እባብ በክረምት ውኃ ሞልቶበት ዳር ዳሩን ሲንቀዋለል አንድ ሰው መጣ፤ እባቡም ሰውዬ እባክህ አሻገረኝ ብሎ ለመነው፡፡ ያም ሰው እጅ የለህ እግር የለህ ምንህን ይዤ ነው የማሻግርህ አለው፡፡ እባቡም ፈቃድህስ ከሆነ ራስህ ላይ ጠምጥመኝ ቢለው ጠምጥሞ አሻገረው፡፡ ካሻገረውም በኋላ በል ውረድልኛ ቢለው እምቢ አልወርድም አለ፡፡ ወደ ዳኞች (አራዊትም) ሁሉ ሂዶ ቢከሰው ዳኞቹ (አራዊቶቹ) በገዛ እጅህ እባብ ራስሀ ላይ ጠምጥመህ እያሉ ፈረዱበት፡፡
በመጨረሻውም በቀበሮ ዳኝነት ከስሰው ቀበሮዋም እባብን ምድር ወርደህ በግራ ቆመህ ሥርዓት ለብሰህ ተነጋገር አለችው፤ እሱም ተተረተረና ዱብ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ ቀበሮዋን ሰውዬው እህ አላት እሷም ሰው በትር ይዞ ቆሞ እባብ እምድር ተጋድሞ ብትለው ራስ ራሱን ብሎ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ ችሎትም ሲመለስ ብድሯን ለመክፈል ማታ በግ አመጣልሻለሁና ቤትሽን አሳዪኝ አላት፡፡ እሷም አስከትላው ሂዳ ቤቷን አይቶ ተመለሰ፡፡ ማታም ውሻውን አስከትሎ ሂዶ ከበር አፏ ቁሞ እንኰይ ቀበሩት ብቅ በዪ አላት በግ ይዞልኝ መጥቶ ይሆናል አለችና ብቅ ብትል ያዢ ኩቲ ብሎ ውሻውን ለቀቀባት፤ እሷም ሰው ሰው ሰው ለሰው ሞት አነሰው እያለች ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
- ደስታ ተክለወልድ ‹‹ገበታዋርያ›› (1926)