Wednesday, September 27, 2023
Homeስፖንሰር የተደረጉየላይፍላይን አዲስ የቤት ለቤት ጤና እንክብካቤ አገልግሎት ድርግጅት በጤናው ዘርፍ የቁርጥ ሥራ...

የላይፍላይን አዲስ የቤት ለቤት ጤና እንክብካቤ አገልግሎት ድርግጅት በጤናው ዘርፍ የቁርጥ ሥራ (ጊግ) ኢኮኖሚን የመገንባት ጉዞ

Published on

- Advertisment -

ዶ/ር ሰለሞን ደሳለኝ  ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በሕክምና የተመረቀው በ2009 ዓ.ም. ማብቂያ ነበር። ትምህርቱን ጨርሶ ብዙም ሳይቆይ፣ ሰለሞን እዛው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በመቀጠር መሥራት ጀመረ፤ ሐሳቡም የማኅጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት የመሆን ጉዞውን መያያዝ ነበር። ይሁን እንጂ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መሥራቱ በኢትዮጵያ የጤና እንክብካቤ ያለበትን አስከፊ ሁኔታ እንዲያይ አደረገው።

“በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በቀን ከ35 እስከ 40 ታካሚዎችን አክም ነበር። ይህም ማለት ከአንድ ታካሚ ጋር ከአምስት ደቂቃ በላይ ማሳለፍ አልችልም ማለት ነው፤ ካልሆነ የቀሩት ሳይታከሙ መመለሳቸው ነው። ሥርዓቱን አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም” በማለት ሰለሞን ታካሚዎችን ከልብ መርዳት ባለመቻሉ የተሰማውን  ስሜት ይገልጻል።

ሰለሞን ሥራ ከጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ ካስተማሩት መምህራን የአንዱ የቅርብ ወዳጅ የሆኑ ሰው በስትሮክ ተጠቅተው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይገባሉ። ታካሚው ሕክምናቸውን ጨርሰው ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ፣ ቤታቸው ሄዶ በመጎብኘት እንዲከታተላቸው መምህሩ ሰለሞንን ይጠይቀዋል።

“አንድ ሰው ስትሮክ ከደረሰበት በኋላ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ የሚመለከቱ ልብ መባል ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ ቤተሰቡ ደግሞ በዚህ አቅጣጫ ልምድ ስላልነበረው የባለሙያ እገዛ ያስፈልጋቸው ነበር” ሲል ሰለሞን አክሎ ይገልጻል።

ሰለሞን አንዴ ቤታቸው በመሄድ ታካሚውን ከጎበኛቸው በኋላ፣ ቤተሰቡ መላልሶ በመምጣት ለቤተሰባቸው አባል በግል የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጣቸው ጠየቁት።

“በመጀመሪያ እንዲያ ያደረግኩት እንደ ውለታ ስለነበር፣ ያሉኝን ለማድረግ ወላውዬ ነበር። በኋላ ላይ ግን አሳመኑኝ፤ ክፍያውም ጥሩ ነበር። ታካሚውን በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ እየሄድኩ እጎበኛቸው ነበር፤ የታካሚው ጤናም እየተሻሻለ ሄደ። ይህም በእውነቱ መነሣሣት ፈጥሮብኝና አስደስቶኝ ነበር” ሲል ሰለሞን ያስረዳል።

“ከዚህም በላይ እኒያ ታካሚ ራሳቸው ሌሎች ወዳጆቻቸው ጋር እያገኛኙኝታካሚዎችን ቤታቸው እየሄደ የሚያክም ሐኪም ሆንኩ” ይላል።

ይህን ከመሰለው አነስተኛ ጅማሮ በመነሣት፣ ከአራት ዓመታት በፊት ሰለሞን ከጓደኞቹ ከቃለአብ ጌታቸው (ዶ/ር) እና ዮናስ ክፍሌ (ዶ/ር) ጋር በመሆን ላይፍላይን አዲስን አቋቋሙ፤ ድርጅቱም ሕጋዊ ሰውነት ያለው ራሱን የቻለ የቤት ለቤት የሕክምና እንክብካቤ አገልግሎት የሚሰጥ ቢዝነስ ሆኖ ተቋቋመ።

ዛሬ ላይፍላይን አዲስ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ የሆኑ ሦስት ጠቅላላ ሐኪሞችና 17 ነርሶች፣ ፍዚዮቴራፒስቶች እንዲሁም ሳይኮቴራፒስቶች (የሥነ ልቦና አማካሪዎች) አሉት። በተጨማሪም የቁርጥ ሥራ ሠራተኞች በመሆን እንደ አስፈላጊነቱ አገልግሎት የሚሰጡ 50 የጤና ባለሙያዎች ከላይፍላይን ጋር ይሠራሉ።

ላይፍላይን አዲስ የቤት ለቤት ጤና እንክብካቤ ድርጅት የሚሰጣቸው አገልግሎቶች

ላይፍላይን አዲስ ሦስት ዓይነት የቤት ለቤት ጤና እንክብካቤ አገልግሎቶችን ይሰጣል፤ የመጀመሪያው እንደ ካንሰር፣ የስኳር ሕመምና ስትሮክ የመሳሰሉ ሥር የሰደዱ ሕመሞች ላሉባቸው ታካሚዎች የቤት ለቤት እንክብካቤ መስጠት ነው። እንዲህ ያሉ ታካሚዎች አብዛኛውን ጊዜ ለመድኃኒት አወሳሰድ፣ አመጋገብ፣ ገላ መታጠብ፣ ዳይፐር መቀየርና ልብስ መልበስ ለመሳሰሉ ነገሮች የነርስ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል።

“ነርሶቻችን በ12 ሰዓት ፈረቃ ይሠራሉ፤ የታካሚዎች ቤት በመሄድም እንክብካቤ ይሰጣሉ። ኢንፌክሽን ወይም ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ዶክተሮች በየሳምንቱ ወይም በየሁለት ሳምንቱ በቋሚነት ጉብኝት ያደርጋሉ” በማለት ሰለሞን ያስረዳል። “የላብራቶሪ ምርመራ ካስፈለገም፣ ናሙና ከታካሚዎቹ የሚወሰደው በቤታቸው ነው።”

ላይፍላይን አዲስ የሚያቀርበው ሁለተኛው አገልግሎት ደግሞ የአጠቃላይ ጤና ጥቅል ሲሆን፣ ይህም የሚያተኩረው የቅድመ መከላከል እንክብካቤ ላይ ነው።

“ዶክተር፣ የአመጋገብ ባለሙያ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አማካሪን በአንድ ላይ የያዘ ቡድን የደንበኞቻችን ቤት ድረስ በመሄድ እንደ ጥቅሉ ዓይነት በየወሩ፣ በየሦስት ወሩ ወይም በየዓመቱ በመሄድ ጉብኝት ያደርጋል። ጉብኝቶቹ መላውን ቤተሰብ የሚሸፍኑ ሊሆኑ ይችላሉ። በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ተቋማት የአጠቃላይ ጤና አጠባበቅ የሚገኝባቸው ወይም እንዲያ ለማድረግ የሚጋብዙ አይደሉም፤ ስለዚህ እንዲህ ያለውን የጤና እንክብካቤ ቤታቸው ድረስ ይዘንላቸው እንሄዳለን” ይላል ሰለሞን።

አክሎም እነዚህን ጥቅሎች ለማስተዋወቅ ያደረጓቸውን ጥረቶች አጽንዖት ሰጥቶ ያስረዳል። ለዚህ እንደ ምሳሌም ዳያስፖራ የሆኑ ሰዎች በቀላሉ አገር ቤት ለሚገኙ ዘመድ ወዳጆቻቸው ጥቅሉን መግዛት የሚችሉበትን አማራጭ ይጠቅሳል፤ እንዲህ በማድረግ የዘመድ ወዳጆቻቸው ጤና በቂ መጠበቅ እና መከታተልይችላሉ።

ላይፍላይን አዲስ የሚሰጠው ሌላኛውአገልግሎት የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ሲሆን፣ በዚህም እንደ የሆስፒታል አልጋዎች፣ ዊልቼይሮች፣ የኦክሲጅን ሲሊንደሮች፣ የመምጠጫ (ሰክሽን) ማሽኖች እና የደም ግፊት መለኪያ ያሉትን ያቀርባል። ይሁን እንጂ የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት የቢዝነሳቸው ዋና ትኩረት አለመሆኑን ሰለሞን ይገልጻል።

“ይህ ከመጀመሪያው አቅደን የገባንበት ሥራ አይደለም። ሆኖም ለሰዎች ሕይወት ወሳኝ የሆኑ ቁሳቁስ አቅርቦትን በተመለከተ፣ ሙሉ በሙሉ ሐሳባችንን ሦስተኛ ወገን ላይ ጥለን ልንቀመጥ አንችልም። የሕክምና ቁሳቁስ ለታካሚዎቻችን ማቅረቡን የጀመርነው ከዚህ የተነሣ ነው” ሲል ሰለሞን ያስረዳል።

ቤተሰቦች የላይፍላይን አዲስ አገልግሎቶችን እንዴት ማግኘት ይችላሉ?

