የጤና ተቋማት በአገርና ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት ባለመሥራታቸው፣ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞት እየጨመረ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አደረግኩት ባለው ክትትል ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡
ወደ ሕክምና ተቋማት የሚያቀኑ ሕሙማን በወቅቱ አገልግሎት እያገኙ ባለመሆኑ፣ የጤና ተቋማት በሽታን ከመከላከል ይልቅ ታመው ወደ ሕክምና የሚያቀኑ ሰዎች ላይ ብቻ አተኩረው በመሥራታቸው፣ አምንቡላንሶች ከታለመላቸው ዓላማ በተቃራኒ እየተሰማሩ በመሆኑ፣ በ2015 በጀት ዓመት የሕፃናትና የእናቶች ሞት ጭማሪ ማሳየቱን የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
አንድ ጤና ጣቢያ በመርህ ደረጃ ለ25 ሺሕ ዜጎች አገልግሎት መስጠት እንዳለበት በስታንዳርድ እንደተቀመጠ፣ ይሁን እንጂ እንደ ከዚህ በፊቱ በ2015 ዓ.ም. ይህ ድርጊት ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑ መረጋገጡንም አክለዋል፡፡
በጤና ጣቢያዎች፣ በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችና በሪፈራል ሆስፒታሎች ሲደረግ የነበረው የጤና ባለሙያዎች ምደባ፣ ክልሎች ‹‹በጀት የለንም›› በማለታቸው እየተመደበ እንዳልሆነ የገለጹት ዋና ዕንባ ጠባቂው፣ ‹‹ክልሎች እንዲያውም ሐኪሞችን ለመቀበል ሁሉ ፈቃደኛ አይደሉም፤›› ብለዋል፡፡
የሕፃናትን ጤና ከመጠበቅ አንፃር በወሊድ፣ በድኅረ ወሊድና የወሊድ አገልግሎት ከተቀመጡ አገርና ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶች አንፃር ተግባራዊ መደረጉን በተመለከተ፣ ተቋሙ አደረኩት ባለው ቁጥጥር የጨቅላ ሕፃናትና የእናቶች ሞት ቁጥር ከሌላው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ መጨመሩን፣ ተቋሙ በጤና አሰጣጥ ዙሪያ አደረኩት ያለው የ2015 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ይህ የሚሆነው የማኅበረሰቡ የመብቶች አከባባር በየተቋማቱ በሚገኙ ኃላፊዎች ይሁንታ ላይ ብቻ በመሠራቱ ነው ተብሏል፡፡
የእናቶችና የሕፃናት ሞት ቅነሳን በተመለከተ፣ በ2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የእናቶች የሞት ቁጥር ከ2014 ዓ.ም. ጋር ሲነጻጸር በአራት ብልጫ ማሳየቱን ሪፖርተር የተመለከተው የተቋሙ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በ2014 ዓ.ም. ከ100 ሺሕ እናቶች መካከል የ49 እናቶች ሞት እንደተመዘገበ፣ በ2015 በጀት ዓመት ከ89 ሺሕ እናቶች መካከል 53 እናቶች በዘጠኝ ወራት ወስጥ በወሊድና ተያያዥ ምክንያቶች ሞተዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ከአጎራባች አካባቢዎች በሪፈር የሚመጡ፣ ወቅቱን ጠብቀው ያልተላኩና ከተጎዱ በኋላ የሚመጡ እናቶች በከተማው በሚገኙ የጤና ተቋማት ውስጥ ሕክምና በማግኘት ላይ መሞታቸው፣ ለእናቶችና ሕፃናት ሞት መጨመር ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
የተከሰቱ ሞቶች በአብዛኛው የሚመዘገቡት በግል ሆስፒታሎች ከባለሙያዎች ብቃት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በተደረገ ውይይት ማወቅ መቻሉን፣ በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 73 የሚሆኑ ሕፃናት መሞታቸውን የሪፖርቱ የሞት ዳሰሳ ክፍል ያስረዳል፡፡
በመንግሥት የጤና ተቋማት ከተመዘገቡ ሞቶች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት አለርትና አበበች ጎበና ሆስፒታል መሆናቸውን፣ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ አለርት ሆስፒታል ከሰበታ፣ አበበች ጎበና ደግሞ ከሰንዳፋና ሱሉልታ በሪፈር የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ከፍ በማድረጋቸው መሆኑን የጤና ተቋማቱ ገልጸዋል ተብሏል፡፡
በጤና ተቋማት በቅድመና ድኅረ ወሊድ ወቅት ለሚገጥሙ ችግሮች በየደረጃው መፍትሔ ለመስጠት ሁለት ኮሚቴ መዋቀሩ፣ የእናቶች ሞት ምክንያት እስከ ቤት ድረስ ተወርዶ በኮሚቴ እየተጠና መሆኑን፣ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ከጤና ተቋማት ጋ ከአምቡላንሶች ጋር በተያያዘ ኮማንድ ፖስት ተዋቅሮ እንደሚሠራ፣ በቂ የአምቡላንስ አቅርቦት እንደሌለ ዕንባ ጠባቂ ጤና ተቋማቱ ነግረውኛል ብሏል፡፡
ዕንባ ጠባቂ ተቋሙ በሪፖርቱ የገለጸው፣ ‹‹ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ምንም እንኳ በሁሉም የመንግሥት ጤና ተቋማት ነፃ የመድኃኒት አቅርቦት እንዳለ ቢገለጽም፣ ባደረግነው ምልከታና ከተገልጋዮች ጋር ባደረግነው ውይይት አንዳንድ ጊዜ መድኃኒቶች ከጤና ተቋማቱ ውጪ በመውጣት በግላቸው እንዲገዙ የሚደረጉባቸው ጊዜዎች እንዳሉ የገለጹልን ሲሆን፣ የሥራ ኃላፊዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል፤›› ሲል ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የጤና ተቋማት በአንድ ጤና ጣቢያ ከስምንት እከከ አሥር አዋላጅ ባለሙያዎች ተመድበው እንደሚሠሩ፣ ከግብዓት አንፃር ከበፊቱ የተሻለ ለውጥ ቢኖርም ለእናቶችና ለሕፃናት የመድኃኒትና የክትባት እጥረት በተቋማቱ ማጋጠሙ ተመላክቷል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከሲዳማ ክልሎች የአምቡላንስ አገልግሎትን በተመለከተ ተመሳሳይ ክፍተት መኖሩ በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