በአበበ ፍቅር
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ትምህርታቸውን በሚያጠናቅቁበት ወቅት ልዩ የሚያደርጋቸውን ሱፍ ከነከረባቱ፣ ጥቁር ጋዋን ከነመነሳንሱ ደፍተው ከወላጆቻቸውና ከጓደኞቻቸው እንዲሁም ከቅርብ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን መመረቃቸው ነው፡፡
ነገር ግን ወቅቱ በፈጠረው የኑሮ ውድነት፣ የሱፍም ሆነ የማንኛውም ልብስ ዋጋ አልቀመስ ብሏል፡፡
የችግሩ ሰለባ ከሆኑ ተማሪዎች መካከል ብሩክ አባተ አንዱ ነው፡፡ ብሩክ የመመረቂያ ወጪን ሲያስበው ከ15 ሺሕ ብር ያላነሰ እንደሚጠይቀው ተናግሯል፡፡
ካሉት ወጪዎች ደግሞ ከፍተኛውን ዋጋ የሚወስደው በምርቃት ወቅት የሚለበሰው ሱፍ እንደሆነ ሳይናገር አላፈም፡፡ በአሁኑ ወቅትም ብሩክ ባለበት አካባቢ የሱፍ ወቅታዊ ዋጋው ከአምስት እስከ ሰባት ሺሕ ብር እንደሚፈጅ ይናገራል፡፡ ከሱፍ ጋር አብረው የሚለበሱ እንደ ጫማና ሸሚዝ ሲጨመሩበት ወደ ዘጠኝና አሥር ሺሕ ብር ገደማ ገንዘብ አስፈላጊ ነው ይላል፡፡
ከዚህ ባሻገር የመጽሔት፣ የፎቶና ሌሎች ወጪዎች ሲጨመሩበት እንደ ምኞቱ ለመመረቅ አዳጋች እንደሆነበት እንዲሁም ከጓደኞቹ ጋር እኩል ለመደሰት አቅሙ ስለማይፈቅድ ‹‹እንደ ነገሩ በማድረግ›› ለመመረቅ ማሰቡን ተናግሯል፡፡
ያለባቸውን ችግር በመደበቅ ወይም ቤተሰብን ከአቅም በላይ በማስቸገር በማሰብ ካልሆነ በቀር በዚህ ወቅት ሙሉ ወጪን አሟልተው የሚመረቁ ተማሪዎች በጣም ጥቂት እንደሆኑ የሚናገረው ተማሪ ብሩክ በርካታ ዓመታት በትምህርት ላይ ያሳለፈ ተማሪ በመጨረሻ በገንዘብ እጥረት በደስታ አለመመረቅ በእጅጉ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው ይላል፡፡
በዚህም ተማሪዎች ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ለፍተው ተምረው ቢያንስ በመውጫ ቀናቸው ከክፍል ጓደኞቻቸው ጋር እኩል ለብሰው ለመመረቅ የሚቸገሩ መኖራቸውን ያክላል፡፡
የመመረቂያ ሱፍ በማጣት ከጓደኞቻቸው ተለይተው ለራሳቸው ተደብቀው የሚያሳልፉ ተማሪዎች መኖራቸውን በመጥቀስ፣ የተማሪዎቹን ችግር በትንሹም ቢሆን ቀለል ያደርጋል ያለውን መፍትሔ ማቅረቡን ደግሞ ዮሐንስ አበበ ይናገራል፡፡
ዮሐንስ መደበኛ ሥራው ፕሮዳክሽን ቢሆንም፣ ከሥራው ጎን ለጎን ‹‹ለወንድሜ ምረቃ እኔ አለሁለት፤›› በማለት የተለያዩ ሱፎችን ከተለያዩ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች በማሰባሰብ፣ በማፅዳትና የሰፋውን በማስጠበብና በሱፍ መመረቅ ለሚፈልጉ፣ ነገር ግን ሱፍ ለመግዛት አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት የሱፍ ዋጋ ውድ በመሆኑና ገዝተው ለመልበስ የማይችሉ ብዙ ተማሪዎች በመኖራቸው እነሱን የምችለውን ያህል ባግዛቸው የሚል ሐሳብ ይዤ ነው የተነሳሁት፤›› ይላል ወጣት ዮሐንስ፡፡
