Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጭነት ትራንስፖርት ሰጪዎችና አስተላለፊዎች የጂቡቲ ቢሮክራሲ ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በጂቡቲ ወደብ የዕቃ አስተላላፊና ትራንስፖርት ሰጪ ተቋማት፣ በጂቡቲ የሚገጥማቸው ተደጋጋሚ የቢሮክራሲና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዲፈታላቸው ለመንግሥት ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማኅበር በዘርፉ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ላይ፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተካሂደዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት በርካታ የዘርፉ ተዋንያን ጂቡቲ በሚቆዩበት ወቅት እንግልት እየደረሰብን ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

ኮከብ አፍሪካ ትራንስፖርት ትሬዲንግ ከተሰኘ ድርጅት የተወከሉት አቶ ታደሰ ገብረ ዮሐንስ፣ ‹‹በጂቡቲ ወደብ በርካታ ችግሮች እገጠሙ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ አዲስ የወደብ አማራጭ የምታገኝበት መንገድ እንዲፈለግም ጠይቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ ካገኘች በኢትዮ ጂቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች እንደሚቀንሱና ለወጣቱም የተሻለ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ወደብ አልባ መሆናችን በጂቡቲ የቢሮክራሲ ችግሮች እየተስተዋሉ ስለሆነ፣ የሚቻል ከሆነ ለወደብ አልባነት መፍትሔ ያሻዋል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ በቀለ ማሞ የተባሉ የዕቃ አስተላላፊ ኩባንያ ወኪል በበኩላቸው በጂቡቲ የትራንሰፖርት ኮሪደር በሚታይ ጊዜያዊና ቋሚ ችግር፣ እንዲሁም ሆን ተብለው በሚፈጠሩ ግጭቶች የተነሳ በሥራ ላይ ማነቆዎች እየገጠሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያና የጂቡቲ መንግሥታት በጋራ የሚሠሩበት ስምምነት ቢኖርም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያሳየው ለዘብተኛ አቋምና ቁርጠኛ አለመሆን ምክንያት ኢትዮጵያውያን ወደ በጂቡቲ ለሥራ በሚሄዱበት ወቅት ተፅዕኖ እየተፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሁለቱ መንግሥታት ባደረጉት ስምምነት መሠረት የጂቡቲ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን የቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ ያመቻቻል ቢባልም፣ እስካሁን ይህ ባለመሆኑ ዕቃ አስተላላፊዎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እስከ 300 ሺሕ ብር ለቪዛና ለመኖሪያ ፈቃድ እየከፈሉ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም የኢትዮጵያ መንግሥት ተፅዕኖ ማድረግ ባለመቻሉና ውሉን ተመልሶ ባለማየቱ ነው ብለዋል፡፡

ከአምባሰል ንግድ ሥራዎች የተወከሉት ጽጌሬዳ ድርጀታቸው ዕቃ ወደ ውጭ በመላክና ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ በጂቡቲ ያለው የቢሮክራሲ ማነቆ ግን ትልቅ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከውጭ አገሮች የሚመጡ እንደ ትራክተር ያሉ ከባድ ማሽነሪዎች ከጂቡቲ ወደብ በቶሎ ስለማይወጡ፣ ሾፌሮች ገብተው ለመውጣት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮባቸዋል ብለዋል፡፡

ከውጭ የመጣ ዕቃ ጂቡቲ ከደረሰ በኋላ ዕቃው እየተቀሸበ መሆኑን በቪዲዮ እንደደረሳቸው የሚገልጹት ተወካይዋ፣ የውጭ ምንዛሪ ከፍለው ላመጡት ዕቃ በጂቡቲ ሚዛን ለመመዘኑ እምነት እንደሌላቸው ጠቅሰው፣ በአንድ ኮንቴነር ውስጥ ካለ ባለ 50 ኪሎ ከረጢት ቢያንስ በቁጥር እስከ ሃያ ከረጢት እየጎደለባቸው መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በጂቡቲ ሕጋዊ ናቸው የሚባሉ ነገር ግን ሕገወጥ ድርጊት ላይ የተሰማሩ አካላት ስለመኖራቸው ጠቁመዋል፡፡

ከትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን የመጡ ተሳታፊ አቶ መኮንን ወርቄ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በመታደልም ይሁን ባለመታደል ወደብ አልባ ሆናለች፡፡ ነገር ግን ባለወደብ የሆነችው ጂቡቲና ወደብ የሌላት ኢትዮጵያ ተባብረው እዚህ ደረጃ ቢደርሱም፣ ለኢትዮጵያ ዕቃ አስተላላፊና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በጂቡቲ የሚሰጠው አገልግሎት በልመና ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ስንገለገል ልንከበር አይገባም ወይ? የጋራ ወንድማማችነት ልናጠናክር አይገባም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ የሚሄዱ ሾፌሮችና ረዳቶች ጂቡቲ ውስጥ እንግልት እየደረሰባቸውም ቢሆንም ትኩረት አልተሰጠም፣ ብዙ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ስለሆነም የሚመለከተው የመንግሥት አካል ለጉዳዩ ትኩረት ይስጥ፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አማራጭ የሌለው ሰው የመጣውን ሁሉ የመቀበል ግዴታ ስላለበት በዚህ መቀጠሉ ትክክል ስላልሆነ ኢትዮጵያ አማራጭ መንገዶችን ልታስብ ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ በርካታ የትራንስፖርት ዘርፍ ተዋናዮች በተለይም ዕቃ አስተላላፊዎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጀቶችና ተወካዮች፣ የኢትዮ ጂቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር አርጅቶ በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳቱ ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ የትራንስፖርት ኮሪደር ሾፌሮች በሽፍታ በተተኮሰ ጥይቅ የመቁሰል፣ የመጎዳትና የሞት አደጋ እየደረሰባቸው የደኅንነት ሥጋት ላይ መውደቃቸው ተገልጿል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሎጂስቲክስ አገልግሎት አቅርቦት አስተባባሪ ምክር ቤት ሊቀመንበርና የፍሊንስቶን ሐውስ ባለቤት ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር)፣ በመደረኩ በነበረ የፓናል ውይይት ላይ ከተሳታፈዎች ለተነሱ ጥያቄዎች  ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በረሃ ላይ ሰውን ለመዝረፍ የሚቆም ሰው የደላው ሰው ነው ብሎ ማሰብ  ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ብዬ በድፍረት ብናገር ደስ ይለኛል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹መሣሪያ ይዞ በረሃ የሚቀመጥ ሰው የደላው ሰው አይደለም፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከሥርዓቱ የሚመነጭ ከሆነ ሥርዓቱን በኅብረት ማስተካከልና ሥራ አጥነት እንዲጠፋ በማድረግ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ በጋራ ብንሠራ ይስተካከላል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ፀደቀ (ኢንጂነር) አክለውም፣ ‹‹ከሰሞኑ የሚሰማውና መንግሥት በግድም ይሁን በውድ ወደብ ይኖረናል የሚለው ነገር ከቀጠለ፣ ካለፉት ጊዜያት ልምዳችን የቀጠለውን ችግር እስከ መጨረሻው ሊፈታ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሁን በጂቡቲ መንግሥት ላይ የሚሰማው ወቀሳ በጎ ነገር ይዞ ላይመጣ ስለሚችልና በትንሽ ነገር ከእነሱ ጋር ከምንጣላ ነገሩ በአጭሩ ቢስተካከል መልካም ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ በበኩላቸው፣ በኢትዮ ጂቡቲ ኮሪደር ላይ የሚታየውን የመሠረተ ልማት ችግርና ለመንገዱ የሚያስፈልጉ ግንባታ ለማከናወን ከዓለም ባንክ 730 ሚሊዮን ዶላር በመገኘቱ ችግሩ ይስተካከላል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የትራንስፖርት ኮሪደሩን የሚያስተዳድር የሁለቱ አገሮች የጋራ የማኔጅመንት ባለሥልጣን ተቋቁሞ የቴክኒክ ቡድን ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ፍቱን የሆነና ብዙ ችግሮችን ይቀርፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም መንግሥት መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን ጉዳዮች መጀማመሩን ጠቅሰው፣ ጉዳዩ በከፍተኛ ትኩረት እየሠራበት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ንግዱ ውስጥ 20 ቢሊዮን ዶላር ያህሉ በጂቡቲ ወደብ የምታስተላልፍ ሲሆን፣ ከጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ ከሌሎች የጎረቤት አገሮች ጋርም የወደብ ስምምነት ማድረጓ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች