- ሕዝቡ በጣም እየተማረረ መምጣቱን ግን ታውቁታላችሁ?
- በምን ምክንያት?
- በኑሮ ውድነቱም በሌላውም። ግን ግን?
- ግን ምን?
- ሕዝቡ ተማሯል ያልኩትን ተወውና …
- እ …?
- በአገሪቱ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት መኖሩን ግን ታውቃላችሁ?
- እንዴት አናውቅም? ሚኒስትር ብሆንም የቤቴ ወጪ መጨመሩን ይጠፋኛል ብለሽ ነው?
- የቤትህ ወይም የቤታችሁ ወጪ መጨመሩን ብቻ ነው የምታውቁት?
- ለምን?
- እ …?
- የሁሉም ነገር ዋጋ መጨመሩን እናውቃለን። ነገር ግን ደግሞ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ያመጣው መሆኑንም እንገነዘባለን።
- እንዴት?
- የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሲያድግ የምርቶች ዋጋ ይጨምራል።
- የአገሪቱ ኢኮኖሚ አድጎ ከሆነማ የተትረፈረፈ ምርት ባይሆንም በቂ ምርት እየተመረተ ነው ማለት ነው።
- እሱን እኮ ነው የምልሽ?
- አይደለም። በቂ ምርት እየተመረተ ከሆነማ ዋጋ ይወርዳል። ዋጋ ከወረደ ደግሞ የኑሮ ውድነት አይኖርም ወይም ሕዝብ አያማርርም።
- የዋጋ ንረቱ የተባባሰው በእኛ ምክንያት አይደለም።
- ታዲያ ምንድነው?
- የዋጋ ንረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በመከሰቱ ነው።
- ምን?
- በአሁኑ ወቅት በዋጋ ንረት ያልተጠቃ የዓለም አገር ፈልገሽ አታገኚም። ሁሉም በዋጋ ንረት ተመቷል።
- የዋጋ ንረት ተስቦ ሆኗል በለኛ?
- ማለት ይቻላል።
- ተስቦ ከሆነማ ተዛምቶ ሕዝቡ እንዳይጎዳ አንድ ነገር ማድረግ አለባችሁ።
- ምን እናድርግ?
- መከተብ!
- ምንድነው የምታወሪው?
- የኑሮ ውድነት ተስቦ ሆኗል አልክ አይደል እንዴ?
- እና ብልስ?
- እንዳይዛመት መከተብ ነዋ፣ ካልሆነ ደግሞ ባህላዊ ሐኪሞችንም ማማከር ነው።
- ትቀልጃለሽ አይደል?
- እናንተ ስትቀልዱ ምን ላድርግ?
[ክቡር ሚኒስትሩ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ሳይገኝ ከቀረው አንድ የተቋማቸው ባልደረባ የሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልን አስጠርተው እያናገሩ ነው]
- ለምንድን ነው በዚህ አገራዊ ፋይዳ ባለው ፕሮግራም ላይ ያልተገኘኸው?
- ክቡር ሚኒስትር ህሊናዬ አልፈቀደልኝም።
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር ችግኝ መትከል እንዳለበት አምናለሁ ነገር ግን ሰው ይቀድማል።
- ሰው ይቀድማል ስትል ምን ማለትህ ነው?
- መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ለችግኝ የሰጡትን ያህል ትኩረት ለዜጋው እየሰጡ አይደለም።
- እንዴት? እና ማንን ነው እያገለገልን ያለነው?
- ዜጋው ለችግኝ የተሰጠውን ያህል ትኩረት አላገኘም። በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው። በልቶ የሚያድረው እያጣ ነው።
- እርግጥ ነው የሁሉም ነገር ዋጋ ጨምሯል። ቢሆንም መንግሥት ዝም ብሎ አልተቀመጠም።
- ክቡር ሚኒስትር ተሳስተዋል።
- ምን?
- የሁሉም ነገር ዋጋ ጨምሯል ያሉት ትክክል አይደለም።
- እንዴት?
- ያልጨመረ አለ።
- ምን?
- የሰው ልጅ ዋጋ ቀንሷል።
- መቃወምና መተቸት ብቻ ውጤት የሚያመጣ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል።
- አልተሳሳትኩም ክቡር ሚኒስትር?
- ቆይ የመጀመሪያ ዓመት የችግኝ ተከላ ፕርግራም ላይ ግንባር ቀደም አልነበርክም እንዴ?
- ነበርኩ።
- እንዲያውም ችግኝ ስታድል እንደነበር አስታውሳለሁ።
- ልክ ነው።
- ታዲያ አሁን ምን ተፈጠረ? ምን የተለየ ነገር መጣ?
- ክቡር ሚኒስትር ያኔ ችግኝ ተከላውን ሳስተባብር ዜጎች ክብር ነበራቸው።
- አሁንስ?
- ክቡር ሚኒስትር አሁን ችግኝ እንትከል ትላላችሁ በሌላ በኩል ደግሞ ነዋሪዎችን …
- ነዋሪዎችን ምን?
- ከመኖሪያ ቤታቸው ትነቅላላችሁ!