Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሥራ የተሰናቱ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች 100 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው በፍርድ ቤት...

ከሥራ የተሰናቱ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች 100 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው በፍርድ ቤት ተወሰነ

ቀን:

  • የፋብሪካውን ንብረት የዘረፉ እጅ ከፈንጅ ተይዘዋል ተብሏል

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከሥራ አሰናነበትኳቸው ካላቸው 1,500 የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች መካከል ለ965 ያህሉ 100 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው ፍርድ ቤት መወሰኑን፣ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

ሠራተኞቹ በስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ላይ በፍርድ ቤት ክስ መሥርተው እንደነበር፣ በክሱ መሠረት ለ965 ሰዎች ገንዘብ ኢንዲከፈላቸው ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን፣ የቀሪ ሠራተኞች ጉዳይ ገና በሒደት ላይ መሆኑን፣ የፋብሪካውን ንብረት የሚዘርፉ እጅ ከፈንጅ መያዛቸውንና ዝርፊያው ተባብሶ መቀጠሉ ነው ከሠራተኞቹ ገለጻ መረዳት የተቻለው፡፡

የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከሥራ ካሰናበታቸው 1,500 ሠራተኞች መካከል 965 ለሚሆኑት የተጠቀሰው መጠን ካሳ እንዲከፈላቸው ፍርድ ቤት መወሰኑን፣ የሠራተኞቹ ጠበቃ አቶ አበራ ከበደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ፍርድ አግኝተው ካሳ የተቀበሉ አሉ፣ ቋሚ ሠራተኞች በብዛት ወስደዋል፤›› ብለው፣ ሠራተኞቹም ምንም ዓይነት ቅሬታ አለማሳየታቸውን አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡

ሠራተኞቹ ካሳ እንዲከፈላቸው የተፈረደላቸው ያልተከፈላቸውን ደመወዝ፣ አበልና ሌሎች ጥቅሞቻቸውን መሠረት በማድረግ መሆኑን አቶ አበራ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ንብረት በጥበቃዎች ጭምር እየተዘረፈ በመሆኑ፣ የሚመለከተው አካል ድርጊቱን እንዲያስቆም ተጠይቋል፡፡

የፋብሪካውን ንብረት የዘረፉ እጅ ከፈንጅ መያዛቸውን፣ ዝርፊያው ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ እንዳልቆመ፣ ዘራፊዎቹም ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደተወሰዱ አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

‹‹ዘራፊዎች የተመደቡ ጥበቃዎች ሲሆኑ የመንግሥት አካላት እጅም አለበት፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹ማስቆም ስላልተፈለገ እንጂ የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ መንግሥት ጫና ቢያደርግ ድርጊቱን ማስቆም የሚያቅት አይደለም፡፡ መንግሥት የፋብሪካውን ዝርፊያ እንዴት ማስቆም ያስቸግረዋል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ኃላፊው በሰጡት ማብራሪያ መሠረት ከፋብሪካው ሕንፃ ላይ ቆርቆሮ እየተነቀለ እየተሸጠ ነው፡፡ ከሕንፃ የፈረሰ የቴንድኖ ብረት በአዋሽ ሰባትና በጂቡቲ መውጫ መንገድ ጋላፊ በተሸከርካሪ ተጭነው እየተያዙ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ፋብሪካው እየደረሰበት ነው የተባለውን ዝርፊያ በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው ጥያቄ የቀረበላቸው የአፋር ክልል የዱፍቲ ከተማ ከንቲባ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዓሊ ሚራህ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ሠራተኞቹ በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ላይ በመሠረቱት ክስ ካሳ እንዲከፈላቸውና ሌሎች ተፈጸሙብን ያሏቸው የመብት ጥሰቶች በሕግ እንዲታዩላቸው አቤቱታ ማቅረባቸውን፣ ከ1,500 በላይ ሠራተኞች ከሥራ በመሰናበታቸው ከ800 ሺሕ በላይ ሰዎች በከፋ ችግር ውስጥ እንደነበሩ፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በፋብሪካው የአገዳ ማሳ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት፣ ለሠራተኞቹ በየወሩ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ደመወዝ ሲከፍል መቆየቱን፣ ‹‹በሕጉ መሠረት በደብዳቤ አሳውቆ›› ሠራተኞቹን በጥር ወር 2015 ዓ.ም. ከሥራ እንዳሰናበተ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...