አንድ በሬ ብቻ የነበረው አንድ ድሃ ገበሬ ነበር፡፡ ታዲያ ሌላ አጣማጅ በሬ ተውሶ ለማረስ በጠየቀ ጊዜ ሁሉም ይከለክሉት ነበር፡፡ ‹‹አንተ ልመና ብቻ ነው የምታውቀው፤›› ይሉት ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በእርሻ ላይ ሳለም በእንስራ ሙሉ ወርቅ ያገኝና ይደብቀዋል፡፡ ከዚያም የበሬውን ሸኮና ቆረጠው፡፡ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው ‹‹ይህን ለምንድነው ያደረግከው?” ብለው ሲጠይቁት፡ ‹‹አልፈልገውም ለድሆች ይሁን›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አንተም ድሃና በቤትህ ውስጥ የምትበላው የሌለህ ሆነህ እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ?›› አሉት፡፡
እርሱ ግን ድርጊቱን ገፍቶበት ሲያበቃ ‹‹በሬውን እግዚአብሔር ስለሰጠኝ አሁን ደግሞ ለድሆች ምግብነት ይዋል፤››” ብሎ መለለሰላቸው፡፡ ሁኔታው ግራ ቢገባቸውም በሬውን አርደው ለድሆች አከፋፈሉት፡፡ ገበሬውም ወደ ቤቱ ተመልሶ ሚስቱን ‹‹ከረጢት ስጪኝና ተከተይኝ፤” አላት፡፡ አብረውም ሄደው ወርቁን ቆፍረው ካወጡ በኋላ ባለፀጋ ሆኖ ሀብት ሞልቶት ለእግዚአብሔር አሥራት እያስገባ መኖር ጀመረ፡፡
ፋጢማ አሊ ‹‹በርታ ተረት››