በሳሙኤል ረጋሳ
ከሃምሳ ዓመት በፊት በአኅጉር ደረጃ አፍሪካና እስያ እኩል ደሃና ኋላቀር አኅጉሮች ነበሩ። በአገር ደረጃም ኢትዮጵያ፣ ቻይናና ህንድ እኩል ደሃና መረጋጋት የማይታይባቸው አገሮች ነበሩ። ዛሬ በአኅጉሮቹም ሆነ በአገሮቹ መሀል ለንፅፅር የሚቀርብ ቀርቶ የሚቀራረብ ነጥብ የለም። ሌሎችንም የእስያና የአፍሪካ አገሮችን በተመሳሳይ ሁኔታ ማንሳት ይቻላል። ዛሬ ከላይ የተጠቀሱት የእስያ አገሮች በኢኮኖሚያቸው ዓለም ላይ ቻይና የሁለተኛነትን፣ ህንድ ደግሞ የአምስተኛነትን ደረጃ ተቆናጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህ የድህነት እኩዮቿ ተዓምራዊ በሚመስል መልክ ይህን ሁሉ መሻሻልና ዕድገት ሲያመጡ የት ነው ከዕድገት ሸሽታና ተደብቃ የነበረው? ምክንያቱ ሊሆን የሚችለው ወይ በተፈጥሮ ያልተሟላላት አገር ስለሆነች፣ ያለበለዚያ ደግሞ ሕዝብና መንግሥት ዘንድ ችግር ስለነበረ ነው። ወደሚለው ድምዳሜ ሊመራን ይችላል። በተፋጥሮ በኩል ያየን እንደሆነ ኢትዮጵያ ሰፊና የለም አፈር ባለቤት ነች። ዓመቱን ሙሉ የውኃ ችግር የማይታይባት አገር ነች። የአየር ፀባይዋም በዓለም ላይ ካሉት ለነፍሳት፣ ለአዝዕርት ሆነ ለኑሮ የሚመች ጥቂት አገሮች ውስጥ ነች። በቂ የማዕድን ሀብትም አላት። ለዘመናት ነፃ ሆና በሌሎች ሳትጨቆን የኖረች ብቸኛዋ አፍሪካዊ አገር ናት። የሚገርመው ጉዳይ ግን ይህ ሁሉ ሆኖ ከማንም አገር በበለጠ ወንዝ ውስጥ ቆማ ትጠማለች። ለም አፈር ላይ ተቀምጣ ትራባለች። በተፈጥሮ የታደለችውን የሚያስቀና የማዕድንና የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ ትተዋት ከሄዱት የቀድሞ ቢጤዎቿ ጋር ለመጓዝ ሙከራም አላደረገችም። አብራ ወደ ዕድገት መጓዝ ሳይሆን በነበረችበትም መርጋት አቅቷት የአገሪቱ ህልውና ፈተና ውስጥ እስከመግባት ደርሷል። የተባበሩት መንግሥታትም ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት ሲመሠረት እኛ ከመሥራቾቹ ውስጥ ነን፡፡ ብዙዎች ዛሬ ከእኛ ልቀው የሄዱ የአፍሪካ መንግሥታት ያን ጊዜ አልተፈጠሩም።
የእኛ ነገር በነበር ብቻ ቀርቷል። የዚህች አገር ያለፉት ታሪኮች የቀደምት ኢትዮጵያውያን እንጂ በምንም መሥፈርት የእኛ ነው ብለን በየአደባባዩ መፎከር የለብንም። የእኛን አሁን በምናየው መልኩ እየሠራን ነው። በከፍተኛ ተጋድሎ የቆመችን አገር የ60ዎቹ ትውልዶች ባልገባቸው ፍልስፍናና በጠላቶቻችን ፕሮፖጋንዳ ተጠልፈው ከመስመር አስወጧት። አሁንም አገሪቱ መዳን ካለባት ይህ ትውልድ የፈለፈላቸውን የጥላቻ ኃይሎችና አስተምሮው ስህተት እንደነበረ፣ እነሱ ጭምር ወጥተው ድምፃቸውን ማሰማት አለባቸው። ሁሉም ዜጋ አገሪቱን ለመደገፍና ለመጥቀም ባይችል እንኳን የሚጎዳትን ላለማድረግ ምንጊዜም ይቻለዋል። አገርን በማዳን ሁሉም ይድናል። ራስን ብቻ በማዳን ግን አገርን ለማዳን አይቻልም። እኛ ራሳችን ለራሳችን ካልሆንን ከውጭ የሚመጣ ማንኛውም ኃይል መብትም ሀብትም ሊሰጠን ወይም ሊጨምርልን አይችልም። ከእኛ የሚፈልጉትን ለማግኘት እንጂ እኛ የምንፈልገውን ሊሰጠን የተዘጋጀ የውጭ ኃይል እንደሌለ የዓለም ሆነ የእኛ ተሞክሮ እያሳየን ነው።
ሁሉም ጉልበተኛ ከደጃችን ሞፈር ለመቁረጥ ነው የሚዘጋጀው። ምዕራባውያን ለሕዝባችን አዝነው የሚያነሱት አንድም የሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብት ጥበቃ ጥያቄ የላቸውም። የሕዝብን የመብት ጉዳይ ለራሳቸው ጥቅም እንዲመች አድርገው ሕግ ቀርፀዋል። ይህንንም ሕግ ለሴራ እየተጠቀሙበት ደሃ አገሮችን ለማንበርከክ አውለውታል። በመጀመርያ ደረጃ ይህንን የመብት ማስከበር ጉዳይ የሚያነሱት ሁሉም አገሮች ላይ አይደለም። ለአብነት ያህል ግብፅ ለመጀመርያ ጊዜ ባደረገችው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሕዝቡ ሞሐመድ ሙርሲን መርጦ ነበር። የሰውየው አካሄድ ሳይመቻቸው ቀረና በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አሁን ያሉት መሪ ጄኔራል አልሲሲ ሥልጣናቸውን ቀምተው ዘብጥያ አወረዷቸው። የምዕራባውያን መንግሥታትም ይህንኑ ፀረ ዴሞክራሲ የሆነ ኩዴታ ተቀብሎ ለጄኔራሉ ቡራኬ ሰጥቶ አቶ ብሎ አነገሣቸው። ይህ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚቻል አይደለም።
ዴሞክራሲን ዕውቀቱና ልምዱ የሌላቸው አካላት በሒደት ሊለማመዱትና ሊማሩት ሲገባ ስሙን ብቻ ነግሮ ወይ እመን ወይ ትሞታለህ የሚባል መሆን የለበትም። ዴሞክራሲ ሕግ አይደለም። በሒደት እንጂ ዕለቱን ለመተግበር አይቻልም።
አዲስ የተወለደ ሕፃን እያደገ ሲሄድ ከእናቱ ጡት ሌላ ተጨማሪ ምግብ ይታዘዝለታል። የታዘዘለት ተጨማሪ ምግብ ካልተስማማው የግድ እስከ ጊዜው ድረስም ቢሆን ወደ እናቱ ጡት መመለስ አለበት። የእኛም አገር ዕድገትና ህልውና ከሌሎች አገር ያስገባናቸው የፖለቲካና የአይዶሎጂ ፍልስፍና ሊዋሃዱ አልቻሉም፣ አልተስማሙንም። ስላልተስማሙንም ነው የቀነጨርነውና ዕድገታችን የተገታው። ስለዚህም ወደ እናታችን ጡት መመለስ የግድ ነው። ከሕዝባችን አኗኗርና ልምድ ጋር የተዋሃደውን የራሳችንን መፍትሔ ማስቀመጥ አለብን። ለጊዜው ለችግራችን መፍትሔ የሚሆን ተጠንቶ የተቀመረ ነገር ላይኖር ይችላል። ዋናው ጉዳይ ችግሩን ለይተን ማወቅ ነው። አዳዲስ ችግሮችም እንዳይፈጠሩ መጣር አለብን። ለችግሮቻችን መፈጠር ወይም መባባስ አዳዲስ አጀንዳዎችን የሚያዘጋጁ ብዙ ወገኖች አሉ። ከሚዲያዎች ጀምሮ እስከ ፅንፈኛና አክራሪዎች። ከውጭና ከአገር ውስጥ ግፋ ሲልም እስከ መንግሥት መዋቅር ሊዘልቅ ይችላል።
