Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ዘረኝነትንና ጥላቻን ከሰበኩት የፊንላንድ ሚኒስትሮች የሚማሩት

ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ዘረኝነትንና ጥላቻን ከሰበኩት የፊንላንድ ሚኒስትሮች የሚማሩት

ቀን:

በኢትዮጵያ በተለይም በፖለቲከኞች ለዓመታት ሲሰበክ የከረመው የጥላቻና የብሔርተኝነት ንግግር ሕዝቦቿን ለግጭትና ለጦርነት ዳርጓል፡፡ ከዚህም ከዚያም ብቅ እያሉ የሚከስሙ አልያም አላባሩ ያሉ ግጭቶች ከመነሻቸው አንዱ ከጥላቻ ንግግርና ትርክት የመነጨ መገፋፋት ነው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የጥላቻ ንግግርም ሆነ አንዱን ብሔር ከአንዱ ብሔር አበላልጦ መናገር፣ አንዱን አወድሶ አንዱን ማኮሰስ፣ አንዱን አጀግኖ አንዱን ማልፈስፈስ፣ አንዱን ባለ ዕውቀት ሌላውን መሃይማን፣ አንዱን የሚችል ሌላው የማይችልና በርካታ ሌሎችም የሕዝብን አብነሮነት የሚሸረሸሩ የጥላቻ ንግግሮች ከአንዳንድ ፖለቲከኞች ይነገራሉ፡፡

ይህ ግን በሠለጠኑ ሕዝቦችና አገሮች ከሥልጣን የሚያስለቅቅ ወይም በአደባባይ ይቅርታ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ከሰሞኑ በፊንላንድ ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ የተከሰተውም ይኸው ነው፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት በማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተጻፈና ከአራት ዓመታት በፊት በአፍሪካውያን ላይ የተሰነዘረ የጥላቻና ዘረኝነት ንግግር የፊንላንድን ፖለቲካ ነቅንቆ ከርሟል፡፡ የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ቪልኸልም ጁኒላ ከሥራ እንዲለቁ ያደረጋቸው ምክንያትም ከአራት ዓመታት በፊት የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክተው አፍሪካውያንን የገለጹበት የዘረኝነት ንግግር ነው፡፡

የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ከአራት ዓመታት በፊት በሰጡት ዘረኛ አስተያየት ምክንያት የሚኒስትርነቱን ሥልጣን በያዙ በአሥረኛ ቀናቸው ሥልጣን መልቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡  

የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ እ.ኤ.አ. በ2019 ‹‹የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለውን ቀውስ ለመዋጋት ፊንላንድ በአፍሪካ ጽንስ ማቋረጥን መደገፍ አለባት፤›› ብለው መናገራቸው ወደ መንግሥት ሥልጣን ሲመጡ እንዲጠየቁ አድርጓቸዋል፡፡

‹‹ያላደገ ማኅበረሰብ፣ ከፍተኛ የሕፃናት ቁጥርና ችግሮች እየተባባሱ ባለበት አፍሪካ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሩን አስከፊ አድርጎታል፡፡ በረሃብ፣ በበሽታና በአየር ንብረት ለውጥ የሚቸገሩ፣ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከፍተኛ የካርቦን ልቀት ወዳለበት የሚሄዱ፤›› ሲሉም ነበር አፍሪካውያንን የገለጿቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ ፊንላንድ በአፍሪካ ጽንስ ማቋረጥን መደገፍ እንዳለባት ተናግረው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ቀልድ ያሳዩት የናዚ ሰላምታ ዛሬ ላይ ተመዞ ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

ዘጋርዲያን እንዳሰፈው፣ እሳቸው ሥልጣን እንደያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተቃውሞ በመውጣት መንግሥታቸውን ተቃውመዋል፡፡ ጁኒላ ከአራት ዓመታት በፊት የተናገሩት ፊንላንዳውያንን አይወክልም ብለዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ይቅርታ የጠየቁት ሚኒስትሩ፣ የእሳቸው በመንግሥት ሥልጣን ላይ መቆየት ለመንግሥታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ስላለው መልቀቃቸውን አሳውቀዋል፡፡

ከፊላንድ ሚኒስትሮች ከ15 ዓመታት በፊት በተናገሩት ወቀሳ እየደረሰባቸው የሚገኙት የፋይናንስ ሚኒስትሯ ሪካ ፑራ ሌላዋ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2008 ሃይማኖትንና ቀለምን/ዘርን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ጽሑፎች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ማስፈራቸው ነው ለዛሬው ቀውስ የዳረጋቸው፡፡

ሚኒስትሯ ፑራ ታዲያ ከ15 ዓመታት በፊት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ስለጻፉት የጥላቻና የዘረኝነት ንግግር ‹‹ከ15 ዓመታት በፊት ለጻፍኩት ያልተገባ አስተያየት፣ ላደረስኩት ጉዳት ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ እኔ ፍፁም ሰው አይደለሁም፡፡ ስለሠራሁት ስህተት ይቅርታ እጠይቃለሁ፤›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸውን ዘጋርዲያን ገልጿል፡፡

ከሥልጣን እንደማይለቁ የተናገሩት ፑራ፣ በቢሮ በሚኖራቸው ብቃት እንደሚመዘኑ፣ የፓርቲያቸው ፖሊሲ በፅንፈኝነት፣ በዘረኝነትም ሆነ በማግለል ላይ ያልተመሠረተና የአገራቸውንና የፊንላንዳውያንን ፍላጎት መሠረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...