Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየከተማ አስተዳደሩና ሪል ስቴት አልሚዎች ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ወጪ መኖሪያ ቤቶችን...

የከተማ አስተዳደሩና ሪል ስቴት አልሚዎች ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ወጪ መኖሪያ ቤቶችን ሊገነቡ ነው

ቀን:

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ በቀረበው የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት አማካይነት የመረጣቸው ሪል ስቴት አልሚዎች፣ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ወጪ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሊጀምሩ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ በቀረፀው 70/30 የተሰኘ የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮግራም ሥር እንዲሳተፉ 68 ሪል ስቴት አልሚዎችን የመረጠ ሲሆን፣ አልሚዎቹም በተቀመጠው 70/30 አጋርነት መሠረት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተጣምረው ግንባታውን ለማካሄድ ውል ገብተዋል። 

ቤቶቹን ለመገንባት የተመረጡት 68 የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ኦቪድ ግሩፕ፣ ፍሊንትስቶን ሆምስ፣ እንይ ኮንስትራክሽን፣ ጊፍት ሪል ስቴትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

በከተማ አስተዳደሩና በሪል ስቴት አልሚዎቹ መካከል የተፈጸመው ውል የሁለቱን የኃላፊነት ድርሻ የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የከተማ አስተዳደሩ የቤቶቹን ግንባታ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን መሬት ከሊዝ ነፃ ማቅረብና መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ይጠበቅበታል። አልሚዎቹ ደግሞ ያስገቡትን የመገንባት አቅም መሠረት ተደርጎ በሚቀርብላቸው መሬት ላይ ወጪውን በመሸፈን የቤቶችን ግንባታ አካሂደው ካጠናቀቁ በኋላ፣ 30 በመቶውን ለከተማ አስተዳደሩ ለማስረከብ መስማማታቸው ታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ በ2016 በጀት ዓመት 100ሺ ቤቶችን በዚህ መንገድ ለማስገባት ማቀዱን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል። በ2016 ዓ.ም. ለመገንባት ከታቀዱ መቶ ሺሕ ቤቶች ውስጥ የሪል ስቴት አልሚና በአልሙኒየም ፍሬምወርክ የግንባታ ሥልት የሚታወቀው አቪድ ግሩፕ ተቋራጭ 60 ሺሕ ቤቶችን ገንብቶ ለማቅረብ ውል መግባቱ ታውቋል።

ሌላኛው ታዋቂ ሪል ስቴት አልሚ ጊፍት ሪል ስቴት ደግሞ 12 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት ተስማምቶ የዝግጅት ሥራዎችን ጀምሯል። ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ደግሞ 10 ሺሕ ቤቶችን ለመግንባት ውል መግባቱን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የከተማ አስተዳደሩን ትልቅ ፕሮጀክት የያዘው ኦቪድ ግሩፕ ለጠቅላላ ፕሮጀክቱ 450 ቢሊዮን ብር ወጪ የመደበ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ለመግባት በሒደት ላይ መሆኑን ከድርጅቱ ኃላፊዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡

ድርጅቱ ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚሆነውን ገንዘብ ከተለያዩ ምንጮች ለማሰባሰብ ማቀዱን የገለጹት የሥራ ኃላፊዎቹ፣ ከድርጅቱ ምንጭ በተጨማሪ ከውጭ ብድር፣ ከአገር ውስጥ ብድርና ከአጋሮቹ የሚያስፈልገውን ወጪ እንደሚያሰባስብ አስረድተዋል።

አክለውም ኦቪድ ግሩፕ በዚሁ የቤት ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ለመቆየት ያቀደ በመሆኑ፣ ኦቪድ ቤቶች የተሰኘ የቤት ልማት ባንክ (ሞርጌጅ ባንክ) እያቋቋመ መሆኑንና ይህም በቀጣይ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆን አክለዋል።

ኦቪድ ግሩፕ ሥራውን ለማቀላጠፍ የጀርመን ኩባንያ ከሆነው ክሊንግ ከተባለ 65 ዓመት ዕድሜ ካለው ድርጅት ጋር በመጣመር፣ ኦቪድ-ክሊንግ አማካሪ የተባለ የሽርክና ድርጅት አቋቁሞ እየሠራ መሆኑንም የሥራ ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ በመንግሥትና በግል አጋርነት ለሚካሄደው የቤት ግንባታ ፕሮጀክት፣ በመሀል አዲስ አበባ 350 ሔክታር መሬት ማዘጋጀቱም ታውቋል።

ለኩባንያዎቹ መሬቱ ከሊዝ ክፍያ ነፃ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ከሚገነቧቸው ቤቶች 70 በመቶውን ለግላቸው ወስደው 30 በመቶውን ለመንግሥት ያስረክባሉ፡፡ ይህ ማለት የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ጥምረት ከሚገነቡት ቤቶች ውስጥ 30 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል።

የኦቪድ ግሩፕ ሥራ ኃላፊዎች ከሚገነቡት ቤቶች ውስጥ ኦቪድ 70 በመቶ ድርሻውን ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ ኢቪድ ግሩፕ ለሚገነባቸው ቤቶች በቦሌ ክፍተ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ 460 ሔክታር መሬት ከከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ እንደሚቀበልና ወደ ግንባታ እንደሚገባ ታውቋል። 

ለቤቶቹ ግንባታ የተለዩ ሦስት አካባቢዎች የተመደቡ ሲሆን እነሱም በከተማ ውስጥ፣ በከተማ አቅራቢያና ከከተማ ወጣ ያሉ ናቸው፡፡

ጊፍት ሪል ስቴት ትልቅ የተባለውን ፕሮጀክት የያዘው ሁለተኛው አልሚ ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ጊፍት ሪል ስቴት የሚገነባቸው ቤቶች 12 ሺሕ መሆናቸውንና ከተማ ውስጥ የሚለው መደብ እንደደረሰው አረጋግጧል። ይሁን አንጂ ጊፍት የግንባታውን አጠቃላይ ወጪና ለግንባታው ከሊዝ ነፃ የተሰጠውን የቦታ መጠን ከመናገር ተቆጥቧል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የሚገኘው ሪል ስቴት አልሚ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሲሆን፣ ኩባንያው 10 ሺሕ ቤቶችን ገንብቶ ለማስረከብ በገባው ውል መሠረት በዋናነት የራሱ ይዞታ የሆነውን በተለምዶ መቻሬ ሜዳ በመባል የሚታወቀውን ይዞታ ጥቅም ላይ እንደሚያውል፣ የቀረውን ደግሞ በሌሎች አካባቢዎች የከተማ አስተዳደሩ በሚያቀርብለት መሬት ላይ እንደሚያከናውን የድርጅቱ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፍሊንትስቶን ሆምስና የእንይ ኮንስትራክሽን ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ከተማ አስተዳደሩ እንዲገነቡ የሰጣቸው የቤት ብዛት ከ3,000 እንደማይበልጥና ለዚህም ግንባታ የሚሆን መሬት እስካሁን እንዳልተረከቡ ገልጸዋል፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በተለያዩ ጊዜያት በመገናኘት ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ፋይናንስ ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በአልሚው ድርጅት ሲሆን የግብዓት አቅርቦት፣ የመብራትና የውኃ፣ እንዲሁም ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት ሲፈጠር አልሚ ድርጅቶቹ ቅድሚያ እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሩ መሆኑም ታውቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...