የ2015 ዓ.ም. የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ፈረሰኞቹ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የዛንዚባሩን ኬኤምኬኤም እግር ኳስ ክለብን ይገጥማል፡፡
በግብፅ ካይሮ ሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ በሆነው ድልድል መሠረት፣ ፈረሰኞቹ የመጀመርያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከሜዳቸው ውጪ የሚያከናውኑ ይሆናል፡፡
በዚህም መሠረት ፈረሰኞቹ የመጀመርያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከነሐሴ 12 እስከ 14 ቀን የሚያከናውኑ ሲሆን፣ የደርሶ መልስ ጨዋታው ከነሐሴ 19 እስከ 21 ቀን ባሉት ቀናት ውስጥ እንደሚያከናውኑ ተገልጿል፡፡
የሁለተኛው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከመስከረም 4 እስከ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚካሄድ የወጣው ድልድል ያሳያል፡፡
በሁለተኛ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር የሚያሸንፉ ክለቦች በቀጥታ በከፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ድልድል ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ለማድረግ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ 52 ቡድኖች የተካተቱ ሲሆን፣ ከፍተኛ የተሳትፎ ደረጃ ያላቸው 10 ክለቦች ከቅድመ ማጣሪያ የጨዋታ ድልድል ውጪ ተደርገዋል፡፡
ፈረሰኞቹ በካፍ በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን የተጫዋቻቸውን ውል እያደሱና አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረሙ ይገኛሉ፡፡