Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሥነ ጥበብና ሕክምና

ሥነ ጥበብና ሕክምና

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በሳይንስና በኪነ ጥበብ ሥራዎች መካከል መሠረታዊ ልዩነቶች ቢኖሩም አንዱ ለሌላው አስፈላጊ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡

ሳይንስ ግቡ በተግባር የተደገፉ መፍትሔዎችን ማዘጋጀት ሲሆን፣ ጥበብ ደግሞ የውስጥ ስሜትን በሥነ ጽሑፍ፣ በዳንስ፣ በሥዕል፣ በሙዚቃና በሌሎችም የጥበብ ሥራዎች ስሜትን ወይም ስሜታዊ ምላሽ ማስገኘት ነው ሲሉ ባለሙያዎች  ዕይታቸውን ሲያስቀምጡ ይስተዋላሉ፡፡

የጥበብና  የሕክምና ዝምድናቸው ምንድነው? ለሚለው ‹‹ጥበብ በራሱ ሕክምና ነው፣ ሕክምና ደግሞ ጥበብ ነው›› ይሉታል። በሐሳቡ ዙሪያ በጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በተዘጋጀው ሲምፖዚየም የጤና ተማሪዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና አርቲስቶች ተገኘተው  ስለ ጥበብና ሕክምና ተወያይተው ነበር፡፡

‹‹ሕክምና ሳይንስነቱ እንዳለ ሆኖ ጥበብ ነው፤›› ‹‹ሲሉ የጥበብና የሕክምናን ተመጋጋቢነትን የሚገልጹት ደራሲው ምሕረት ደበበ (ዶ/ር)፣ ‹‹ጥበብ ሕክምና ነው፣ ሰዎች በጥበብ ይታከማሉ፣ ጥበብ በራሱ ማከም መፈወስ የሚያስችል ነው፤›› ሲሉ ያክላሉ፡፡ በሌላ በኩል ሕክምናው እንዳለ ሆኖ ለብቻው እንደ ጥበብ መታየት ይኖርበታል ሲሉም ያብራራሉ፡፡

የሕክምና ጫናን በማንሳት በሕክምና ውስጥ ያለው ጥበብ ሕክምና በመሆኑ  እንዴት  እንጠቀምበት? የሚለውም በደንብ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ባለሙያው አገላለጽ፣ ሕክምና  ጥበብ ነው የሚለውን ሐሳብ ትኩረት ሰጥቶ ማሰብ፣ ጥበብ ደግሞ ሕክምና ነው የሚለውን ለብቻ መረዳት ለአርቲስቶችም ሆነ ለሕክምና ባለሙያዎች   በእጅጉ ጠቃሚ ነው ።

በተለይ ሐኪም በውስጡ ያለውን  ጥበብ ቆፍሮ ማውጣት  ይኖርበታል የሚሉት  ምሕረት ደበበ፣ የሕክምና ትምህርት የተዋጣለት ዶክተር ያደርገኛል ከሚለው ሐሳብ ውጭ ሕክምናን እንደ ጥበብ በመውሰድና እንደ ሐሳብና ስሜት ማፍለቂያነት መጠቀም ተገቢ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ጥበብ የሰውን ልጅ ነፃ የሚያወጣ ሲሆን፣ ሕክምና ደግሞ ነፍስን የሚያስጨንቅ በራስ ላይ ከፍተኛ ጫናን የሚፈጥር በመሆኑ፣ ሕክምና ለጥበብ  ከሚሰጠው ትኩረት ይልቅ ለተግባራዊነቱ የሚሰጠው ነፃነትና ደስታ ይበልጣል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

 በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ባለሙያው አታክልቲ  ባራኪ (ዶ/ር)  በበኩላቸው፣ በሕክምና ትምህርት ያሉ ተማሪዎች በውስጣቸው ያለውን ጥበብ በደንብ ማወቅ ከቻሉ ጥሩ የሕክምና ባለሙያ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ከሕክምና ስንወጣ ሥነ ጥበብን እንዴት በሕክምና ላይ እንጠቀምበታለን ሳይሆን፣ ታማሚዎች ለሕክምና ሲመጡ ደስተኛ ሆነው እንዲመለሱ ወደ ጥበብ መሳብ  እንዲችሉ ማድረግ አለባቸሁ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ  አታክልቲ (ዶ/ር) ገለጻ፣ የጥበብና የሕክምና አንድነት ሁለቱም በጥልቀት ማሰብን መጠየቃቸው ነው፡፡ ስለ ጥበብ ዕውቀት ያለው ሰው አንድን ነገር ሲመለከት የሚያይበት መንገድና ምንም ግንዛቤ የሌለው ሰው የሚያይበት ምልከታ እኩል አይደለም፡፡

የሳይንስና የኪነ ጥበብ ፉክክር ከጥንት ጀምሮ ነው የሚሉት ደግሞ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም ደነቀ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ሳይንስና ጥበብ ፉክክራቸው  ልዩነትና አንድነታቸው ከጥንት መጀመሩን፣ ሳይንስ ማለት ሁሉን ነገር በሒሳብ ሥሌት መሥራት ወይም መለካት  ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡  ‹‹ጥበብ  ከሳይንስ ዝቅ ይላል›› በማለት የሶቅራጥስን ሐሳብ በመጥቀስ  ጥበብና ሕክምና በማወዳደር ገልጸውታል፡፡

ትክክል ነው አይደለም የሚለው እንዳለ ሆኖ፣ ሐሳቡ በጥበብና በሕክምና አንድነትና ልዩነት ላይ የነበረው ክርክር ከጥንት የጀመረ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡

በጥበብና በሳይንስ መካከል ያለውን ልዩነት ለማመዛዘን እየተደረገ ያለው ትግል ቀጥሎ፣ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የሚባሉ ትምህርት ቤቶች ጥበብና ሳይንስን አያይዘው ቢያስተምሩም፣ ጥበቡ ግን ቢያመዝን የተሻለ ነው በማለት ሙከራ እያደረጉበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ እሳቸው አገላለጽ፣ በተለይ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ጥበብና ሕክምናን ለማዋሃድ መጀመር ያለባቸው በቅድሚያ  መፅዳትና ለዓይን ምቹ መሆን አለባቸው ። ስለ ጥበብ ማውራት ያለባቸው  አርቲስቶች ብቻ ሳይሆኑ መምህራንም ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም በመምህራንና በተማሪዎች መካከል ያለውን መቀራረብ  የሚያጠናክር  መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው  ጥበብ  ሚና አለው ።

ዛሬ በጫና  ውስጥ ሆኖ ያሳለፈ ተማሪ ነገ  በሥራ ቦታው ተማሪዎች እሱ ባለፈበት መንገድ እንዲያልፉ ይፈልጋል፡፡  ተማሪዎችን ቢያጣ እንኳን  በበሽተኞች ላይ ማንፀባረቁ አይቀርም፡፡

ስለዚህ ይህ ሁሉ ነገር ይቀር ዘንድ  ሳይንስ በጥበብ እየተዋዛ ለሁሉም ተማሪ ቢሰጥ የሚሉ አስተያየቶች በመድረኩ ቀርበዋል።

ሐኪም የቱንም ያህል የሕክምና ጥበብ ቢኖረውም ከሕመምተኛው ጋር እንዴት መቀራረብ አለበት? በምን መልኩ በሽተኛውን መረዳት አለበት? የሚለውን ግንዛቤ ማወቅና ጥበብን መረዳት ያሻዋል፡፡

የሕክምና ባለሙያ ጥበብን ማወቅ መረዳትና መተግበር እንዳለበት ሁሉ፣ አርቲስቶችም ስለ ሕክምና ጥበብ ግንዛቤው ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ ጥበብና ሕክምናን  በጋራ ለመተግበር አመቺ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...