ቤተሰቦች የላይፍላይን አዲስ ባለሙያዎች ቤታቸው እንዲመጡ ሲፈልጉ፣ በቀላሉ ላይፍላይን አዲስ ጋር መደወል ይችላሉ፤ እንዲህ ሲያደርጉ ወዲያውኑ ዶክተር መጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲጎበኛቸው ይመቻችላቸዋል። በመጀመሪያ ምርመራው ላይ በመመሥረት፣ ለታካሚው የሚስማማ  የሕክምና ዕቅድ ይቀረጽላቸዋል።

ምን ያህል የነርስና የሐኪም ጉብኝት ያስፈልጋል የሚለው የሚወሰነው በዚህ ምርመራ ነው። የላይፍላይን አዲስ የዶክተር ጉብኝት በአንድ ጊዜ ከ1,500 እስከ 2,000 ብር ሲሆን፣ የነርስ ጉብኝት ደግሞ በ12 ሰዓታት ፈረቃ 700 ብር ያህል ያስከፍላል።

ሰለሞን የላይፍላይን አዲስ ዋጋ በመጠኑ ከፍ ያለ መሆኑን ቢያምንም፣ ትኩረቱ የአገልግሎቱ ጥራት ላይ መሆኑን አጽንዖት ይሰጣል።

“ነርሶች አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ታካሚ ጋር ለ12 ሰዓታት ሙሉ እንክብካቤ በመስጠት፣ ልዩ ልዩ ተግባራትን በማከናወንና የሚያስፈልጋቸውን በማድረግ አብረዋቸው ይቆያሉ። ቤተሰቦች የሚከፍሉት እንዲህ ላለው በሙሉ  ትኩረት ለሚሰጥ የተሟላ የሙሉ ቀን የጤና እንክብካቤ ነው” በማለት ሰለሞን ያብራራል።

“ከዚህም በላይ፣ የግል ሆስፒታሎች የሚያስከፍሉት ክፍያ በጣም ውድ ነው። በአማካይ አንድ ሆስፒታል ለአንድ ቀን ብቻ ከ5,000 ብር በላይ ያስከፍላል፤ ይህ ያውም ተጨማሪ ወጪዎችን ሳይጨምር ነው። ሥር የሰደዱ ሕመሞች ያሉባቸው ታካሚዎች ለበርካታ ወራት ሕክምና መከታተል ሊያስፈልጋቸው ስለሚችል እንዲህ ያለ ክፍያ እየከፈሉ መታከም ሊያቅታቸው ይችላል” ሲል ያክላል።

የላይፍላይን የአጠቃላይ ጤና አጠባበቅ ጥቅሎች ግን ከ50 እስከ 250 ዶላር የሚከፍልባቸው ናቸው። የ50 ዶላሩ ጥቅል በዓመት የአንድ ጊዜ የተሟላ የሕክምና ምርመራና አጠቃላይ የላብራቶሪ ምርመራን የሚያካትት ሲሆን፣ የ250 ዶላሩ ጥቅል ደግሞ በዓመት የ12 ወርሃዊ የሐኪም ጉብኝትና በየሦስት ወሩ የሚደረግ የላብራቶሪ ምርመራዎችን የያዘ ነው።

እንደ ቀዳሚ የጤና እንክብካቤ የቁርጥ ሥራ ፕላትፎርም የላይፍላይን አዲስ የወደፊት ጉዞ

ላይፍላይን አዲስ በቅርቡ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን እና ገበያ ኩባንያ ትብብር ውጤት የሆነውን መሥራት ፕሮግራምን ተቀላቅሏል። መጋቢት 2015 ዓ.ም. በይፋ ሥራውን የጀመረው ፕሮግራሙ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ 100 ሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ለመጨመር ያለመ ሲሆን፣ ይህንንም የሚያደርገው ዘርፈ ብዙ የቁርጥ ሥራ የገበያ ፕላትፎርሞችን በማቅረብ ነው።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ልዩ ልዩ የገበያ ፕላትፎርሞች አንዱ የሆነው ላይፍላይን አዲስ ከፕሮግራሙ ጋር አብሮ እንዲሠራ ተመርጧል። በመሥራት ፕሮግራም ድጋፍ፣ ላይፍላይን አዲስ 10,000 ሥራዎችን መፍጠርንና በኢትዮጵያ ቀዳሚ የጤና የቁርጥ ሥራ ፕላትፎርም መሆኑን አስጠብቆ መቀጠልን ዓላማ አድርጎ ይዟል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የጤና ባለሙያዎች እጥረት የለም፤ ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ባለሙያዎቹ የሚያገኙት ክፍያ አነስተኛ ነው። “ወደ ፕላትፎርሙ ብዙ የቁርጥ ሥራ ሠራተኞችን ከመጨመራችን በፊት በቅድሚያ ገበያውን መፍጠር እንፈልጋለን” ሲል ሰለሞን ያስረዳል።

“ከመሥራት ፕሮግራም የቴክኖሎጂ ድጋፍ፣ የገበያ ማፈላለግ (ማርኬቲንግ) እገዛ፣ ሥልጠና እንዲሁም የአቅም ግንባታ እናገኛለን” ሲል ያክላል።

ላይፍላይን አዲስ ከመዲናዋ የማለፍን ራእይ ሰንቋል።

“ስትሮክ ከተማና ገጠር ወይም ሃብታምና ድሃን የማይለይ ሕመም ነው። ሁሉንም ያጠቃል። ገጠሩን አካባቢ መድረስና አገልግሎቶቻችንን ለሕዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንፈልጋለን። በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች ውስጥ ለመስፋፋት የምናስበው ለዚህ ነው” ሲል ሰለሞን ይገልጻል።

ሰለሞን እነዚህን ግቦች ማሳካት እንደሚቻል በጽኑ ያምናል፤ ደግሞም የቤት ለቤት የሕክምና አገልግሎት በኢትዮጵያ ያለው ገበያ እያደገ እንደሚሄድ ተስፋ አለው።

“ከቤት ለቤት ጤና እንክብካቤ ሌላ ያለው አማራጭ ሆስፒታል ውስጥ መቆየት ወይም ደግሞ ቀን ተሌት ታካሚውን እንዲንከባከቡ የቤተሰብ አባላት ላይ መደገፍ ነው። ነገር ግን ሆስፒታሎች ውድ ናቸው፤ ታካሚዎችም አብዛኛውን ጊዜ ቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር መቆየትን ይመርጣሉ። ይህ መሆኑ በራሱ የማገገም ዕድላቸውን ይጨምረዋል። በተጨማሪም የጤና እንክብካቤውን ኃላፊነት በመውሰድ ላይፍላይን አዲስ የቤተሰብ አባላት ቤተሰባቸውን ማገዝ በሚያስችላቸው የቀን ተቀን ተግባራቸውላይ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል” በማለት ዶክተሩ ያክላል።

የቅርብ ጊዜ መጣጥፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ለሁለት ሳምንት ያክል የፓርቲ ስብሰባ ላይ ቆይተው አመሻሹ ላይ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ባለቤታቸው በአግራሞት ተቀብለው ስለቆይታቸው ይጠይቋቸው ጀመር]

እኔ እምልክ...? ውይ... ውይ... በመጀመሪያ እንኳን በሰላም መጣህ፡፡ እሺ ...ምን ልትጠይቂኝ ነበር? ይህን ያህል ጊዜ የቆያችሁት ለስብሰባ...

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች የመንግሥት ጦርን አስለቅቀው የጎንደር ከተማን...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ተከታታይ የሆኑ ማሻሻያዎችና አዲስ...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ ተንፍሶባቸው እየቀየሩ ናቸው። በዚህ ስንሞላው...

ተመሳሳይ

በአፍሪካ የገንዲ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችሉ መፍትሄዎች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደረሰ

የአፍሪካ እንስሳት ትራይፓኖሶሚያሲስ (AAT) በመባል የሚታወቀው የገንዲ በሽታ ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካውያን የእንስሳ እርባታ...

ታምሪን ሞተርስ አዲስ ያስመጣዉን ሱዙኪ ኢኮ ቫን ሞዴል በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ

ለአካባቢ ሥነ ምህዳር ምቹ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ከሚያመርተው እና በዓለም ታዋቂ ከሆነው የሱዙኪ ኩባንያ ጋር...

 “ሰው ልማትን ማግኘት መብቱ ነው የሚለው ዕሳቤ እንዳይጠፋ በሰፊው አስተዋጽኦ አድርገናል”

ወ/ሮ ሰላማዊት መንክር፣ የሲቪል ማኅበራት ድጋፍ ፕሮግራም ቡድን መሪ በብሪቲሽ ካውንስል በሚመራ የአስፈፃሚዎች ጥምረት አማካይነት...