‹‹ደራሲ መሆን ሦስት ችግሮች አሉት፡፡ ለኅትመት የሚመጥን ጽሑፍ መጻፍ፣ የሚያሳትሙ ቅን ሰዎችን መፈለግ፣ የሚያነቡትን አስተዋይ ሰዎች ማግኘት›› ይላል መግቢያው ላይ ያለው ጽሑፍ፡፡
መጽሐፉ በዘጠኝ ምዕራፎችና በ653 ገፆች የተሰነደ ሲሆን ወታደራዊ ደንቦችን፣ የማይረሱ ትዝታዎችና የጦር ሜዳ ውሎ አዳሮችን፣ የጸሐፊውን ከልጅነት እስከ ወጣትነት አሁን እስካሉበት፣ ከንጉሡ ዘመን እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የነበሩትን ውጣ ውረዶች ይዳስሳል፡፡
‹‹የኔ መንገድ›› በሚል ርዕስ የቀረበው መጽሐፍ ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ተመርቆ ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡ መጽሐፍ ምንም እንኳን ግለ ታሪክ (ኦቶ ባዮግራፊ) ቢሆንም የብዙ የአገር ባለውለታዎችን የጦር ሜዳ ጀግኖችንና ለአገራቸው እስከ መስዋዕትነት ድረስ የከፈሉ ጀግኖችን፣ የተረሱና በሠሩት ሥራ ልክ ዋጋ ያልተከፈላቸው ባለውለታዎችን የሚያወሳ እንደሆነ የመጽሐፉ ደራሲ ኮሎኔል ፈቃደ ገብረየስ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል፡፡
በመጽሐፉ ከተጠቀሱ አርበኞች መካከል ኮሎኔል ኃይሌ ተስፋ ሚካኤል ይገኙበታል፡፡
‹‹በአመራር ብቃታቸው ምርጥና ኮስታራ፣ ሲበዛ ደፋርና ተናጋሪ በማዕረግ አቻዎቻቸውና ለበላይ አለቆቻቸው ሳይቀር ጠንከር ያለ የኃይለኛነት የድፍረትና የእልኸኝነት ባህሪ ያሳያሉ ከሚባሉ መኮንኖች መካከል፣ ልበ ሙሉውና ያልተዘመረላቸው ቆፍጣናው የጦር ሰው ኮሎኔል ኃይሌ ተስፋ ሚካኤል አንዱ ናቸው፤›› በማለት በመጽሐፉ በገጽ 177 ታሪካቸው ተገልጿል፡፡
በመጽሐፍ አዟሪነት የልጅነት ጊዜያቸውን እንዳሳለፉ በግል የሕይወት ታሪካቸው ላይ ያሰፈሩት ኮሎኔል ፈቃደ፣ በወቅቱ ‹‹አባባ ጃንሆይን መንገድ ላይ አግኝቼ መጽሐፍ ሸጥኩላቸው፤›› ሲሉ አጋጣሚውን በመገረም አስፍረውታል፡፡
‹‹የአጋጣሚ ነገር መቼም ይገርማል፣ ጊዜው 1962 ዓ.ም. ገደማ ነበር፣ እንደ አሁኑ ዘመን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ ምክንያት እያንዳንዱ ሰው አይደለም ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ዓለምን በጣቱ ላይ አስቀምጦ በፈለገው ቦታ የፈለገውን መረጃ ማግኘት መቻሉ ከዚያ ዘመን ጋር መቼም ማወዳደር አይገባም፤›› በማለት የጻፉት ኮሎኔል ፈቃደ፣ በወቅቱ ሜክሲኮ አካባቢ ከአንድ መጽሐፍ አዟሪ ጓደኛቸው ጋር በመሆን አርፈው ዜና በሚሰሙበት ወቅት ‹‹ድንገት ዞር ስል በቴሌቪዥን መስኮትና በየጋዜጣ ላይ ብቻ እመለከታቸው የነበሩት ባለግርማ ሞገሱና አስፈሪውን ንጉሥ አባባ ጃንሆይን፣ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ‹ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሥ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሞዓ አንበሳ ዘእምነገድ ይሁዳ ሥዩመ እግዝአብሔር› የትራፊክ መብራት አስቁሟቸው ተመለከትኩ፡፡
‹‹ዕውን አልመስልህም አለኝ፣ ዓይኔን ማመን አልቻልኩም ፈራ ተባ እያልኩ ልጠጋቸው ዳዳኝ፣ በዚህ ላይ እርሳቸውም ደግሞ ከነ ግርማ ሞገሳቸው በጣም ያስፈራሉ… ፈጠን ፈጠን በማለትም ወደ መኪናቸው በመጠጋት ተመለከትኳቸው… መብራቱ ለቋቸው ሾፌሩ ሊንቀሳቀስ ሲል ቆይ፡፡ አትሂድ!! አሉት፡፡ …እኔም ፈጠን ብዬ አንገቴን ዝቅ በማድረግ ሰላምታ ከሰጠኋቸው በኋላ እግዚአብሔርን ያገኘሁ ያህል ድንጋጤም በተቀላቀለበት መንፈስ ጃንሆይ!! መጽሐፍ ይግዙኝ አልኳቸው፣ እርሳቸውም የመኪናውን መስኮት ዝቅ አድርገው በሚያናግሩኝ ቅፅበት የንጉሠ ነገሥቱ የትራፊክ ፖሊስ ዋና መሪ ሞተረኛው ሻምበል በቀለ ደመሣ በቅፅል ስሙ ‹በቀለ ጢሞ› ድንገት ደርሶ ‹ዞር በል ከዚህ› ጠላታችሁ ክው ይበል ክው ብዬ ቀረሁ፡፡ …ዞር በል ከዚህ ብሎ አንገቴን ጨብጦ ሊወረውረኝ ሲል ‹ተወው!! በቀለ› ካሉት በኋላ ምንድነው የምትሠሩት አሉ፡፡ መጽሐፍ ነው የምንነግደው ጃንሆይ አልኳቸው፡፡
