Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም የመሠረተ ልማት ዝርጋታን በሚመለከት ተቋማትና ግለሰቦች አልተረዱኝም አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊው ግዙፉ የቴሌኮም ተቋም የሆነው የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎች፣ በተደጋጋሚ የሚነሱበትን የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጥያቄዎች በሚመለከት፣ ኃላፊነቴን እየተወጣሁና የቤት ሥራዬን እየሠራሁ ቢሆንም ተቋማትና ግለሰቦች ሳይረዱኝ ቀርተዋል አሉ፡፡

የተቋማቸውን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል በገለጹበት ወቅት የመሠረተ ልማት ግንባታን በሚመለከት ተጠይቀው ማብራሪያ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ቀድሞውንም ተቋማቸው የቤት ሥራውን በብዙ እጥፍ መሥራቱን አብራርተዋል፡፡

በገጠራማ የአገሪቱ ክፍሎች የንግድ ትርፋማነት በሌለበት የማስፋፊያ ሥራ ከከተማ በበለጠ በራሱ ወጪ እያከናወነ እንደሆነ፣ እንዲሁም ተቋሙ ካሉት 9,078 የሞባይል ጣቢያዎች ከግማሸ በላይ (52 በመቶ) የሚሆነውን በገጠራማ አካባቢዎች እንደሆነ ነው ኃላፊዋ የገለጹት፡፡

‹‹ይሄ ሁሉ ግልጽ ሆኖ ባለመረዳት ይሁን በሌላ፣ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ይሄንን ማጣመም ትክክል አይደለም፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ እንደ መንግሥት የልማት ድርጅት ‹‹ሊጨበጨብለት የሚገባው ጉዳይ ነው›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጨምሮ በተለያዩ ኩነቶች ተቋሙ የመሠረተ ልማት ጥያቄ ሲነሳበት የቆየ ሲሆን፣ የ99 በመቶ የሕዝብ ተደራሽነትንና ከግማሽ በላይ የሞባይል ጣቢያዎችን በገጠራማ ቦታ ተገንብቶ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን ማንሳት ‹‹ንፉግነት ነው›› ሲሉ ኃላፊዋ አክለዋል፡፡ ‹‹ጥቂት የቀሩ ቀበሌዎችን እያነሳን የተሠራውን መዘንጋት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተቋሙ በራሱ ወጪ ካለተጨማሪ በጀት ሲያድስ እንደቆየና በዚህም ኃላፊነቱን እየተወጣ በመሆኑ የሠራውን ሥራ ማሳነስ ‹‹ቅንነት የጎደለው›› እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በቀጣይም በዩኒቨርሳል አክሰስ መሠረት ከተወዳዳሪ ተቋማት ጋር በንግድ አዋጭ የሆኑ ቦታዎች ብቻም ሳይሆን በሌሎችም ቦታዎች ከገቢያቸው እያዋጡ ማስፋፊያ እንደሚደረግ ነው ሥራ አስፈጻሚዋ የገለጹት፡፡ ‹‹ኢትዮ ቴሌኮም አሁንም አልሠራም፣ ድርሻዬ አይደለም አላለም፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡  

ተጨማሪ መሠረተ ልማትን በመገንባት በኩል ተቋሙ 998 የሞባይል ጣቢያዎችን በተያዘው በጀት ዓመት ለመገንባት ያቀደ ሲሆን፣ ከእነዚህም 140 የሚሆኑት በገጠራማ አካባቢዎች እንደሚሆን ይፋ ባደረገው ዕቅድ ገልጿል፡፡

ዘርፉ ለሌሎችም ተፎካካሪ የቴሌኮም ተቋማት የተከፈተ በመሆኑ ሥራ የጀመረውን ሳፋሪኮም ጨምሮ በተያዘው በጀት ዓመት ሁለት ተፎካካሪዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ በማሰብ ተቋሙ የዓመት ዕቅዱን እንዳወጣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተው ነበር፡፡

ለተፎካካሪዎችም የመሠረተ ልማቶችን በማጋራት የውጭ ምንዛሪ ከሚያገኝባቸው ምንጮች ይሄን ዘርፍ አንደኛው እንዳደረጉትም ነው የገለጹት፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ ካስመዘገበው የ75.8 ቢሊዮን ብር ገቢ አንድ በመቶው ከመሠረተ ልማት ኪራይ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ተገልጾ ነበር፡፡

የተጀመረው በጀት ዓመት ሲጠናቀቅ የደንበኛውን ቁጥር አሁን ካለበት 72 ሚሊዮን ወደ 78 ሚሊዮን ለማድረስ፣ ገቢውንም የተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ካስመዘገበው 75.8 ቢሊዮን ብር ወደ 90.5 ቢሊዮን ለማድረስ አቅዷል፡፡

የቴሌ ብር ተጠቃሚዎቹንም አሁን ካለበት 34.3 ሚሊዮን ወደ 44.1 ሚሊዮን ለማድረስ ያቀደ ሲሆን፣ በቴሌ ብር የሚጠቀሙትን ነጋዴዎች 50 በመቶ በማሳደግ 88 ሺሕ አድርሶ ወኪሎቹን ደግሞ 124 ሺሕ ለማድረስ አቅዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች