- በኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው)
ዲግሪማ ነበረን — በዓይነት በብዛት
ከቶ አልቻልንም — እንጂ ቁንጫን ለማጥፋት!!
ዲግሪማ ነበረን — ከእያንዳንዱ ምሁር
አላጠፋም እንጂ — ቅማልን ከሀገር!!
ዲግሪ ተሸክሞ — መሥራት ካልተቻለ
አህያስ በአቅሟ — ጨርቅ ትጭን የለ!!
ዲግሪማ ነበረን — ለወሬ የሚበጅ
ሙጀሌን ከሀገር — አልነቀለም እንጂ!!
ዲግሪማ ነበረን — በሊቃውንት ተርታ
አላዳነም እንጂ — ከገዳይ በሽታ!!
ዲግሪማ ነበረን — ያገኘነው ዓምና
አልረዳንም እንጂ — ሲያሸንፍ ድንቁርና!!
አይተኙበት እንጂ — ዲግሪማ ነበረን
አልመከተም እንጂ — ድህነት ሲያጉላላን!!
ጥሮ ተጣጥሮ — ዲግሪማ ለማግኘት
ለመሆን አልነበር — ለሰው መድኃኒት?
ተምሮ ተምሮ — ማፍራት ያን ዲግሪማ
ላለማስ ነበር — በጭቆና ዶማ!!
ዲግሪ የምንለው — የሠራልን ቢኖር
በእኔነት ራስ ላይ — ምቾትን ማሳደር
የውስጥ ድንቁርናን — በውጭ ለመሞሸር!
- ገሞራው ‹‹በረከተ መርገም››