Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

እኔ ይህንን ገጠመኝ የምጽፍላችሁ ግለሰብ በምንም ምክንያት ምንም ነገር ለመጻፍም ሆነ አስተያየት ለመስጠት ፍላጎቴ ከቀዘቀዘ ስለቆየ፣ ለረጅም ጊዜ በአርምሞ ውስጥ በመሆን ማኅበረ-ፖለቲካ ጉዳዮቻችን ላይ የነበረኝን ዕሳቤ በውስጤ ሳብሰለስል ነው የከረምኩት፡፡ አሁን ግን በአንድ መሠረታዊ ጉዳያችን ላይ አስተያየት መስጠትና ገጠመኜን ማካፈል አለብኝ ብዬ ስለወሰንኩ፣ በዚህ መሠረት ውሳኔዬን ሽሬ ተከስቻለሁ፡፡ አንዳንዴ የሚያስገድዱ ጉዳዮች ሲኖሩ ግትር አቋምን በማላላት የሐሳብ ገበያው ውስጥ መንሸራሸር አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የረዳኝ በውስጤ ሲብላላ የከረመውን አንድ ጉዳይ አንድ የተባረከ ሰው በተባ ብዕሩ በምሁራዊ ዕይታ ስላብራራው ነው፡፡

ከወራት በፊት በጠዋት ተነስቼ ባልደራስ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቴ ወደ ዊንጌት አቅጣጫ እያሽከረከርኩ ስጓዝ፣ የመኪናዬን ሬዲዮ ከፍቼ ሙዚቃ ለማዳመጥ ጣቢያ ሳማርጥ አንድ ኃይለኛ አስገምጋሚ ድምፅ የአንደኛው የኤፍኤም ሬዲዮ ላይ ጆሮዎቼን ያዛቸው፡፡ ሰውዬው በዚያ የሚያስተጋባ ድምፁ ማንም ሰው የፈለገውን ማድረግ የሚያስችል ኢነርጂ እንዳለው፣ ካሰበበት ለመድረስም ቁርጠኛ ከሆነ ምንም ነገር እንደማያስቸግረው ነበር የሚናገረው፡፡ የተለያዩ ምሳሌዎችንና ተምሳሌቶቹን ከአገር ውስጥም ከውጭም እየጠቃቀሰ ሲናገር ትኩረት ይስብ ነበረ፡፡ ዊንጌት እስክደርስ ድረስ ሳዳምጠው ከሞላ ጎደል ሐሳቡ መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን በማር የተለወሰ መርዝ ሊሆን እንደሚችልም ልቤ መጠርጠሩን ባልናገር ልክ አይሆንም፡፡

በወቅቱ የእኔ ጥያቄ የእዚህን ሰው ሐሳብ እያንዳንዳችን የምናስተናግድበት የዕውቀት አቅምና የመረዳት ብቃት፣ እንዲሁም እሱና መሰሎቹ ያላቸው የዕውቀት ምንጭ ምን ያህል ሊሆን ይችላል የሚል ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ በአገራችን ብዙ ሰዎች ሥራ ይፈልጋሉ፣ መለወጥ ይሻሉ፣ ከድህነት ተላቀው የሀብት ማማ ላይ መድረስ ሕልማቸው እንደሆነ ስለማውቅ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ከዛሬው ኑሮ የነገው የተሻለ እንዲሆን የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፡፡ ነገር ግን የምንፈልገውን ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ‹‹አነቃቂ›› ተብለው በሚጠሩ ሰዎች የሚሰጠን ምክርም ሆነ ሥልጠና እኛ ዘንድ እንዴት ነው የሚሰርፀው የሚለው ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹አነቃቂዎቹ›› ራሳቸው የእነ ማንን ልምድ ነው የሚግቱን የሚለውም አሳስቦኝ ነበር፡፡

‹‹ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው›› እንደሚባለው ከዚህ በፊት በውጭ ኢአማንያን ተጽፈው በአማርኛ እየተተረጎሙ ብስለት ለጎደላቸው ሰዎች እንደ ወረደ ሲሸጡ የነበሩ መጻሕፍት፣ ጥልቅ የእምነት አስተምህሮ ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በረቀቀ መንገድ ድህነትን እየታከኩ ሲቀርቡ ሃይ ባይ መታጣቱ ድንቅ እስኪል ድረስ ሬዲዮ ጣቢያዎቻችን መፈንጫ ሆኑ፡፡ ለምሳሌ የስህበት ሕግ (Law of Attraction) እና ሚስጥሩ (The Secret) መጻሕፍት በ‹‹አነቃቂዎቹ›› በልዩ አቀራረብ ትውልዱ ላይ ሲነዙ፣ እንዲሁም በዓለም ታዋቂዎቹ የአዲሱ ዘመን እምነት (New Age Religion) አራማጆችና መሪዎች ተምሳሌት ሆነው ቀረቡልን፡፡

በልዩ ልዩ አንጀት አርስ ጽሑፎቹ የምናውቀው ጌታሁን ሔራሞ (ኢንጂነር) ፈጣሪ ይባርከውና ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በቅርቡ በፌስቡክ ገጹ ባሠፈረው ጽሑፍ በአሁኑ ጊዜ በ‹‹አነቃቂነት›› የሚታወቁ ሰዎችን ስሞች ጠቅሶ፣ የኤካርት ቶልና የድፓክ ቾፕራ አስተምህሮን እንደሚከተሉና የሚሰጧቸውም ሥልጠናዎች የተቃኘው እነዚሁ የአዲሱ ዘመን ሃይማኖት አስተማሪዎች በጻፏቸው መጻሕፍት ዙሪያ እንደሆነ ራሳቸው ከለቀቋቸው ቪዲዮዎችና ከሰጧቸው ቃለ መጠይቆች በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል ብሏል።

‹‹የትኛውም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል መብቱ የተጠበቀ ነው። ነገር ግን የሮንዳ በርንን፣ የቦብ ፕሮክተርን፣ የድፓክ ቾፕራንና የኤካርት ቶልን የአዲሱ ዘመን ሃይማኖት አስተምህሮን እያቀነቀኑ የክርስትና፣ የእስልምና ወይም የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ነኝ ማለት ፈፅሞ አይቻልም። እንዲያውም የአዲሱ ዘመን ሃይማኖት ዋናው ዕቅድ አብርሃማዊ እምነቶችን ማለትም የይሁዲ፣ የክርስትናንና የእስልምና እምነቶችን በሒደት ማክሰም ነው፡፡ ምክንያቱም በአዲሱ ዘመን ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች በአንድ አምላክ መኖር የሚያምኑ በመሆናቸው የ‹‹Low Vibration›› ባለቤት ናቸው ተብለው ይታመናሉ…›› ሲልም እውነታውን አፍርጥርጦታል። እንደ ጌታሁን (ኢንጂነር) ዓይነት የተባረከ ሰው አያሳጣን፡፡

እሱን ፈጣሪ ይባርከውና፣ ‹‹…በአንፃሩ የቡዲሂዝምና የሂንዱይዝም እምነት ተከታዮች ‹‹High Vibration›› እንዳላቸው ስለሚታመኑ፣ በአዲሱ ዘመን ሃይማኖት መምህራን ዘንድ የተለየ ክብር አላቸው። ምክንያቱም እነዚህ ሃይማኖቶች እንደ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች (Monotheistic Religions) የአንድ አምላክ መኖርን እንደ ቅድመ ሁኔታ አያስቀምጡም፡፡ እግዚአብሔርነት በፍጥረተ ዓለሙ ባሉ ፍጥረታት ውስጥ መኖር (Pantheism) ደግሞ የአዲሱ ዘመን ሃይማኖት ዋልታና ማገሩ ነው።  ለማንኛውም የአዲሱ ዘመን ሃይማኖት ራሱን የቻለ የሃይማኖት ዓይነት ነው፡፡ ለዚህም በመስኩ ጥናት ያደረጉ የሶሲዮሎጂና የአንትሮፖሎጂ ምሁራንን የጥናት ውጤት በዋቢነት በመጥቀስ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፤›› በማለት ‹‹አነቃቂ›› ተብዬዎቹን ሞግቷቸዋል።

ጌታሁን (ኢንጂነር) እዚህ ያሉትን በስም የጠቃቀሳቸውን ‹‹አነቃቂዎች›› ራሳቸውን የአዲሱ ዘመን ሃይማኖት ተከታይ መሆናቸውን ይፋ እያደረጉ የሚያምኑትን አስተምህሮ መከተልም ሆነ ማስተማር መብታቸው ነው ይላል። ነገር ግን የአዲሱ ዘመን ሃይማኖት አስተምህሮን በግልጽ እያሠራጩ ‹‹የክርስትና/የእስልምና እምነት ተከታይ ነኝ›› ማለት እውነታውን ከሕዝብ እንደ መደበቅ ይቆጠራል ሲልም ያክላል። ‹‹ባለንበት ዘመን እውነተኛ መረጃን ከሕዝብ መሰወር ለጊዜው ይሞከር ይሆናል እንጂ፣ ቆይቶም ቢሆን እውነቱ ወደ አደባባይ መውጣቱ የማይቀር ነው፤›› በማለት አጋልጧቸዋል። እኔም ለጊዜው ራሴን ካገለልኩበት ወጥቼ ይህንን ገጠመኝ ያጋራኋችሁ የጌታሁን ሔራሞ (ኢንጂነር) ጽሑፍ ለትውልዱ ተዳርሶ፣ ከአጉል ‹‹አነቃቂዎች›› የተሳሳተ መንገድ እንዲመልስ ትንሽ አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው፣ አመሠግናለሁ፡፡

(ቢልልኝ ማሩ፣ ከባልደራስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...