሳሳቢ የሆነ የትምህርት ሁኔታ ያለበት እንደሆነ፣ ትምህርት ቤት እያለ ተማሪው ግን ትምህርት ለመማር ዕድል ማጣቱ እንደሚስተዋል፣ ሥራ ለማግኘት ከሚያጋጥመው እክል ባሻገር በሥነ ልቦና ጉዳይም የኢትዮጵያ ወጣት ግራ መጋባት ውስጥ እንደሚገኝ አቶ አማረ ተናግረዋል፡፡
‹‹ዕድሉና ሁሉም ነገር በእጃችን እያለ እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡ ስለሆነም የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፕሮግራም ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ወጣቱ በአሁኑ ጊዜ ልዩ ችግር ውስጥም ስላለ ነው፤›› በማለት ያስረዱት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢው፣ ትምህርትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ወጣት ከየትኛውም የሃይማኖትና የብሔር ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሶ እንዲማር መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ሚዲያን ጨምሮ ልዩ ትኩረት መጫወት አለባቸው ብለዋል፡፡
ወጣቱ ያለበትን የሥነ ልቦና ችግር፣ ሥራ ለመጀመር የሚያግዝ የፋይናንስ ችግር፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ችግር ሊፈታለት እንደሚገባ የገለጹት አቶ አማረ፣ በኢትዮጵያ ዋነኛ የሆነውን ይህንን ሥራ አበክሮ የሚሠራ ሥርዓትና ተቋም መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አስተያየታቸውን የሰጡ የውይይቱ ታዳሚያን ወጣቱ የሚነሳሳበትን አማራጭ ብቻ መፍጠር በቂ እንዳልሆነ፣ መሥራት የሚችልበትን ሥነ ምኅዳር መፍጠር እንደሚገባ፣ የሥራ ፈጠራ ፕሮግራሞችን ተቋማት ማገዝ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
ሚዲያውም የወጣቱ ሥነ ልቦና ውቅር ላይ ሥራውን እንዲሠራ፣ አዕምሮውን ሊቀይሩና ሊያነሳሱ የሚችሉ ሥራዎችን እንዲተገብር ተቋማት በጋራ መሥራት እንዳለባቸው የሚዲያ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