Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት ዕውቅና ለሰጠው የቅርስ አዋጅ ተገዥ መሆን አለበት›› አቶ መቆያ ማሞ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበርን በዋና ሥራ አስኪያጅነት እያስተዳደሩ ያሉት አቶ መቆያ ማሞ ናቸው፡፡ በትምህርት ዝግጅት በዋይልድ ላይፍ ማኔጅመንትና ኤኮቱሪዝም፣ ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽንና ማኔጅመንት በተሰኙ ሙያዎች የማስተርስና የባችለር ዲግሪዎቻቸውን አግኝተዋል፡፡ በሥራ መስክም በካፋ ቦንጋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን በተለያዩ የኃላፊት ደረጃዎች ሠርተዋል፡፡ የአዋሽ የኦሞና ሃላይደጌህ-አሰቦት ገዳም ብሔራዊ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡ የምርምር ሥራዎቻቸውን በአፍሪካን ጆርናል ኦቭ ኢኮሎጂ (African Journal of Ecology) እና ጆርናል ኦቭ ናቹራል ሳይንስስ ሪሰርች (Journal of Natural Sciences Research) ላይ አሳትመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር ሠላሳኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የማኅበሩን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ ሔኖክ ያሬድ ከሳቸው ጋራ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡– ከማኅበሩ ዓላማዎች አንዱ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን መንከባከብ፣ ተጠብቀው ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ነው፡፡ ለተግባራችሁ አንዱ ማሳያ ከሁለት አሠርታት በላይ በጽሕፈት ቤትነት እየተጠቀማችሁበት ያለውንና ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የራስ ከበደ መንገሻ አቲከም ጥንታዊ ቤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቤቶች ኮርፖሬሽን ጥያቄ አንስቶባችኋል፡፡

አቶ መቆያ ፡- ቅርስ ባለአደራ በዚህ ቤት ትልቅ ፈተና ነው ያጋጠመው፡፡ ይሄን ቤት ማኅበሩ በ1997 ዓ.ም. ከቀበሌ ሲረከብ በርካታ አባወራዎች ነበሩበት፣ ቤቱ በዚህ ልክ ሳይሆን ውስጡ፣ በረንዳውና ግቢው በሙሉ ተዳክሞ የነበረ ሲሆን ከቀበሌው ጋር ውለታ በመፈጸም፣ ነዋሪዎቹም ለሚሄዱበት ካሳ ከፍሎ ነው የተረከበው፡፡ ከኔዘርላንድስ ኤምባሲ ገንዘብ አፈላልጎ ቅርስነቱ እንደተጠበቀ አድሶ ነው የገባበት፡፡ በ2008 ዓ.ም. ዳግም አድሶታል፡፡ አሁን የሆነው ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቱ ይገባኛል ብሎ ነው የጠየቀው፡፡ የክፍለ ከተማው ሰዎች በቅርስ ባለአደራው ይዞታ ላይ በ2006 ዓ.ም. ለኪራይ ቤቶች ካርታ ሠርተውለታል፡፡ ወድቆ የነበረን ቤት በቀበሌው እጅ የነበረን ቤት አሁን ደርሶ ካርታ አሠርቻለሁ ብሎ ማለት ምን ማለት ነው? በጣም በትልቁ የሚጣረስ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ቀበሌው ሲሰጠን ክፍለ ከተማው አያውቅም ማለት አይቻልም፡፡ ካርታው ሲሰጥ እኛ ማወቅ ነበረብን፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ካርታ አለው ብሎ መላክ በምን አግባብ ነው? ለማኅበሩ ትልቅ አጋር እየሆኑ ያሉ ድርጅቶች አሉ፡፡ ቤቶች ኮርፖሬሽን እንደነሱ መደገፍ ይገባው ነበር፡፡ እኛ ስለ ወይራ፣ ኮሶ፣ ዝግባ፣ ዋንዛ፣ ስለ ብሳና ነው የምናወራው፡፡ እነዚህ አገር በቀል ዛፎች መጥፋት የለባቸውም፣ የእኛ መገለጫ ናቸው፡፡ ይሄ ሊያማቸው ይገባ ነበር፡፡ ለዚህ ተቋም ሌላ ቤት እንጨምርልህ ይላሉ ብዬ ነበር የማስበው፡፡ ነገሩ ግን አልሆነም፡፡ ይህ ማኅበር ግለሰቦች አባል ሆነው በወር አሥር ወይም ሃያ ብር እየከፈሉ፣ ያን ሰብስቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፡፡ ቤቱ አሁን እየሰጠበት ካለው በተጨማሪ የጋለሪና የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲሰጥበት እየተሠራ ነው፡፡ ተማሪዎች መጥተው የሚያነቡበት፣ ስለ ቅርስ፣ ስለተፈጥሮ ምንነት የሚገነዘቡበት ማዕከል ይሆናል፡፡ የራስ ከበደ መንገሻ ቤት በ1882 ዓ.ም. የታነፀ ቤት ነው፡፡ የኪነ ሕንፃው እሴት እያንዳንዱ ነገር ቅርስ ነው ብሎ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በወጣው መሥፈርት ከአንድም ሦስቴ ቅርስ ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ ይህን ቅርስ ቅርስን የሚጠብቁ አካላት ናቸው ማስተዳደር ያለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡– ማኅበሩ በጉዞው ያጋጠመው ተግዳሮት እንዴት ይገለጻል?

አቶ መቆያ፡- ቅርስ ባለ አደራ በየወቅቱ የመንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ለውጥ ሲፈጠር ቅርሶች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና፣ ማኅበሩን ሁሌ እንዳቆሰለው ነው፡፡ ግን ከመጮህ ሕዝብን ከመቀስቀስ ወደ ኋላ አላለም፡፡ የለገሀር ባቡር ጣቢያ ሕንፃ ሊፈርስ ሲል ሲምፖዚየም በማዘጋጀት ከፍተኛ አመራሮችን በመጋበዝ የመታደግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ጣይቱ ሆቴል ሲሸጥና ሲታደሰ ቅርሶቹን በጠበቀ መልኩ መታደስ አለባቸው ብሎ ጣልቃ በመግባት የገዛው አካል ውለታ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በድሬዳዋ ቅርንጫፍ ቢሮ ስላለን በዚያ ያሉ ቅርሶች ተመዝግበው እንዲጠበቁ ተደርጓል፡፡ የልጅ ኢያሱ ቤት ፈርሶ ለሌላ አገልግሎት ሊውል ሲል በማዳን ለከተማው ኅብረተሰብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቅርሶችን ለመታደግ ከመከራከር፣ ከመሟገት አላፈገፈገም፡፡ አልፎም እስከ ፍርድ ቤት፣ ሰበር ደርሶ ቅርሶች እንዳይፈርሱ ያስቆማቸውም አሉ፡፡ ነገር ግን በዕቅዱ ልክ ሄዷል ወይ?  ብንል ብዙ ነገሮች ይቀራሉ፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶቹ የፖለቲካ ውሳኔ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ የግንዛቤ ጉዳይም ይነሳል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በእንጦጦ ፓርክ ያከናወናቸው ተግባራት እንዴት ይገለጻሉ?

አቶ መቆያ ፡- የቅርስ ባለአደራ ማኅበር  ከተቋቋመ በኋላ በመጀመርያ ያደረገው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእንጦጦን 1,300 ሔክታር ቦታ መረከብ ነው፡፡ በከፍተኛማው ቦታ ከባሕር ጠለል 3,000 ሜትር ላይ የሚገኘውን ቦታ በአገር በቀል ዛፎች የመሸፈን ሥራውን ነው የጀመረው፡፡ ቦታው ቀደም ሲል ባሕር ዛፍ የለማበት ስለነበርና ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ቦታውን እያደረቀ፣ የከርሰ ምድር ውኃ እያጠፋ ስለሄደ ሥነ ምኅዳሩንም ስላዛባ ያን በመቀነስ፣ በአገር በቀል ዛፎች እንዲሸፈን ለማድረግ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡

በአካባቢው የተደረገው አንደኛ በአራት ሔክታር ላይ የችግኝ ጣቢያ በመሥራት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ችግኞች ፈልተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ማኅበሩ ትልቁ የሠራው ሥራ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለኢትዮጵያ ሚሌኒየምን ጨምሮ አሠራጭቷል፡፡ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይና በኦሮሚያ በሚገኙ 52 ትምህርት ቤቶች አገር በቀል ዛፍን የማሳደግና የመንከባከብ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በአዲስ አበባ ባሉ ትምህርት ቤቶች ያኔ የተከልናቸው የዝግባ፣ የኮሶ፣ ሾላ ዝርያዎች አሁን ደግሞ ከነርሱ ዘር እየወሰድን ነው፡፡

ሁለተኛም በእንጦጦ አካባቢ ዛሬ ከዓመት እስከ ዓመት የሚዘልቁ በርካታ ምንጮች እንደገና እንዲያገግሙ ሆነው ኅብረተሰቡ ለተለያዩ አገልግሎቶች እየተጠቀመባቸው ናቸው፡፡ ከኅብረተሰቡም አልፎ መንግሥት በአካባቢው ላይ ቦኖዎችን በመትከል ውኃ እያሠራጨ ነው፡፡

በማኅበሩ አማካይነት በአዕዋፋት፣ በዕፀዋትና በብርቅዬ እንስሳት ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ ከዚያ ባለፈ ብዙ ሰው የምኒልክ ድኩላን ባሌ ሄጄ ማየት አለብኝ ብሎ ነው የሚያስበው እዚህ ቅርስ ባለአደራ ያለማው ቦታ ገብቶ ሦስት አራት የምኒልክ ድኩላን ማየት ይችላል፡፡ ይህም ውጤት ያገኘንበት ሥራ ነው፡፡ ሌላው ሥራችን ከትምህርት ቤቶችና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ችግኝ ተከላ ይካሄዳል፡፡ ተማሪዎች አገር በቀል ዛፍ ምንድነው? የሚለውን የሚረዱበት አጋጣሚ ነው፡፡

ማኅበሩ ብቻውን አይደለም፡፡ አባላቱም፣ ባንኮች፣ መንግሥታዊ ተቋማትና ሌሎችም በእንጦጦ ላይ አሻራቸውን ያኖራሉ፡፡ ያም ትኩረት ተሰጥቶት እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡– ተጓዳኝ ሥራዎቻችሁስ ከምን ላይ ናቸው?

አቶ መቆያ ፡- ከዚህ በፊት አምስት ሺሕ ያህል የአፕል ተክሎች ነበሩን፡፡ ተለቅሞ መሸጥ የተጀመረ፣ የንብ ማነብና የቀርከሃ ሥራዎችም ነበሩን፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ በ2008 እና 2009 ዓ.ም. ተፈጥሮ የነበረው ያለመረጋጋትና የድንበር ጉዳይ ሦስት ሚሊዮን ችግኝ ያፈላበት የችግኝ ጣቢያ ወድሞበታል፡፡  አንድ የለማ ችግኝ ጣቢያ ከዚያ  ለማድረስ በጣም ከባድ ነው፡፡ በመጀመርያው የችግኝ ጣቢያ ትልልቅ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ስለሆነ መውደሙ አሳዝኗቸዋል፡፡ እነሱም፣ እኛም እንዳዘንን እንዳንቀር እየሠራን ነው፡፡ ቅርስ ባለ አደራ በጣም የተጎዳበት ቢኖር ያ ዘመን ነው፡፡ አንደኛው ቦታውም ተወስዷል፡፡ የንብ ማነቢያ ቀፎው፣ የቀርከሃው ሥራ ሁሉ እንዳለ ወድሞበታል፡፡  የአካባቢው ኅብረተሰብ የሥራ ዕድልን ጨምሮ በምርቶቹ ተጠቃሚ ነበር፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ይጠቀሙ የነበሩት የተፈናቀሉበት፣ ማኅበሩ ብቻ ሳይሆን በሥሩ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሥራቸውን ያጡበት ነው፡፡ ነገር ግን ያን ቦታ የማስመለሱ ሒደት በጣም ፈታኝ ሆኗል፡፡ ቦታውን የመቀራመት ነገር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡፡- ማኅበሩ እስካሁን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አለማግኘቱ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ መፍትሔ አልተገኘለትም?

አቶ መቆያ ፡- የእንጦጦው ቦታ ከከተማ አስተዳደሩ ተለክቶ ቢሰጠንም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን እስካሁን አላገኘንም፡፡ በተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም፣ በእኛ አገር ሁኔታ ሰዎች ሲቀየሩ ነገሩ እንደ አዲስ ነው የሚጀመሩት፡፡ ከዜሮ መጀመሩ ደግሞ ፈተና ነው የሆነብን፡፡ ሌላው አሁን ያለው የድንበር ጉዳይ ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡   የድንበር ክለላው ተሠርቶ እንዲሰጠንና የደን አስተዳደር (ፎረስት ማኔጅመንት) ለማሠራት ከጨረስን በኋላ አሁን የተፈጠረው የድንበር ጉዳይ መጣ፡፡ ከተቋሞች የተሰጠን ምላሽ የድንበር ጉዳዩ ይጠናቀቅና ታቀርባላችሁ የሚል ነው፡፡ አሁንም ተስፋ አልቆረጥንም፡፡ የደን አስተዳደርን በተመለከተ እየተሠራ ያለው ሥራ አንደኛ በመንግሥት የሚደገፍ ሁለተኛ እንደ አገር አስፈላጊም ነው፡፡

ሪፖርተር፡፡- ለተፈጥሮ ቅርስ ባለውለታ ለሆኑ የ‹‹ሜሞሪያል ጋርደን›› (የመታሰቢያ ዐፀድ) የማቋቋም ሐሳባችሁ ከምን ደረሰ?

አቶ መቆያ ፡- በውጭው ዓለም ‹‹ሜሞሪያል ጋርደን›› (የመታሰቢያ ዐፀድ) እየተባለ የሚቀመጠው ዓይነት በእንጦጦም ለመሥራት ፕላን ተደርጎ እየተሄደበት ነው፡፡ ሜሞሪያል ጋርደኑ ሲሠራ ቦታዎች ይመረጣሉ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድና መናፈሻ ይኖራቸዋል፡፡ መዝናኛ፣ ሰዎች የጥሞና ጊዜ የሚወስዱበት ይሆናል፡፡ የመጀመርያው ትኩረት የቅርስ ባለውለታዎችን ለማሰብ ነው፡፡ ያንን ቦታ ለዚህ ያበቁት እነሱ ናቸውና፡፡ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በነበሩበት ጊዜ ትልቅ ሥራ ነው የሠሩት፡፡ ፕሬዚዳንቱ የተከሏቸው ዛፎች እስካሁን በእንጦጦ ጫካ ሪፖርተር፡ ማኅበሩ በሚያስተዳድረው ቦታ ውስጥ በስማቸው አሉ፡፡ ስለዚህ የነዚህ ባለውለታዎች መታሰቢያዎችን ማቆም ትልቅ ነገር ነው፡፡ በሦስት አራት ሰዎች የተጀመረው መታሰቢያቱ እየሰፋ የሚሄድ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የምናመሠግነው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ባለሙያዎችን ተማሪዎችን መድቦልን ሄደው ቦታ አይተው ነድፈዋል፡፡ አሁን የኛን ምላሽ ነው የሚጠብቁት፡፡ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ድንበሩ ሲለይልን ሥራውን የምንቀጥል ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡፡- ማኅበሩ አባላትን ከማሰባሰብ ባለፈ በተለይ ከቅርስ ጋር ተያያዥ ሥራ ካላቸው ተቋማት ጋር ለመሥራት ምን አቅዷል?

አቶ መቆያ ፡-  ቅርሶች ትልቅ ድምፅ እንዲያገኙ እንደ ሔሪቴጅ ዎች ካሉ ተቋማት፣ ከግለሰቦችና ጋለሪ ካላቸውም ጋር በቅንጅት ለመሥራት አቅደናል፡፡ ከዚያ ባለፈ አባልነቱ የግለሰብ፣ የተማሪ፣ የቤተሰብና የዕድሜ ልክ አለ፡፡ በተለይ በ2014 በፓርላማ ያሉትን ሰዎች ጭምር አባል ያደረግንበት፣ በችግኝ ተከላ ፕሮግራማችንም ያሳተፍንበትና ተባባሪነታቸውን ያሳዩበት ነበር፡፡ በርካታ ደጋፊዎች አሉን፡፡ ባሳለፍነው ክረምት የባንኮች ሥራ አስፈጻሚዎች ቃል ገብተው የሄዱት ሠራተኞቻቸውን  የቅርስ ባለአደራው አባል እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡ ከሚዲያ ጋርም መሥራት እንፈልጋለን፡፡ ቅርሶች ሲፈርሱ ነው ሚዲያዎች ብዙ ጊዜ ትኩረት የሚሰጡት፡፡ ግን ሳይፈርሱ፣ በተጎዱበት ወቅት ፕሮግራም በማዘጋጀት ውይይት በመፍጠር መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ 316 ቤቶች በቅርስነት እንደተያዙ መረጃ አለ፡፡ ይጣራል ተብሏል፡፡ እነዚህን ቤቶች ምን ያህሉ ሰዎች ያውቃቸዋል፡፡ ሁሉም እንዲያውቅ ባይጠበቅም የሚዲያ ሰውና አመራሩ ማወቅ አለበት፡፡ አመራሩ ታሪኩን ካወቀው ያንን ነገር እንዲፈርስ ለመፈረም፣ ለመወሰን ይቸግረው ይሆናል፡፡ ይታደስ ሲባል በጀት ለመመደብ ብዙ ቅር ላይለው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡– በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ማኅበሩን የሚደግፍ ተቋም አለ፡፡ ምን እየሠራ ነው?

