‹‹ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ያስተዋወቀችና የኢትዮጵያን ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ያደረገች፣ ለእውነት፣ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለታሪክ፣ ለፍቅርና ለጀግንነት፣ እንዲሁም ለሰው ልጅ ክብር የተጋች ከራሷ ይልቅ አገሯን ያስቀደመች የኢትዮጵያ ዓርማና የአፍሪካ ፈርጥ በመሆኗ ተገቢ ዕውቅና ይሆናት ዘንድ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት፣ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 352/2008 ዓ.ም. በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በማኅበረሰብ አገልግሎት የዓመቱ የክብር ዶክትሬት (Honoris Causa) ለእንቁዋ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እንዲሰጣት ወስኗል፡፡››

(ጂጂ) በአንድ ወቅት
ይህ ኃይለ ቃለ የተስተጋባው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ተማሪዎቹን በማስመረቀበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረክ ጎልታ ለምትታወቀዋ ስመ ጥር ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው (በዘፈን ስሟ ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መስጠቱን ባወጀበት ጊዜ ነው፡፡
ነዋሪነቷ በአሜሪካ ለሆነችው ጂጂ፣ በዕለቱ እሷ ባለመገኘቷ የተቀበሉት ወላጅ እናቷ ወ/ሮ ተናኘ ሥዩም ናቸው፡፡
በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ የድምፃዊቷን ሥራዎችና አበርክቶ በአቶ ጥበቡ በለጠ አማካይነት ቀርቧል፡፡
እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በአርቲስትነት የምትጥቀሰው ከድምፃዊነቷ ባሻገር ባለቅኔ፣ ተዋናይት፣ የዜማና የግጥም ደራሲ፣ ተወዛዋዥና የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችም መሆኗ ነው፡፡
በገጸ ታሪኳ እንደተመለከተው ጂጂ የሙዚቃ ፍቅር ያደረባት ገና በልጅነቷ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ አልበሞችን ሠርታለች፡፡
ከሠራቻቸው አልበሞች ቀዳሚው ፀሐይ የተሰኘውና ከሕዝብ ጋር የተዋወቀችበት ነው፡፡ በማከታተልም ኢትዮጵያ፣ ጉራማይሌ፣ Abyssinia Infinite፣ ሰምና ወርቅ እና ምሥጋና በተሰኙ ሥራዎቿ ዝናን አትርፋበታለች፡፡
ኢትዮጵያ አገሬ የሦስት ሺሕ ዓመት እመቤትና ‹‹እኔን የራበኝ ፍቅር ነው›› ተጠቃሽ ሥራዎቿ ናቸው፡፡
‹‹ጎጃም ያረሰውን ለጎንደር ካልሸጠ
ጎንደር ያረሰውን ለጎጃም ካልሸጠ
የሽዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ…
የሐረር ነጋዴ፣ ወለጋ ካልሸጠ
ፍቅር ወዴት ወዴት፣ ወዴት ዘመም ዘመም
አገር አለችኝ ወገኔ ነው ሽመም
እያለች የኢትዮጵያ ሕዝብ መስተጋብር ሊታወክ እንደሚችል ከማንም ቀድማ ሥጋቷን አስተጋብታ እንደነበር በመድረኩ ተወስቷል፡፡
ዓድዋ የተሰኘው ሙዚቃዊ ሥራዋም ለዘመን ተሻጋሪነት የበቃ፣ አገራዊ ነፃነትን በልዕልና ያውም በእርመኛ አርበኞች ሰማዕትነት መከበሩን ያሳየችበት ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡
‹‹የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት››… እንድትል፡፡
ጂጂ የአገሯን ገጽታ ከዳሰሰችባቸው ሙዚቃዎቿ መካከል ‹‹ዓባይ›› አንዱ ነው፡፡ እሱም ከመልክዓ ምድራዊ ባህሪና ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው ባሻገር፣ ስለ ጥንታዊነቱም በንቡር ጠቃሽና ሰውኛ ዘይቤዎች ማዜሟን አቅራቢው አቶ ጥበቡ በለጠ ገልጾታል፡፡
‹‹ስለ ዓባይ ወንዝ ከብሉይ ኪዳንና ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምራ እስከ ግብፅ አስዋን ግድብ ድረስ በዜማዋ ይዛን ከዓባይ ጋር በየሸለቆው እንድንፈስ አድርጋናለች፡፡ የጂጂን የባለቅኔነት ደረጃዋን በከፍታ ላይ ከሚያስቀምጡላት ሥራዎች መካከል ይኸው ዓባይ የተሰኘው ሙዚቃዋ ነው።››
ጂጂ ከአገሯ ባሻገር ኮንሰርቷን ከኬንያ ጀምሮ በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች አቅርባለች፡፡
ዘፈኖቿ ለተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ፊልሞች ማጀቢያ የሆኑ ሲሆን ለአብነትም በአገር ውስጥ ‹‹ያልደረቀ እንባ›› (Beyond Border) በተሰኘውና አንጀሊና ጆሊ በተወነችበት ፊልም ማጀቢያ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ጂጂ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለሰጣት ክብር ያስተላለፈችው የምስጋና መልዕክትም በዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ሠፍሯል፡፡ እንዲህም አለች፡-
‹‹በአክብሮት የሰጣችሁኝን የአክብሮት ዶክትሬት በጣም በትልቅ ደስታ ነው የተቀበልኩት። በጣም አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር ይስጥልኝ። እኔ በጣም፣ በጣም ነው የገረመኝ… ታጭቼ ብገኝ እንኳን የሚያስደንቀኝ ነበር፤ …ተመርጬ ስለተነገረኝ በጣም ነው የማመሰግነው። በጣም እግዚአብሔር ያክብርልኝ።››