ለሐሳቡ መነሻ ደግሞ ከአንድ ጊዜ በላይ ለብሶ ሳጥን ውስጥ ያስቀመጣቸው ወደ አምስት የሚሆኑ ሙሉ ልብሶች እንደሆኑ ተናግሯል፡፡
‹‹ብዙ ጊዜ የሱፍ ለባሽ አይደለሁም፡፡ ስለዚህ የማልለብሰው ልብስ ቤት ውስጥ ከሚቀመጥ ለተቸገሩ ተመራቂ ተማሪዎች ልሰጥ በማለት ነው የራሴን ከመስጠት አልፌ የሌሎችን እንዲሰጡ እየተናገርኩ ያለሁት፤›› ብሏል፡፡
ሌሎችም እንደ እኔ አንድ ጊዜ ተጠቅመው አይተዋቸው የማያውቁ ሱፎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለው ዩሐንስ፣ የተቀመጡ ልብሶች በሌሎች ዘንድ በጣም ተፈላጊና ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡ እንደሚሆኑ ገልጿል፡፡
ልብሶቹ በባህሪያቸው አንድ ጊዜ ተለብሰው የሚቀመጡ በመሆናቸው በብዙዎች ቤት ይኖራሉ ብሎ በመነሳትና ሐሳቡንም በማኅበራዊ ሚዲያ በማጋራት የብዙዎች የሚያበረታታ ስለነበር ልብሶቹን ማሰባሰብ መጀመሩን ገልጿል፡፡
ሐሳቡን በማኅበራዊ ሚዲያ ካጋራ በኋላ በርካታ ሰዎች እየደወሉ መጥተህ ውሰድ እያሉት ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ቢሮ ድረስ በማምጣት እየሰጡት መሆኑን ገልጿል፡፡ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ልብሱን የሚፈልጉ ነገር ግን ለመግዛት አቅም የሌላቸው ተማሪዎች እየደወሉ እየተመዘገቡ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
በዚህ ዓመት ተመራቂ መሆናቸውን የሚያሳይ ማንኛውንም የትምህርት ማስረጃ በማሳየት እየወሰዱ እንደሆነ ወጣት ዮሐንስ አስረድቷል፡፡
መግዛት የሚችሉ ተማሪዎች ቢመጡ በምን መለየት እንደሚቻል ወጣቱ ሲናገር፣ ‹‹ሥራችን ታማኝነትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በታማኝነት ከሰዎች እንቀበላለን፣ በታማኝነት ለመጡ ሁሉ በእምነት ያለውን እንሰጣለን፤›› ሲል ነው ያስረዳው፡፡
ሰባት ዓመት ሙሉ ሕክምና ተምረው ‹‹መመረቂያ ሱፍ አጣን›› እያሉ የመጡ ተማሪዎች መኖራቸውን የተናገረው ወጣት ዮሐንስ፣ እነዚህን ተማሪዎች አለንላችሁ ብንላቸው በጣም ጥሩ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
በዚህ በጎ ተግባርም ከ20 በላይ ሱፎችን መሰብሰብ እንደቻለ የተናገረው ወጣቱ፣ ሱፉን የሚፈልጉ ተማሪዎችም ቁጥር ከ30 በላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የማሰባሰብና የመስጠት ሥራውም እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ እንደሚቀጥልና የተገኘውን ለሚመጡ ተማሪዎች እንደሚያስረክብ ገልጿል፡፡
ምናልባት ብር መርዳት የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ በጥሬ ገንዘብ መቀበል እንደማይችል፣ ነገር ግን መስጠት ያሰቡትን ገንዘብ ወደ ሱፍ ቀይረው ቢያመጡት የተሻለ እንደሚሆን ተናግሯል፡፡