አቶ መቆያ ፡- በእንግሊዝ የሚገኘውን ማኅበር የመሠረቱት እዚህ የነበሩት የቅርስ ባላደራው ሲቋቋም አብረው የነበሩት ሚስተር ማይክል ሰርጀንት ናቸው፡፡ ለእሳቸው ትልቅ ክብር ነው ያለን፡፡ እዚህ በነበሩ ጊዜ ማኅበሩ በብሪቲሽ ካውንስል ቢሮ እንዲሰጠውና በርካታ ሰዎችን አባል በማድረግ ሠርተዋል፡፡ የእንግሊዙ የበጎ አድራጎት ተቋም ትልቅ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ አባላቱ ብዙዎቹ በቁርጠኝነት እየሠሩልን ነው፡፡ ስለሥራችን መጽሔት (ኒውስ ሌተር) በየጊዜው እያዘጋጁ ይልኩልናል፡፡ ያስተዋውቁልናል፡፡ ስለዚህ ቤትና ስለ እንጦጦው ይዞታ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ሄደው ያነጋግራሉ፡፡ አንድ የገጠመን ችግር በርሳቸው ማኅበር በኩል ለማኅበሩ ሥራ የሚውል መኪና በዕርዳታ ቢያስገኙልንም በተጠየቅነው ከፍተኛ ቀረጥ ምክንያት መረከብ አልቻልንም፡፡ የእኛ አገር ሕግ እስርስር ያለ ነው፡፡ እስካሁን እየታገልን ነው፡፡ እነሱ መኪና ሰጥተውን እንደገና ቀረጥ ክፈሉ ማለት በጣም ከባድ ነው፡፡ የኛ አገር ፖሊሲ አንዳንድ ነገሮች ላይ ተወስኗል ነው የሚባለው፤ ማገናዘብ የሚባል ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡– የማኅበሩ የገቢ ምንጭ ምንድነው?

አቶ መቆያ፡- የመጀመርያ ዓላማው በርካታ አባላትን በማፍራት፣ ገቢውን ማጠናከር ነው፡፡ አባላትን በተመለከተ የግለሰብም፣ የድርጅትም አሉን፤ የቤተሰብ አባላት የዕድሜ ልክ እነ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ አሉን፡፡ ሌላው ገቢያችን በእንጦጦ ከሚሠሩ ሥራዎች የሚገኝው ነው፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ የድርጅት አባሎቻችን የተሠራውን ሥራ ካዩ በኋላ እባካችሁ የምንከፍለውን ከፍ አድርጉ ብለው ጠይቀውን ከፍ አድርገናል፡፡ ከዚያ በተረፈ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እያዘጋጀን ፈንዶች እናገኛለን፡፡ እስካሁን ከነበርንበት በዚህ ዓመት ከፍ ያለ የፕሮጀክት ሥራ ተሠርቶ ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከፕሮጀክት ባሻገር በዋናነት አባላትን በማሰባሰብ ከገቢ አንፃር ብዙ ሊሠራ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡– በሥራችሁ ላይ ተግዳሮቶች እያጋጠማችሁ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት ምን ማድረግ አለበት?

አቶ መቆያ፡- መንግሥት ቅርስን በተመለከተ ያወጣው አዋጅ፣ እንዲሁም መመርያ አለ፡፡ ያንን ተከትሎ ሄዶ ይሄ ቅርስ ነው ብሎ ከመዘገበ በኋላ ቅርሱን ላለማፍረስ እስከመጨረሻው ጥግ መሄድ አለበት፡፡ ለግንባታ ቅርስ የሆነውን ማፍረስ ነው የሚቀለው ወይስ ሌላ ቦታ መፈለግ? ይሄ አንዱ ነው፡፡ ቅርሶች ዕጣ ፈንታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መንግሥት ዕውቅና ለሰጠው የቅርስ አዋጅ ተገዥ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት በዚህ ጉዳይ እንዲያተኩር አስፈላጊ ድጋፍም እንዲያደርግ ይጠበቅበታል፡፡ ቱሪዝም ስንል መሠረቶቹ ቅርሶች ናቸው፡፡ ተደራሽ እንዲሆኑ መደረግ አለበት፡፡  ቅርሶችን ኔትወርክ በማድረግ ለቱሪስቶች ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ አንድን ቦታ ሲጎበኝ ብዙ ነገር እንዲያይ መመቻቸት አለበት፡፡ ከተመቻቸለት ሁለት ሦስት ቀን ሊጨምር ይችላል፡፡ ከብዙ አንፃር ገቢ ሊገኝበት ኅብረተሰቡም ተጠቃሚ ይሆንበታል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች