Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትእግር ኳሱን በቪዲዮ የሚተነትነው ባለሙያና ስኬቱ

እግር ኳሱን በቪዲዮ የሚተነትነው ባለሙያና ስኬቱ

ቀን:

ስለእግር ኳስ ታክቲካዊ እንቅስቃሴዎች ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ራሱን በንባብ እያዳበረ መሄዱን ይገልጻል፡፡ ከዚያም በሬዲዮ የቀጥታ ሥርጭት በሚተላለፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ እየቀረበ ትንተና መስጠት፣ በግል የፌስቡክ ገጹ የእግር ኳስ ትንተናዎች ማቅረቡን ተያያዘው፡፡ በሒደት የእግር ኳስ ታክቲካል እንቅስቃሴዎችን፣ ትንተናዎችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች እያቀረበና ልምድ እያዳበረ የመጣው አዲስ ወርቁ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በመቀላቀል የብቃት ተንታኝ ሆኖ ሥራውን ጀመረ፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ባልተለመደው በዚህ ሙያ የተሰማራው አዲስ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ የጎላ ሚና መጫወቱ ይወሳል፡፡ በሊጉ ባልተለመደ ዘመናዊ እግር ኳስ ሙያ የተሰማራውን አዲስ ወርቁን ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከምሕንድስና ሙያ ወደ እግር ኳስ እንዴት ልትገባ ቻልክ?

አቶ አዲስ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምሕንድስና ነው የተመረቅኩት፡፡ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ ለተወሰኑ ዓመታት በዘርፉ ተሰማርቼ ነበር፡፡ በአንፃሩ ከአራት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ አባቴ ጨዋታ ለመመልከት ወደ ስታዲየም ሲሄድ ይዞኝ ይገባ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእግር ኳስ ፍቅር በውስጤ ሊያድር ችሏል፡፡ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት ቢኖረኝም፣ ቤተሰቦቼ ግን በትምህርቱ እንድገፋ ፍላጎት ስለነበራቸው ትኩረቴን በትምህርቱ ላይ ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ በሒደት ግን የእግር ኳስ ፍቅሩ ሊለቀኝ ስላልቻለ የሬዲዮ ስፖርት ፕሮግራሞችን ማዳመጥ፣ ጋዜጦችን ማንበብ፣ በተለይ የኢትዮ ስፖርት ጋዜጠኛው መንሱር አብዱልቀኒ ያነሳሳኝ ነበር፡፡ ለእግር ኳስ በነበረኝ ፍቅር የበለጠ ወደ ሚዲያ መቅረብ ጀመርኩ፡፡ የእግር ኳስ ትንተና እየሰጠሁና የበለጠ ራሴን በንባብ እያዳበርኩ ስመጣ አንድ ውሳኔ መወሰን እንደሚገባኝ ተረዳሁ፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የቪዲዮ ታክቲክ ትንተና ሙያ እምብዛም ያልተለመደ ቢሆንም፣ ሙያውን በክለብ ደረጃ ለመጀመር ቅዱስ ጊዮርጊስን መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ቀጥታ ወደ አቶ ንዋይ በየነ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ አመራር ቦርድ ዋና ጸሐፊ ጋር ቀርቤ ከእግር ኳስ ቪዲዮ ትንተናና አፈጻጸም በተያያዘ መሥራት እንደምፈልግ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ጥያቄዬ ተቀባይነት አግኝቶ መሥራት ጀመርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም እግር ኳስን በቪዲዮ በመታገዝ መተንተን የዘመናዊ እግር ኳስ መገለጫ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ የተለመደ ባለመሆኑ ውጤታማ ልሆን እችላለሁ ብለህ አስበህ ነበር?

አቶ አዲስ፡- እውነቱን ለመናገር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ ለሦስት ዓመታት በክለቡ ለውጥ ማምጣት ችያለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም አጠቃላይ የእግር ኳሱ አካሄድ ፈታኝ ነበር፡፡ አንደኛ ሙያው አዲስ ነው፣ እኔ ለክለቡ አዲስ ነኝ፡፡ በጊዜው በነበሩት ፈተናዎች ምክንያት ክለቡን ለመልቀቅ የወሰንኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ተጫዋቾቹም የቪዲዮ ትንተና የመመልከት ብዙም ልምድ አልነበራቸውም፡፡ ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም ፈተና ነበሩ፡፡ ስለዚህ ወዲያው እንደገባሁ ውጤታማ መሆን ችያለሁ ማለት አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በቆይታህ በክለቡ እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ ማሳየት ችያለሁ ያልክበት አጋጣሚ መቼ ነው?

አቶ አዲስ፡- በክለቡ የመጀመርያዎቹን ሦስት ዓመታት ያሳለፍኩበት ፈታኝ ጊዜ በ2013 ዓ.ም. ክለቡን ለማሠልጠን የደቡብ አፍሪካው ማሂር ዴቪድስና ጀርመናዊው አሠልጣኝ ኤርነስት ሚዲንሮፕ በተረከቡበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በክለብ ውስጥ በነበረኝ ሚና ከቪዲዮ ተንታኝነት ባሻገር፣ ቡድኑ በሚጫወትበት መንገድ አኳያ፣ በጨዋታ ዝግጅት፣ በድኅረ ግጥሚያ ትንተና እንዲሁም በልምምድ ቦታዎች ላይ እንደ ምክትል አሠልጣኝ ሆኜ የአቅሜን አስተዋጽኦ ሳደርግ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር የትርጉም ሥራ እሠራ ነበር፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ከተሰናበተ በኃላ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ዋና አሰልጣኝ ሆነ። ከዋና አሰልጣኝ ዘሪሁን ጋርም በፍፁም መግባባት፣ መደማመጥ እና መረዳዳት ከላይ በጠቀስኩት ኃላፊነት ቀጥያለሁ። ቡድኑን አቅሜ በፈቀደ መልኩ ለማገዝ ሞክሬያለሁ። በዚሁም አሰልጣኝ ዘሪሁን ለፈጠረው መልካም የስራ ከባቢ በእጅጉ አመሰግናለሁ።

ሪፖርተር፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ባሻገር፣ በዛምቢያና ዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ስታገለግል ነበር፡፡ አጋጣሚውን ብታብራራልኝ?

አቶ አዲስ፡- አጋጣሚው በ2014 ዓ.ም. በመሀል የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ሰርቢያዊው ሚሉቲን ሶሬደጄቪች ሚቾ ሥራዬን ከተመለከተ በኋላ ግብዣ አቀረበልኝ፡፡ በዚህም እሱ የዑጋንዳና የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ሲያሠለጥን በቪዲዮ ትንተና ሥራ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጎን ለጎን የመሥራት ዕድል አግኝቼያለሁ፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ ልምድ ያገኘሁበት አጋጣሚ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከቪዲዮ ተንታኝነት በዘለለ የአሠልጣኝነት ሥልጠናህ እንዴት ይገለጻል?

አቶ አዲስ፡- የአሠልጣኝነት ትምህርት የመውሰድ ትልቅ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጠናውን ለማግኘት ለስምንት ዓመታት ያህል ተጓቶብኝ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት በግል ጥረቴ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የሚሰጠውን የአሠልጣኝነት የ‹‹ሲ›› ፈቃድ ባለፈው ዓመት ወስጄያለሁ፡፡ በቅርቡ የ‹‹ቢ›› የአሠልጣኝነት ፈቃድ እወስዳለሁ፡፡ ሥልጠናው በጣም ዘመናዊና የረቀቀ ነው፡፡ ሥልጠናው እግር ኳስን ከእግር ኳስ ባሻገር መረዳት በሚያስችል መልኩ መረዳት የሚያስችልና ልምድ ባላቸው ዕውቅ በሆኑ ባለሙያዎች የሚሰጥ ነው፡፡ ተማሪውም ሥልጠናውን በአግባቡ ሊወጣው ስለሚገባ በርካታ መወጣት የሚገባው ኃላፊነት አለበት፡፡ ከእነዚህ አጫጭር ሥልጠናዎች ባሻገር ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በግሌ ያነበብኳቸው መጻሕፍት፣ የተመለከትኳቸው ቃለ መጠይቆች፣ በድረ ገጽ የወሰድኳቸው ሥልጠናዎች የበለጠ ዕውቀቴን ጨምረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከመደበኛ የአሠልጣኝነት ሥልጠናዎች ባሻገር በግል ጥረት ያገኘሃቸውና ምሳሌ የሆኑህ አካላት አሉ?

አቶ አዲስ፡- በዋነኛነት እኔ ወደ አሠልጣኝነት እንዳዘነብል ምሳሌ የሆነኝ የሳልስቦርግ፣ ቦርቪያ ዶርቶሞንድ፣ ሞንቼግላድባ፣ እንዲሁም በቅርቡ የሊድስ ዩናይትድ ምክትል አሠልጣኝ የነበረው ሬኔ ማሪች ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ጓደኛዬ በመሆን ጭምር በጣም ረድቶኛል፡፡ ስለአጠቃላይ ሥልጠና እንዲሁም ብቃት ትንተና በጣም ብዙ ተምሬያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስና ሊጉ ያለህ አስተያየት ምንድነው?

አቶ አዲስ፡- ስለ ኢትየጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስተያየት ለመስጠት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ነገር ለይተን ካልተወያየንበት በስተቀር በጣም ውስብስብ ጉዳዮች የሚነሱበት ነው፡፡ በአንፃሩ ፕሪሚየር ሊጉ በዲስቲቪ መተላለፍ መቻሉ ብቻ እንደ በጎ መነሳት ይችላል፡፡ የሊጉ ጨዋታዎች በቀጥታ መተላለፍ መቻላቸው ለተጫዋቹም፣ ለአሠልጣኙም፣ እንዲሁም ለአገሪቱ እግር ኳስ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከዚያ በዘለለ የውድድሩ ፎርማት፣ የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ፣ የክለቦች ለሆቴል ከፍተኛ ወጪ ማውጣት፣ ክለቦች ጨዋታቸው በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጪ ማድረግ አለመቻላቸው፣ እንዲሁም ምቹ የሆኑ ሜዳዎች አለመኖራቸው እንደ ክፍተት የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅድህ ምንድነው?

አቶ አዲስ፡- በእርግጠኝነት ወደፊት ዋና አሠልጣኝ እሆናለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን በደንብ መማርና ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ዕውቀቴን ከኢትዮጵያ ከፍ ባሉ ሊጎች ላይ ለመፈጸም የበለጠ ዕውቀቴን ማዳበር እፈልጋለሁ፡፡ በዛምቢያና ዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች እንደነበረኝ የሥራ ዕድል በሌሎቹም የማስፋፋት ዕቅድ አለኝ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...