Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን የሚደግፈው ‹‹ፋርም›› ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች የሚገኙ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ጨምሮ፣ ሌሎች የግብርና ግብዓቶች የሚያቀርበው ‹‹ፋርም›› ፕሮጀክት ይፋዊ ሥራ ጀመረ፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በኩል ለሚተገበረው የፋርም ፕሮጀክት፣ የተሻሻሉ የእህል፣ የዶሮ፣ የትንንሽ በግና ፍየል፣ የሆልቲካቸር ዝርያዎች፣ እንዲሁም ለመስኖ የሚያገለግሉ ፓምፖች ድጋፍ ለማድረግ የአውሮፓ ኅብረትና የፈረንሣይ ልማት ኤጀንሲ እንዲሁም የዴንማርክ መንግሥት በአጠቃላይ 31 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡

‹‹ፋርም›› የሚል ስያሜ የተሰጠውና ለአምስት ዓመታት የሚተገበረው ፕሮጀክት በጦርነት ውስጥ የቆዩትንና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከዚህ ቀደም ይታገዙ ከነበሩ 300 ወረዳዎች ጉዳት የደረሰባቸውን 84 ወረዳዎች መልሶ ለማቋቋም የተቀረፀ ፕሮጀክት መሆኑን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል በተደረገ የማስጀመርያ ሁነት ላይ ተናግረዋል፡፡

የተገኘውን የገንዘብ ድጋፍ መሠረት በማድረግ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ከፍል በሚገኙትና በግጭት ውስጥ በቆዩት ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ከላይ በተገለጹ ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ተፈላጊውን የግብርና ድጋፍ በማቅረብ እንደገና እንዲያመርቱ፣ ከዚህ ቀደም በገጠማቸው ከፍተኛ ቀውስ ምክንያት የተቋረጠውን የአገልግሎት መሠረተ ልማት ለማሻሻል የሚረዱ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ተጠቅሷል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተደረገው ጦርነት ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የግብርና ዘርፉ መሆኑ፣ በተለይም በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል በርካታ የእርሻ መሬቶች ያለ ምርት እንዲከርሙ፣ የተዘራውም የሚሰበስበው ባለመኖሩ ረግፎ መቅረቱ ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል፡፡

ለአብነትም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ድንበር ዘለል ከሚባሉ 11 ዓይነት በሽታዎች አሥር የሚሆኑት በትግራይ ክልል በመከሰታቸው ምክንያት ከ70 እስከ 80 ሺሕ የሚጠጉ እንስሳት ለሞት መዳረጋቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ከደነው ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት የአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት በዘጠኝ ዞኖች በርካታ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ክልሉ በጥናት ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለ ማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ በጦርነቱ ሳቢያ የግብርናው ዘርፍ 92 በሊዮን ብር የሚደርስ ኪሳራ አስተናግዷል፡፡

በሌላ በኩል ሌላው ጦርነት ውስጥ የነበረው የአፋር ክልል 1.3 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በጦርነቱ ጉዳት እንደደረሰበት፣ እንዲሁም ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንስሳት መታጣቱን፣ 8.6 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የሰብልና እንስሳት ዘርፍ ኪሳራ የአፋር ክልል እንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች