ለሰላሳ ዓመታት የተገለገለበተን የቅርስ ቤት እንዲለቅ መገደዱንና ዋና መሥሪያ ቤቱ መታሸጉን፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ ለሪፖርተር እንዳስረዳው፣ ለ30 ዓመታት የተገለገለበትን ዋና መሥሪያ ቤቱን እንዲለቅ ያስገደደው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ነው፡፡
ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት የፀጥታ አካላት ዋና መሥሪያ ቤቱን እንዳሸጉት፣ እስከ ረቡዕ ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ንብረቱን ካላወጣ መንግሥት ይወርሰዋል የሚል ዛቻ እንደደረሰበት የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መቆያ ማሞ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በመጀመሪያ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲለቁ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ደብዳቤ እንደጻፈላቸው፣ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በተደጋጋሚ ውይይት አድርገው እንደነበር፣ በውይይቱ መሠረት ለችግሩ መፍትሔ ይሰጣል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው እንጂ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለቃችሁ ውጡ እንባላለን ብለው እንዳላሰቡ አስረድተዋል፡፡
ያሉበትን ቢሮ ለምን ልቀቁ እንደተባሉ ማብራሪያ እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ምንም ምክንያት የለም፣ በኪራይም ከሆነ ወደ መከራየት መግባት እንደምንችል አማራጭ አስቀምጠናል፡፡ እንድንለቅ በደብዳቤ ከተገለጸልን ውጪ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አላወቅንም፤›› ብለዋል፡፡
ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በደረሳቸው ደብዳቤ መሠረት የቅርስ ጉዳይ ለሚመለከተቻው አካላት ሁሉ ሁኔታውን አሳውቀው እንደነበር፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋርም በጉዳዩ ላይ በተደጋጋሚ ውይይት እንደተደረገ፣ ይህ በእንዲህ እያለ ሰኞ ሐምሌ 10 ቀን በተጻፈ ደብዳቤ መሥሪያ ቤቱን እንዲለቁ መጠየቃቸውን አቶ መቆያ አስረድተዋል፡፡
የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት መታሸጉን ሪፖርተር በቦታው በመገኘት ያረጋገጠ ሲሆን፣ ማኅበሩ የቅርስ ቤቱን እንዲለቅ መባሉን የኮርፖሬሽኑ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡
በቅርስ ጥበቃ ለሰላሳ ዓመታት ሲሠራበት የቆየውና ከ100 ዓመት በላይ በማስቆጠር ራሱ ቅርስ የሆነው ዋና መሥሪያ ቤቱ ይፈርሳል የሚል ሥጋት እንዳደረባቸው፣ ድርጊቱ በቅርስ ዙሪያ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማጨለም ተብሎ የታሰበ ነው ብለው እንደሚያምኑም ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ ግቢውን ከተረከበ በኋላ እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው ዕድሳት በወቅቱ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ብር ፈሰስ ማድረጉን ያስረዱት አቶ መቆያ፣ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽ ኃላፊ አቶ አማኑኤል ይርዳው፣ ‹‹ጉዳዩን አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም አጣርተው እንደሚገልጹ ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ ለአካባቢ ጥበቃ ተግባር በእንጦጦ 1,300 ሔክታር መሬት ላይ ከ28 ዓመታት በፊት ጀምሮ የተፈጥሮ ፓርክ መሥርቶ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያገለገለ እንደሚገኝ፣ በጦርነት ጉዳት የደረሰበት የደሴ ሙዚየምን መልሶ ለመጠገን ፕሮጀክት ቀርፆ እየሠራ እንደሆነ፣ ዋና ሥራውን የሚያቀላጥፍበት ዋና ጽሕፈት ቤቱ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን በ1890 ዓ.ም. እንደተገነባና የአዲስ አበባ ጥንታዊ ቅርስ የራስ ከበደ መንገሻ ቤት እንደነበር ተነግሯል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ‹‹ጥንታዊ ቤቱ ለማኅበሩ መገልገያነት ከመንግሥት ተሰጥቶት የተቋቋመበትን ዓላማ በአግባቡ ሲያከናውን ቆይቷል፤›› ሲል ማኅበሩ ለሪፖርተር በላከው ጽሑፍ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር በ1985 ዓ.ም. የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነና በተለያዩ ከተሞች ቅርንጫፎች ያሉት አገር በቀል ድርጅት መሆኑን፣ ለሦስት አሥርት ዓመታት ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ሲሠራ መቆየቱን አክሏል፡፡