ፈጠን ብዬ ለእርሳቸው ይመጥናል ያልኩትን በወቅቱ ታዋቂነትንና ተወዳጅነትን አትርፎ በአማርኛ ታትሞ የነበረውን የጆን ኤፍ ኬኔዲን መጽሐፍ ሰጠኋቸው፡፡ ጃንሆይም ‹ምርጫህ ትክክል ነው ለማን ምን መስጠት እንዳለብህ በሚገባ ታውቃለህ› ዋጋው ስንት ነው? አሉኝ፡፡ የመጽሐፉ ምን ቢበዛ ከአንድ ብር አይበልጥም ስፈራ ስቸር አራት ብር አልኳቸው፣ እርሳቸው ግን ከጎናቸው ካስቀመጡት አዳዲስ ብሮች አሥር ብር ዘገኑና በመስጠት በርታ አሉኝ›› በማለት ከንጉሡ ጋር የተገናኙበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡
ከንጉሡ ባሻገር ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር የነበራቸውን ገጠመኝ፣ እንዲሁም ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና አሁን ላይ ባሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፕሮጀክት ደብዳቤ መላካቸውንና ምላሽ ሳይሰጣቸው እንደቀረ በዝርዝር ጠቅሰዋል፡፡
መጽሐፉ በተለያየ ጊዜና ቦታ የተነሱ ፎቶዎችንና አባሪዎች ተብለው በተሰየሙ ስምንት ዓበይት ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን በጠቅላላው 68 ምዕራፎችና በርካታ ንዑሳን ርዕሶችን አካቷል፡፡
‹‹ስንጥር እየፈለግን እነ አፄ ምኒልክ፣ እነ አፄ ኃይለ ሥላሴን፣ እነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምንና አቶ መለስ ዜናዊን ጥለን ማንን እናነሳለን፣ በእያንዳንዳቸው ክፍተት አለ›› ያሉት ኮሎኔል ፈቃደ፣ ‹‹እኔ ሙሉ ነኝ የሚል ሰው ካለ እርሱ የባሰ ጎዶሎ ነው ሙሉ ሰው በዓለም የለም ሲሉ ተናግረው፣ የአንዱ ጎዶሎ አንዱ እየሞላ ነው የሚሄደው ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹ከዚህም አንፃር የአገራችንን ሰዎች ታሪክ ጽፌያለሁ›› ያሉት ኮሎኔሉ፣ ‹‹ሁሉን ጎጥ እየፈጠርን ከጣልን መጨረሻ ምንም አይኖረንም፣ ይህ ካልሆነ ሾተላይ ኢትዮጵያ ትሆናለች ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
መጽሐፉ በበርካታ መረጃዎች የበለፀገ ነው ያሉት ደግሞ በአርትኦት ሥራው የተሳተፉት አቶ ባዩልኝ አያሌው ናቸው፡፡
መጽሐፉ በመረጃዎች ስለመበልፀጉ ‹‹በእኔ ግምት›› ብለው አራት ምክንያቶችን አስቀምጠዋል፡፡
የመጀመርያው ደራሲው በሦስት መንግሥታት ያገለገለ በመሆኑ ሲሆን፣ በሁለተኛ ኮሎኔል ፈቃደ ንቁ ተሳታፊ በመሆኑ እያንዳንዳቸውን መሪጃዎች መዝግቦ የማስቀመጥና የማስታወስ ችሎታ ስላለው ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በየዘመናቱ ከትልልቅ የጦር አለቆችና ግለሰቦች ጋር በመሥራቱ ቁልፍ ሚና ካላቸው ትልልቅ ጄኔራሎችና አመራሮች ጋር አብሮ የመሥራት ዕድሉን በማግኘቱና ኮሎኔል ፈቃደ በወጣትነቱ ጀምሮ ለመጻፍ ያላቸው ዝንባሌ መጽሐፉን የተሟላ ለማድረግ ረድተውታል ሲሉ አቶ ባዩልኝ ተናግረዋል፡፡
የመጽሐፉ የአተራረክ (የአቀራረብ) ስልት ከኢልቦለድ መጽሐፍ የሚመደብ ነው፡፡ አቀራረቡም መደበኛ የሆነ የአተራረክ መንገድን ነው የሚጠቀመው ሲሉ ምልከታቸውን አስቀምጠዋል፡፡