Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱን ይቆጣጠር!

በአሁኑ ጊዜ በብዙዎቹ የመንግሥት አገልግሎት መስጫዎች የሚስተዋለው ዳተኝነት፣ የሥራ መጓተት፣ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ብልሹ አሠራርና ሙስና የዜጎችን መብት በእጅጉ እየተገዳደረ ነው፡፡ በመንግሥት ሆስፒታሎች፣ በወረዳዎችና በክፍላተ ከተሞች፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግብር ስብሰባ፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችና በመሳሰሉት ከመጠን ያለፉ ብልሹ አሠራሮች በስፋት ተለምደዋል፡፡ ለአገራቸው የሚያስቡ፣ ለሙያቸውና ለህሊናቸው የሚጨነቁና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የሚወጡ አመራሮችና ሠራተኞች እንዳሉ የማይካድ ቢሆንም፣ ከእነዚህ በተቃራኒ በብሔርና በጥቅም እየተሳሳቡ መንግሥታዊ ተቋማትን ያጨናነቁ ነውረኞች ግን እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ አገልግሎት ፈላጊዎች የሚያስፈልጋቸውን በትህትና የተሞላ መስተንግዶ ማቅረብ ቀርቶ፣ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ከአገልግሎት ፈላጊዎች ጥቅም ካላገኙ በስተቀር ሥራቸውን ማከናወን የተሳናቸው ተቋማቱን መጫወቻ እያደረጓቸው ነው፡፡ የመንግሥት ሆስፒታል በራፍ ላይ የሐኪም ፈቃድና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች ከመቸርቸር ጀምሮ፣ ዜጎችን በሀቅና በቅንነት ማገልገል የማይቻል ደረጃ ላይ ሲደረስ መንግሥት ምን እየሠራ ነው? ብቃት የሌላቸው ሹሞችና ሠራተኞች በዜጎች ጊዜና ገንዘብ ላይ ሲጫወቱ ተጠያቂው ማነው? ይህ ችግር በፍጥነት ይፈታ፡፡

በኅብረተሰቡ ከፍተኛ የሆነ ብሶት የሚሰማባቸው የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጉዳይ አንገፍጋፊ እየሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ኅብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ፣ ጥራትና ጊዜ አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም ብሏል፡፡ ለምሳሌ ብሎ ከጠቃቀሳቸው መካከል የሥራ ቅጥር፣ ፓስፖርት፣ የተሽከርካሪ ሰሌዳ፣ የኢንቨስትመንት መሬትና ከመሬት ጋር ተያያዥ አገልግሎቶች በትውውቅ፣ በምልጃና በገንዘብ እንደሚሸጡ አስታውቋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት የአሠራር ሥርዓት እንዲዘረጋ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል፡፡ አሁን ያለውን ያገነገነ ሙስና ለመከላከልና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊነትን አሳስቧል፡፡ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተጨማሪም የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በአደራ የተቀበሉት ኃላፊነት ዜጎችን በሕጉ መሠረት በቅንነት ለማገልገል ቢሆንም፣ ከዚህ በተቃራኒ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንቢተኛ የሆኑ አንዳንድ አካላት መኖራቸውንና ሊታሰብበት እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮችን በመጥቀስ የመፍትሔ ያለህ ብሏል፡፡

በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ዋና ተጠሪነቱ ለሕዝብ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መንግሥት ዜጎች መብቶቻቸውንና ግዴታዎቻቸውን ተረድተው በሥርዓት እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥታዊ ተቋማት አወቃቀርና የሹማምንቱ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ወሰን ግልጽ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ዜጎች የግብር ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ በተለያዩ ብሔራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑና ለአገራቸው ባላቸው አቅምና ዕውቀት እንዲያገለግሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን የሚያስፈጽሙ የመንግሥት ተሿሚዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት አሠራር ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት ሲጎድለውና የሹማምንቱ የተጠያቂነት ወሰን በማይታወቅበት ሁኔታ ውስጥ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይደፈጠጣሉ፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ተሿሚዎች በአግባቡ የሥራ ገበታቸው ላይ አይገኙም፡፡ ባለጉዳዮች አንድ ተሿሚ የያዘውን ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ለወራት ይንከራተታሉ፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ግዴታውን እየተወጣ፣ ተሿሚው የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ማከናወን ሲያቅተው እንዴት ነው የሚጠየቀው? የት ነው የሚከሰሰው? የት ነው የሚዳኘው? በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡

ባለጉዳዮችን እያንገላታ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ጥቅም ለማጋበስ የሚፈልግና ሥልጣኑን መከታ በማድረግ ሕግ የሚጋፋን ሹም ማን ነው የሚያስታግሰው? መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች ‹‹ሙስናንና ሌብነትን አልታገስም›› ሲል ይደመጣል፡፡ ከዚያ አልፎ ተርፎ የሥርዓቱ አደጋ እንደሆኑ ይወተውታል፡፡ ነገር ግን የሰው ኪስ ካልዳበሱ ሥራ መሥራት የማይሆንላቸው ሙሰኞች ሕዝብ እያማረሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ባለጉዳዮች መብታቸውን ለማስከበር ከሙሰኞች ጋር መደራደር እንደሌለባቸውና ድርጊቱም ሕገወጥ መሆኑ ቢታመንም፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ የተደራጁ ኃይሎችን እንዴት መቋቋም ይቻላል የሚለው አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል፡፡ በደላላና በጉዳይ አስፈጻሚዎች አማካይነት መረን የተለቀቀውን የዘቀጠ ድርጊት መንግሥት ካልዘመተበት ማን ይቋቋመዋል? እኔ ሙሰኝነትን አይዞህ አላልኩም ብሎ ዕርምጃ ካልወሰደ እንዴት ሊኮን ነው? በዚህ ላይ የራሱ የመንግሥት ቁርጠኛ አቋም ግልጽ ሆኖ መታወቅ አለበት፡፡ የሹማምንቱም ተጠያቂነት እንዲሁ፡፡ ተቆጣጣሪም ሆነ ተቆጪ የሌላቸው ጉልበተኞች አገር እያበላሹ ነው፡፡

የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕጉ ዜጎችን ካልታደገ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ሕዝቡን በታማኝነትና በቅንነት ካላገለገሉ፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስተዳዳሪዎች ሕዝቡን በሥርዓት ካላስተዳደሩ፣ የገበያውን ጤናማነት እየተቆጣጠሩ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት እንዲያሰፍኑ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ካልተወጡ፣ የሕዝቡን በሰላም ወጥቶ መግባት በተግባር ካላረጋገጡ፣ ግዴለሽነትና ሕገወጥነትን የሚያስፋፉ አካላት እንደፈለጋቸው እንዲፈነጩ ከተደረገ፣ መንግሥት አገር እያስተዳደርኩ ነው ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም፡፡ ይልቁንም አሉታዊ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እየቦረቦሩት ነው ማለት ይቀላል፡፡ ስለዚህ ምን ታስቧል? በእጅ ላይ ያለ አፋጣኝ መፍትሔስ ምንድነው? በሕዝቡ ውስጥ ማኅበራዊ እኩልነት ሰፍኖ ዜጎች በአገራቸው ልማት ተሳታፊና የውጤቱ የጋራ ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው፣ ይህ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት የሚሆኑ ራስ ወዳዶች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ በተለይ የመንግሥት ሥልጣንን ላልተገባ ዓላማ በማዋል ዜጎችን የሚያስለቅሱ ኃይሎች እንዴት ነው በዚህ ድርጊታቸው የሚቀጥሉት? የኃላፊነቱና የተጠያቂነቱ ወሰን የት ጋ ነው?

የመልካም አስተዳደር ዕጦት የአገር አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኖ፣ በተደጋጋሚ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙባቸው የውይይት መድረኮች ብዙ ተብሏል፡፡ ነገር ግን የችግሮቹን ምንጮች ታሪካዊ ዳራ እያወሱ በይደር ከመተው ይልቅ፣ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ወገኖች መጠየቅ ማንን ይገዳል? መፍትሔ ያጣ ነገር ተሸክሞ ከመዞር፣ ችግሩን አሽቀንጥሮ መጣልና መገላገል ለምን ያቅታል? የተጠያቂነትና የኃላፊነት ወሰን በመጥፋቱ ምክንያት ብቻ አገር ይታመሳል፡፡ የሕዝብ አደራ አለብኝ የሚል መንግሥት የአገር ኢኮኖሚን ከማሳደግና መሠረተ ልማቶችን ከማስፋፋት በተጨማሪ፣ ለሕዝቡ ማኅበራዊ ዋስትና ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህም መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ የኑሮ ውድነትን በማርገብ፣ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት በማስፈን፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን በማስፋት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት በማስከበርና በመሳሰሉት ጉዳዮች ይገለጻል፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚኖረው ደግሞ መንግሥት አሠራሩ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሲኖርበት ነው፡፡ ባለሥልጣናቱም በዚህ መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲደረግ ነው፡፡ የመንግሥት አገልግሎት መስጫዎች ግን የተቆጣጣሪ ያለህ እያሉ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...