ግለሰቦች ከእሱ ዕውቅና ውጪ በስሙ የንግዱን ማኅበረሰብ እያታለሉ እንደሆነ ጥቆማ እንደደረሰው የገለጸው የፋይናነስ ደኅንነት አገልግሎት፣ በድርጊቱ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን አስጠነቀቀ፡፡
በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ለግል ጥቅማቸው ሲሉ፣ ‹‹እከሌን አውቀዋለሁ›› እያሉ በማስፈራራት ገንዘብ እንደሚቀበሉና እንደሚያታልሉ ነው የተቋሙ ኃላፊዎች ለሪፖርተር የገለጹት፡፡
አገልግሎቱ ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው የማስጠንቀቂያ መግለጫ፣ ‹‹ግለሰቦች ሐሰተኛ የማደናገሪያና የማስፈራሪያ ሥልቶችን በመጠቀም በተለይም የንግዱን ማኅበረሰብ በማሸበር››፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የግል ጥቅማቸውን የማስጠበቅ ዝንባሌ እያሳዩ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
አገልግሎቱ በማስጠንቀቂያው አክሎም፣ ሐሰተኛ በማዘጋጀት የወንጀል ድርጊት እየፈጸሙ ነው ባላቸው በንግድ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ድርጀቶችን በማጥመድ፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ‹‹የገንዘብ እንቅስቃሴያቸው ላይ ዕግድ ሊጥል እንደሆነ›› የወንጀል ድርጊት እየፈጸሙ መሆኑን ገልጿል፡፡
ስለጉዳዩ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የአገልግሎቱ ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳለ አሰፋ፣ ግለሰቦች የወንጀል ተጠቂዎችን በመቅረብ ‹‹የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሒሳባችሁን ሊያግድ እንደሆነ መረጃ ደርሶናል፤›› እያሉ በማወናበድ ገንዘብ የመቀበል አዝማሚያ እያሳዩ ነው ብለዋል፡፡
‹‹እከሌን አውቀዋለሁ›› በማለት ከተቋሙ ጋር አያይዘው የማስፈራራትና የማጭበርበር ድርጊት እየፈጸሙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሰፊ ሳይሆን በዝንባሌ ደረጃ ነው እየታየ ያለው፤›› ሲሉ ድርጊቱ በስፋት እየተፈጸመ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተቋሙ የማይሠሩና ማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ራሳቸውን በዚህ መንገድ ለመጥቀም በመፈለግ፣ ነጋዴው ተረጋግቶ ሥራውን እንዳይሠራ እንደሚያውኩት አቶ እንዳለ ገልጸዋል፡፡
ተቋማቸው ጥቆማዎችን እየተቀበለ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲወሰድና በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትም እንዲታቀቡ በማሰብ መግለጫው መውጣቱን ተናግረዋል፡፡
ተቋማቸው በዋነኝነት ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ጠንካራ ክትትል በማድረግ የደረሰበትን ውጤት ለሕግ አስከባሪ ተቋማት መስጠት ዋነኛ ተግባሩ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ ግለሰቦቹ የተሰማሩበት ድርጊት የአገልግሎቱ ‹‹ሥራም፣ ተልዕኮም አይደለም›› ብለዋል፡፡
አገልግሎቱ አውጥቶት በነበረው የማስጠንቀቂያ መግለጫ ላይ እንዳሰፈረው፣ ‹‹ዕግድን በሚመለከት የተሰጠው ሥልጣን ውስን›› እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም ዕግድ እንደ ብቸኛ ተልዕኮው ሆኖ ሊወሰድ እንደማይገባና ‹‹አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ሥራ ላይ የሚውል›› መሆኑን በግልጽ አስታውቋል፡፡