ቀደምትና የነፃ አገሮች ምሳሌ ከሆንና ከላይ እንደተገለጸው የተፈጥሮና የታሪክ በጎ ጎን ካለን በዚህ ሁሉ ረዥም የነፃነት ዘመን እስካሁን የመጣንበት መንገድ ለሚፈለገው ደረጃ ለምን አላደረሰንም የሚል ጥያቄ የሁሉም ዜጋ መሆን አለበት። እስካሁን ችግራችንን በመፍታት ወደ መስመር ይመልሱናል ብለን የሞከርናቸው መንግሥታት፣ ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች ነበሩን። ቢያድለን አንድ ጠንካራ መሠረት ያለው ፓርቲ ላይ ይጥለን ነበር። እንዳየነው ግን ፓርቲዎች የሚቃወሙት አስተሳሰብንና ፍልስፍናን ሳይሆን አስተሳሰቡን የተሸከመውን ግለሰብም ይሁን ሌላ ፓርቲ ጭምር ነው። ግፋ ሲልም ጥላቻው ወደ ብሔር ሊዘልቅ ይችላል። ስለዚህም ነው እስካሁን ያየናቸው እንደ ውኃ ሙላት የሚችሉትን ሁሉ ጠራርገውና አጥፍተው የሚያልፉት። ለብልሆች፣ ለነገር አዋቂዎችና ለመፍትሔ አምጪዎች የምንሰጠው ግምት እጅግ ዝቅ ያለ ነው። ብዙ ጊዜ እንደምናየው የአገራችን ሰው የሚደርስበትን ጥቃት የሚከላከለው በምክክርና በሐሳብ ሳይሆን በበለጠ መልሶ ማጥቃት ነው ብሎ ያስባል።
ጥቃትን ለመከላከል ያካበትነው ልምድ ጀግንነትን ፈጥሮልናል። ይህ ግን የተሟላ አይደለም። ይህ በበለጠ ማጥቃት ላይ የተመሠረተው ወኔ ትዕግሥትን፣ ብልኃትንና ምክክርን ቢጨምር ኖሮ በመጠቃቃት ከሚደርሰው የሰብዓዊና የኢኮኖሚ ኪሳራ ተርፈን ሀብታም አገር ትኖረን ነበር። ይህ ባለመሆኑ ነው ጀግና ሆኖ ወዲያውም ደሃ የሆነ ማኅበረሰብ የፈጠርነው። አሁን በዓለም ፊት ያለን ገጽታ ከቀድሞው የተሻለ ክብርና ደረጃ የሚያሰጠን ሳይሆን በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። የመራብ፣ የመጨራረስ፣ የኋላቀርነትና ሥልጣኔ አልባነት ቀዳሚ ተምሳሌት ሆነናል። ሰው ሲያልቅብን የማናዝን ብቻ ሳይሆን የማይገርመን ሆነናል። የመፈራረስ አደጋም ይደርሳል ብለው የሚሠጉ ብዙዎች አሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ከእነ ችግሯም ቢሆን መቀጠል የቻለችው የተፈጠረችበት መንገድና መሠረታዊ ሥሪቷ ጥልቀት ያለውና በቀላሉ የማይናድ በመሆኑ ነው።
አንዳንድ ምዕራባውያንና በቅርብም ያሉ ጠላቶቻችን ዋናው አጀንዳቸው የእኛን የአገር ሥሪት ጠንካራና ደካማ ጎን ስለሚያውቅ በደካማ ጎናችን ገብተው የዓላማቸው ማስፈጸሚያ ሊያደርጉን እንጂ፣ አንዱን ከሌላው የበለጠ ወደውት ወይም አዝነውለት አይደለም።
የኢትዮጵያ ችግር ብዙ ነው። ሥርም የሰደደ ነው። የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በርካታ እውነታዎች ሊኖሯቸው ይችላሉ። ለዚህም ነው ጠላቶቻችን መግቢያ ቀዳዳ የሚፈልጉብን። እኛ ቀዳዳውን መድፈን አቅቶን በድህነትና በጦርነት ዘለዓለማችንን እንማቅቃለን። አሁን ለችግራችን መፍትሔ ያመጣል የተባለ አንድ ዋናና ብቸኛ አማራጭ መጥቷል። ችግራችንን በአገር አቀፍ ደረጃ ተመካክረን መፍታት። ከዚህ የተሻለ ሊያድነን የሚችል ሌላ አማራጭ እንደሌለ ማወቅ አለብን። የኮሚሽኑን እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ በየሚዲያው እናያለን። አሁን ያለው ወቅታዊ ተግባሩም አጀንዳ መሰብሰብና ተወያዮችን መለየት ነው። በየክልሎች ውይይት ተደርጎበታል ሲባል ሰማን እንጂ፣ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ አልታየም። ሆነም ቀረ ጉዳዩ የአገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቡድንም ሆነ በግል ለምክክሩ ይጠቅማል ብሎ የሚያምንበትን ሐሳብ በሚችለው መንገድ ሁሉ ማንሸራሸር አለበት። እዚህ ላይ አንድ ሁላችንንም የሚመለከት ሐሳብ ማንሳት ያስፈልጋል። ለሺሕ ዓመታትም ይሁን ለመቶ ዓመታት ተጉዘን የመጣንበት መንገድ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ አድርሶናል። በዚህ ረዥም ዘመን ውስጥ የወደፊትም የወደኋላም የሒደት ጉዞ እንደነበር መገመት አይከብድም።
አሁን ሁላችንም ልንመካከርበት የሚገባ አንድ ዋነኛ አጀንዳ አለ። ይኼውም እስከ ዛሬ በመጣንበት መንገድ እንጓዝ ብንል እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር መቀጠል እንችላለን ወይ? የሚለው ነው። እስከ ዛሬ የመጣንበትን መንገድ ስንመረምር አማራጮች አሉን። ብንፈልግ እንደ አገር ከቆምንበት ጀምረን፣ ብንፈልግ በሺዎች፣ በመቶዎች፣ በስልሳ ዓመታትና ከዚያም ወዲህ ባሉ መገደብ እንችላለን። የዚህ አጀንዳ ውጤት ሊሆን የሚችለው አዎ እንዳለ መቀጠል እንችላለን፣ ማሻሻያ አድርገን መቀጠል እንችላለን፣ ፈፅሞ ሊያስኬደን ስለማይችል ሙሉ በሙሉ መለወጥ አለበት ከሚሉት አማራጮች አንዱ ላይ እናርፋለን። ጥያቄው መመለስ ያለበት በሁሉም የኢትዮጵያዊ ክልል ነው።
ኢትዮጵያ ስንል የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጥርቅምና ውህደት እንጂ አየር አይደለችም። ሁላችንም የሚያለያዩንን፣ የማንግባባበት ባህሪና ማንነት ይዘን ነው በዚህች አገር ውስጥ ያለነው። ጂኦግራፊያዊ ክልላችን በዚች አገር ውስጥ ሆነን ኢትዮጵያ የተፈጠረችው። ስለዚህ ተመካክረን ካልጠበቅናት እኛም የምንጠበቅበት የተለየ አገር የለንም። ኢትዮጵያ የምትባለው እንደ አገር ከፈረሰች ከፍርስራሹ ውስጥ ተርፎ የሚወጣ ልዩ ፍራሽ ወይም ክልል አይኖርም። እስከ ዛሬ የመጣንበትን መንገድ ስንመረምረው በዚህ መንፈስ መሆን አለበት። ጊዜውና ፖለቲካው በሒደት የፈጠሩብን የጥላቻና የመገፋፋት ስሜትን በጥበብና በብልኃት ከአገር ህልውና ጋር መዝነን ነው መመካከር ያለብን። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ልቦናችን ተመልሰን በድርጊታችን ተፀፅተን የምትፈራ የጋራ አገር መፍጠራችን የማይቀር ነው። አሁን ማድረግ የሚገባንን ባለማድረግ ወይም ማድረግ የማይገባንን በማድረግ የሚመጣውን አደጋ አስከትለን በፀፀት ወደማንመልሰው ደረጃ እንዳንደርስ እንጠንቀቅ። የመዳኛ ጊዜ እንደ ሁኔታው ሊያጥርም ሊረዝምም ይችላል። ዓለም ለሚሊዮን ዓመታት የሚያሠራ ሰፊ ጊዜ አላት፡፡ እኛ ደግሞ ለሥራ በጣም አጭር ጊዜ ነው ያለን። በትንሽ ጊዜ ከሚሠሩ መቋጫ የሌላቸው ሥራዎች ለምን ትንሿን ሠርተን አናልፍም? ይህች ዛሬ አንዳንዶች የሚታበዩባትና አንዳንዶች የሚያጣጥሏት አገር ሳናውቀው ከእጃችን ከወጣች በጩኸትና በለቅሶ መልሰን አናገኛትም።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