Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
Uncategorized “ሰው ልማትን ማግኘት መብቱ ነው የሚለው ዕሳቤ እንዳይጠፋ በሰፊው አስተዋጽኦ አድርገናል”

 “ሰው ልማትን ማግኘት መብቱ ነው የሚለው ዕሳቤ እንዳይጠፋ በሰፊው አስተዋጽኦ አድርገናል”

ቀን:

ወ/ሮ ሰላማዊት መንክር፣ የሲቪል ማኅበራት ድጋፍ ፕሮግራም ቡድን መሪ

በብሪቲሽ ካውንስል በሚመራ የአስፈፃሚዎች ጥምረት አማካይነት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የሲቪል ማኅበራት ድጋፍ ፕሮግራም ለሁለት ተከታታይ ምዕራፍ ተደርጓል፡፡ እኤአ ከ2011 ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የድጋፍ ፕሮግራም የተመዘገቡ ውጤቶች ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጡ ይነገራል፡፡ ይህ በሁለት ምዕራፍ የተተገበረው የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትን የመደገፍና የማፅናት ፕሮግራም ሁለተኛው ምዕራፍ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ለመሆኑ ይህ የድጋፍ ፕሮግራም ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተጨባጭ የመጣው ለውጥ ምንድን ነው? ቀጣይነቱስ ምን ይመስላል? በሚለው ዙሪያ በአራት (FCDO, Irish Aid, Sweden, Nowray) የሲቪል ማኅበራት ድጋፍ ፕሮግራም/CSSP-2/ ቡድን መሪ ከሆኑት ወ/ሮ ሰላማዊት መንክር ጋር የተደረገ ቆይታ፡፡

ግንቦት 22 እና 23 ቀን 2015 ዓ.ም የሲቪልማኅበረሰብየድጋፍፕሮግራም 2 (CSSP2)በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ያዘጋጀው ትልቅ ሁነት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሁነቱ ምን ያህል ውጤታማ ነበር? እንዴትስ ገመገማችሁት?

ሰላማዊትባለፈው ወር መገባደጃ የተደረገው ስብሰባ ጥሩ የነበረና በዋናነት ያስፈለገበት ምክንያትም እንደ ሲኤስኤስፒ ዓይነት ፕሮግራሞች እንዲበዙ ነው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጠንካራ ካልሆኑ ፕሮጀክት ብቻ እያስፈጸሙ የሚዘጉ ከሆነ ራሳቸው ድርጅቶቹ የተቋቋሙበት ራዕይና ተልዕኮ አያሳኩም፡፡ እናገለግለዋለን ያሉትንም ሕዝብ በተቀነጨበ ፕሮጀክት ብቻ እየመጡና እየሄዱ የሚፈልጉትን ያህል ውጤትና ለውጥ ማምጣት አይችሉም፡፡ ከመንግሥት ጋር በተለይ ደግሞ ሰብዓዊ መብት ማስከበር፣ መሟገትና ማሳመን ደግሞ የአጭር ጊዜ ሥራ አይደለም፡፡ በጣም የተቀናጀና የተሰናሰለ የማስተማርና የማወያየት የማሳወቅ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ አገሪቱ ያሏትን ሕጎች፣ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ደንቦችና መመርያዎች በየዕርከኑ ላሉ የሥራ ኃላፊዎችና ተሿሚዎች ማሳወቅ በራሱ ጊዜ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ፕሮጀክትን ብቻ መሠረት ያደረገ ድጋፍ ለሲቪል ማኅበረሰቡ ለውጥ ያመጣል ብለን አናስብም፡፡ አቅምን ለማጎልበት ካልተሠራ በስተቀር ውጤቱ ብዙ አመርቂ አይደለም፡፡ አመርቂ የማይሆነው ለሲቪል ማኅበረሰቡና ለሚያገለግለው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የልማት አጋር ጭምር ነው፡፡

በልማት አጋር የሚደገፍ ኢንቨስትመንት የሚጎለብተው አንድ ፕሮጀክት ይዞ መጥቶ አጠናቆ ሄዶ በሌላ ጊዜ እንደዚሁ ሌላ ፕሮጀከት ይዞ ሲመጣ ሳይሆን፣ ወጥነት ባለው መንገድ የያዘውን ፕሮጀክት መተግበር ሲችል ነው፡፡በዚህ ወቅት በዓለም ላይ ያለው ብዙ ቀውስ ነው፡፡ እኛ አገር ያሉ የልማት አጋሮች የምንላቸውና ሲቪል ማኅበረሰቡን የሚደግፉ ድጋፍ ሰጪዎች (Donors) ወጪ ቆጣቢውንና ቀልጣፋ ነገር አለመደገፍ አይችሉም፡፡ባለፈው ወር ያዘጋጀነው ዝግጅት የሲቪል ማኅበረሰብን አቅም መደገፍ ወቅታዊ ነው ያስፈልጋል፣ ሁለተኛ ደግሞ ውጤትም ያመጣል ለዚያ ‹‹አድቮኬሲ›› ሥራ ነው የሠራነው፡፡የእኛ ፕሮጀክት በጥቂት ወራት ውስጥ ያልቃል፡፡ ግን ሲያልቅ እኛን የሚደግፉ አካላት ስለቀጣይ ነገር እንዲያስቡ ሌሎችም ተቋማትም ድጋፍ ማድረግ ሲያስቡ የሲቪል ማኅበራትን አቅምና የመሥሪያ ምኅዳሩ መስፋት ላይ ብዙ መሥራት አለባቸው የሚል የማግባባት ሥራ ለመሥራት ሞክረናል፡፡የማግባባት ወይም የመወትወት ጥረታችን በጣም ውጤታማ ነው ብለን ገምግመናል፡፡ 300 ተሳታፊዎችን ጠርተን መዝጊያውም ላይ በጣም ጥቂት ቁልፍ ከሚባሉ ኃላፊዎች በስተቀር ሙሉ ሆኖ የተጠናቀቀና ተሳትፎ ጥሩ ነበር፡፡ የፓናል ውይይቱ ጥሩ ነበር፣ የሲቪል ማኅበራት የገበያ ቦታ ብለን ያዘጋጀነው ሥፍራ ብዙ ገበያተኛ ነበረው፡፡ በአጠቃላይ የሁለቱ ቀናት ቆይታ ጥሩ ነበር ብለን ገምግመናል፡፡

ፕሮጀክቶቻችሁ በሁለት ምዕራፍ በአሥር ዓመት ተግባራዊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ ከመጀመርያው ምን የተሻለ ውጤት ተገኘበት? ከዚህስ ምን ውጤት አገኘ?

ሰላማዊት፡- የመጀመርያው ምዕራፍ ሲተገበር የነበረው የድሮ ሕግ ነበር፡፡ ስለዚህ ስለ መብት ማውራት የሚቻልበት ጊዜ አልነበረም፡፡ አሁን በሁለተኛው ምዕራፍ የምንሠራቸውን ሥራዎች በዚያን ወቅት በአደባባይ መሥራት አይቻልም ነበር፡፡ለምሳሌ ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች ላይ መድረስ ብለን የምንሰራቸው ብዙዎቹ ሲታዩ በልማት ያልተደረሱ፣በአገልግሎት ያልተደረሱ ክፍሎች ሲባል፣ ጥያቄው መብት ሲሆን የበፊቱ ግን ይሄን የሚከለክል ነበር፡፡ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ መክፈትን እንጂ ስለ ጤናና ትምህርት፣ ስለ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች መብት ማንሳት አይቻልም ነበር፡፡ በወቅቱ ከ500 በላይ የሲቪል ማኅበራትን ደግፈን ብዙ ድርጅቶችን ከመዘጋት ታድገናል፡፡ ከዚያ ውጭ ሰው ልማትን ማግኘት መብቱ ነው የሚለው ዕሳቤ እንዳይጠፋ በጣም በሰፊው አስተዋጽኦ አድርገናል ብለን ነው የምናምነው፡፡ ሁለቱን ምዕራፎች አንድ ላይ በድምር በፕሮጀክት በግራንት  መልክ የወጣው 50 ሺሕ ፓውንድ ይሆናል፡፡አንድ ላይ ድጋፍ የተደረገላቸው 800የሚጠጉ ድርጅቶች በስራቸው በትንሹ ሁለትና ሦስት ሠራተኞች ቀጥረው ከሆነ ያንን ከእነሱ ብዛት ጋር ስናበዛው የሚገኘው ውጤት ብዙ ነው፡፡

የእኛ ፕሮግራም  የሚታወቀው ዓቅምን ግንባታ ላይ ስለሆነ የድርጅቶቹን ዓቅም በማጎልበት የእነዚህን ሁሉ ሰዎች ዓቅም ከመገንባት ባሻገር ለሥራ ፈጠራ ያደረገነው አስተዋፅኦ ጎልህ ነው፡፡

በሌላ በኩል ለፕሮጀክቱ የሚውለው ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ሲገባ ለአገሪቱ የሚያደርገው አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚያ በዘለለ በሚሠራባቸው የትኩረት አካባቢዎች ላይ ትምህርት ቤት መሄድ የቻሉ ልጃገረዶች፣ ወንዶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች ጉዳያቸው የተረሳና የተዘለሉት ሁሉ ታሳቢ እንዲሆኑ በማድረግ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡

ከኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲ ፎረም ምሥረታ ጀምሮ ፎረሙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶን እያስተባበረ ጥናት እንዲደረግ፣ የሕግ ክፍተቶቹ ምንድናቸው?  ለአገር ያለው ጉዳት ምንድነው? የሚለውን ጥናት ደግፈናል (ከለውጡ በፊት) ጥናቱ ከተደረገ በኋላ በሕግ ማውጣት ሒደት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የዘርፍ ባለሙያዎችን አካተን  ረቂቅ ሪፖርት ወጥቶ ቀርቦ በካቢኔ ውይይት ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ለውጡ ሲመጣ ብዙ መቀየር የነበረባቸው ሕጎች ሲቀየር የሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ አንደኛው ነው፡፡

ሁለተኛ ምዕራፍ የሲቪል ማኅበራት ድጋፍ ፕሮግራም ሲጀምር የመጀመርያው ሥራችን የሲቪል ማኅበረሰብ ክፍል ላይ የውይይት መድረኮችን ድጋፍ በማድረግ የጀመረ ነው፡፡ የፓርላማ ስሚ በሚደረግበት ጊዜ ብዙ ቅስቀሳዎች ስለተደረገ የተለያዩ ግብዓቶች ተሰጥቶበት እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት ተቋማቱ አቅማቸው እንዲገነባና ራሳቸውን እንዲፈትሹ ከዘርፉ ጋር ያላቸውን መጥፎ ስሜትና አለመተማመንና እንዲለወጥ የቴክኒካል ድጋፍ የውይይት በማድረግ ድጋፍ አድርገንላቸዋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ቦርድ ሲቋቋም እስካሁን የወጡ 13 መመርያዎች እንዲወጡ አስተዋጽኦ ያደረጉ ቢኖሩም፣ ሰፊ ውይይት ተደርጎ እንዲፀድቅ ያደረገው የእኛ ድጋፍ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የፌደራል እና ክልል ፎረም በሚባለው ሁሉም የመንግስት መሥሪያ ቤቶች በተሰጣቸው ተልዕኮ ሲንቀሳቀሱ አብረው ካለመስራታቸው የተነሳ አንዳንዴ አለመናበብ ይፈጠራል፤ አንዱ የሚለው ሌላው ከሚለው ጋር ይፋለሳል፡፡ ይህ ለሲቪል ማኅበረሰብ ምኅዳሩ መጥበብ ምክንያት ስለሚሆን የፌዴራልም ሆነ የክልል ተቋማት አንድ ላይ ቀርበው የሚነጋገሩበትን መድረክ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ  ይሄ ነገር ለሰባት ጊዜ ተደርጓል፡፡ በተለይም የወል ተግዳሮቶች በሆኑትጉዳዮች ለምሳሌ ከመንገድ ትራንስፖርት ሕግ፣ ከገቢ ሕግ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከሚያወጣቸው ሕጎች ጋር የተያያዙ ችግሮች በየክልሉ ይነሳሉ፡፡ የዘርፉ መሥሪያ ቤቶች አለመናበብ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፕሮጀክት እስከመዝጋት ድረስ እንዲሄዱ ስለሚያደርጋቸው ይህንን ተወያይተውበት በሚይዙት ነጥብ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከኢምግሬሽን ጀምሮ የሚመለከታቸው ተቋማት መልስ ለመስጠት ቀርበዋል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክታችን ካደረግነው አስተዋጽኦ መታየት አለበት ብዬ የማስበው ፕሮጀክቱ እንደተጀመረ ሕጉ ተቀየረ፣ የፖለቲካው ዕሳቤው ተቀይሮ አስፈጻሚ አካላት የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትን “እነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች” ማለት ትተው‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትን የልማት አጋር ናቸው›› ወደሚል ዕሳቤ የመጡበት ወቅት ነበር፡፡ ይህንን ወደ ክልሎች አውርደን ለመስራት ስንቀሳቀስ የኮቪድ ወረርሽኝ መጣ፡፡ በወረርሽኙ ብዙ ፕሮጀክቶች ሥራ ሲያቆሙ ሲኤስኤስፒ ግን አልቆመም፡፡ ይህም የሆነው የመፍትሔ አማራጮችን በፍጥነት በመውሰዳችን ነው፡፡ በወቅቱ በሁሉም ክልሎች የሚሠራ 17 ሚሊዮን ብር የሚሆን የኮቪድ ድጋፍ ሰጥተናል፡፡ ይኼንን ተከትሎ ደግሞ የሰሜኑ ጦርነት ሲመጣ ያ ደግሞ እኛ የምንሠራውን ሥራ ወደ ኋላ የሚመልስ ነበር፡ፕሮጀክቶቻችን ለጊዜው  ቢቆሙም  ዳግም ሲከፈት ከትግራይ በስተቀር አፋርና አማራ ክልል ላይ መሥራት የተቻለውን ሠርተናል፡፡ ነገር ግን የትግራይ ክልል በቆመበት ወቅት ምን ማድረግ እንችላለን? መቼ ሊከፈት ይችላል? ሲከፈት የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ጠንካራ ሆነው ለማኅበረሰባቸው መኖር እንዲችሉ ምን እናድርግ? የሚል ጥናት በየወቅቱ እንሠራ ነበር ለአማራ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉልና ወለጋ አካባቢዎች ጭምር በተመሳሳይ ሰርተናል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በደህናው ቀን ብቻ የሚመጡ አጋፋሪዎች አይደሉም፡፡ በደህናውም ሆነ በመጥፎው ቀን እንደ ሁኔታው ማኅበረሰቡን የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በተለይም አገርበቀሎቹ ማኅበረሰብ ውስጥ ስላሉ አቅም አላቸው፡፡ ግን ገንዘብ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ማገልገል ያለባቸውን ያህል አያገለግሉም፡፡ እኛ ትግራይ ላይ ዳግም ሁኔታዎች መከፈት ሲጀምሩ ለአገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ በማድረግ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ ድርጅት ነን፡፡የግጭት አፈታትና እና የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ አዘጋጅተን፣ ተጨማሪ የትኩረት ከባቢ (Thematic Area) አድርገን በስድስት ቦታዎች ከደቡብ ክልል ኮንሶ፣ በወለጋ አራቱም ዞኖች፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ አማራ፣ አፋርና ትግራይ ላይ ግጭትን ለመቀነስ፣ የተሻለ ሰላምን ለማምጣት እንዲቻል ለ45 የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ወደ 1.8 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ ሰጥተን ሥራ እንዲሠራ አድርገናል፡፡ችግሮች እንዳይፈጠሩ የቅድሚያ ተከላካይ በመሆን በሒደቶቹ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ንብረት እንዳይወድም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማድረግ ይችላሉ፡፡ ግን ይሄን የሚችሉት እነሱ ጠንካራ ሆነው ሲገኙ ነው የሚለውን ማሳየት የቻልን ይመስለኛል፡፡

እናንተ ያላችሁን ተልዕኮ ጨርሳችሁ ስትወጡ የሚኖረው ሁኔታ ምን ሊሆን ይችላል? የደገፋችኋቸው ተቋማት ራሳቸውን ችለው የቆሙ ናቸው? የእናንተስ ፕሮጀክት ሦስተኛ ምዕራፍ ጉዞ አለው? የረጂዎቻችሁንስ እርካታ እንዴት ትመዝኑታላችሁ?

ሰላማዊት፡- ሦስተኛው ምዕራፍ ተብሎ ይሁን በሌላ ስም መምጣት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በተለይም የባለፈው ወር ዝግጅት ምስክርነት የሰጠው ያንን ነው፡፡ አሁን ላይ ድርጀቶች በጣም ጥሩ ሒደት ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩበት የአሥር ዓመታት ፍርኃት ለመውጣት በሚጣጣሩበት ሰዓት ደግሞ ኮቪድ-19 እና የመሳሰሉት ይዘዋቸዋል፡፡እየተለወጡ ቢሆንም በብዙ መደናቅፍ ውስጥ ነው የሆነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በኮቪድና ሌሎች ግጭቶች ምክንያት በሆነው ነገር ሳቢያ ተቋማቱ እየተውተረተሩ ነው፡፡ ሰላም ላይ፣ተደራሽነት ላይ፣ መብትን ጮክ ብሎ ለመናገር እየተውተረተሩ እንደመሆናቸው ድጋፍ ካልተደረገላቸው ይወድቃሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ድጋፍ አድራጊ ተቋማትም ለአሥር ዓመታት ያህል ገንዘብ ፈሰስ አድርገው የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማቱ ወደ ኋላ ሲመለሱ ማየት አይፈልጉም፡፡ እነሱም ይኼን ተረድተው ውይይቶችን ጀምረዋል፡፡ እኔም ሆንኩኝ የምመራው ቡድን ለእኛ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት መቀጠል ብቻ ሳይሆን ብዙ ድጋፍ አድራጊዎች በተበጣጠሰ መልኩ የሚያደርጉትን ድጋፍ በተሰባሰበ ሁኔታና ዘርፉን ወደፊት በሚወስድ መልኩ እንዲያደርጉ ማስተባበር መሥራትን ስለፈለግን ነው፡፡ ሲኤስኤስፒ-3 ወይም ያንን የሚመስል ሌላ ፕሮግራም ይመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡በሲኤስኤስፒ ድጋፍ ውስጥ ራሳቸውን የቻሉና ለውጥ ያሳዩ ድርጅቶች አሉ፤ የድርጅቶቹ የተቋም ዓቅም ግምገማ (Organizational Capacity Assessment) ልክ ከፕሮግራሙ ጋር አብሮ መስራት ሲጀምሩ መሰራት ይጀመራል፡፡በየ ዓመቱም ግምገማው ይሰራል፡፡ይህም ድርጅቶቹ በየ ጊዜው ዕድገታቸው ፈጣን ነው አይደለም የሚለውን ይረዱበታል፡፡  በሲኤስኤስፒ ፈንድ ምክንያት ራሳቸውን ችለው የቆሙና ተጨማሪ ፈንዶችን ያገኙ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ እኛ አሁንም አልጠነከሩም ገና ናቸው የምንላቸውም ራሱ ችግራቸውን ያወቁ ናቸው፡፡ እኛ ቀጥታ ድጋፍ ላደረግንላቸው ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን በፌደራልና በክልል ደረጃ የተመዘገቡ ሌሎች  የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትን የማቀራረብ ድጋፍ እንሰራለን፡፡

ባለፉት ዓመታት በተለይም ከአዋጅ መውጣት ጀምሮ ስለ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ያለው አመለካከት አንፃራዊ በሆነ መንገድ ተለውጧል ይባላል፡፡ እስኪ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት መካከል ያለው መቀራረብ ምን ይመስላል?

ሰላማዊት፡- በመቀራረብ ዙሪያ ከላይ የተገለፁት ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው በጉዳዩ ላይ የሚስተዋል ፈተና አለ፡፡ይኽም ፈተና በሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማቱም፣ በመንግሥትም ውስጥ ያለ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሕግ መቀየሩን የማያውቁ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ. 2019 ላይ ሕጉ መቀየሩን ስላላወቁ ድጋሚ ያልተመዘገቡ ድርጅቶች አሉ፡፡ ስለሆነም ራሱ ሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ላይ ያለው የጠያቂነት መንፈስ ትንተና መሥራት ዘርፉን ማየት ያሻል፡፡ ምኅዳሩ ካልተስተካከለ ለብቻ መሮጥ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ትግሉ ከመንግሥት የተቀየረ ቢሮክራሲ ጋር ሳይሆን የእኔ የሚለውን ነገር ነቅቶ ካልያዘ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትም ጭምር ነው፡፡ ከመንግሥት አንፃር ሲታይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ባለሥልጣን ተቋም መቀየር ከፈለገ እንደሚቻል ቀላሉ ማሳያ ነው ሊባል ይችላል፡፡ የአመራር ቁርጠኝነት ምን  ያህል ድርጅትን እንደሚቀይር ማሳያው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ነው፡፡ በክልሎች ላይ ያሉ የእነሱ “ማንዴትድ ኦፊስ”፣ (የፋይናንስ ዲፓርትመንትና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጎች) የተሻለ ዕሳቤና አስተሳሰብ ይዘው እንዲያገለግሉ ባለሥልጣኑ ብዙ ጥሯል፡፡ እኛም ባለሥልጣኑን በመደገፍ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትም የጉትጎታ ሥራ እንዲሠሩ አድርገናል፡፡ ለውጡ አመርቂ ባይሆንም፣ ገና ብዙ መሠራት ያለበትና የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ ፡፡ ግን ደግሞ በሦስትና አራት ዓመታት ብዙ ነገሮች በችግር ውስጥ ሆኖ መሥራት ተችሏል፡፡ ሲጠቃለል በጣም አበረታች ለውጦች አሉ፡፡ ግን የቆየ ስለሆነ ብዙ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ እውነቱን ለመናገር ሚዲያው ይህን ለመቀየር እየሠራ አይደለም፡፡ሚዲያው አሥር ዓመት ሲቪል ማኅበረሰቡን ለመውቀጥ ያወጣውን ጉልበት ያህል አሁን ላይ በፍፁም እየተጠቀመ አይደለም፡፡ ብዙ ሰው የሚከታተላቸው የቲቪና የሬዲዮ ፕሮግራሞች የአየር ሰዓታቸው ውድ ነው፡፡ በአንፃሩ ሬዲዮ ይሻላል፡፡ ይህንን ማኅበረሰብ ውስጥ ገብቶ የሚሠራ ሥራን ለማሳየት ከሚዲያው ብዙ ተነሳሽነት አላየሁም፡፡ ይሄ መቀየር አለበት፡፡ ሚዲያ ቁልፍ የሆነ ሚና ያለው የሕዝብ ተቋም ነው (የግሉም ሆነ የመንግሥት) ይህንን ለውጥ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ መውሰድ ካስፈለገና ካለብን የሚዲያው ሚና ትልቅ ነው፡፡ ሥራዬ ብለው ወጥተው አጀንዳቸው አድርገው ለጉዳዩ ውትወታ ባያደርጉ እንኳን የአየር ሰዓት ዋጋን ተመጣጣኝና ፍትሃዊ አድርገው በማስተካከል የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ይኼን ሥራ መሥራት እንዲችሉ ቢያደርጉ እነሱም ይህን ለውጥ ማምጣት ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክታችሁ ትግበራ ላይ ካደረጋችሁትና በነጠረ ሁኔታ የምትገልጹት ሥራን ለማሳያነት ብትገልጹልን?

ሰላማዊት፡- ይኼን መግለጽ ለእኔ አስቸጋሪ ነው፡፡ 173 ድርጀቶች ጋራ ላይ ሠርተናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ቢያንስ እያንዳንዳቸው አንድ የተሳካ ታሪክ አላቸው፡፡ ልብሽ ውስጥ የቀረ ከተባልኩ ግን በተለይ የወጣት ሴቶች የመሬት መብት መጠበቁን እጠቅሳለሁ፡፡ የመሬት መብት ሲባል ሁሌ ትልቅ ሴት እንጂ ወጣ ት ሴት አትታሰብም፡፡ አጀንዳም አትሆንም፡፡ ለምን? ገና አላገባችም፣ ማንን እንደምታመጣ አይታወቅም፣ እዚህ መሬት ወስዳ እዚያ ትሄዳለች የሚል የተለያየ የተፋለሰ የማኅበረሰብ አስተሳሰብ ስላለ በዚህ ላይ በኮንሶ በተለያዩ ቦታዎችም ላይ የመጣው ለውጥ ልቤን ከሚያስደስቱት አንደኛው ነው፡፡ ሌላው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ‹‹ትምራን›› የሚያስተባብረውና በአማራ ክልል ደግሞ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) እና  የአማራ ሴቶች ማኅበር ሴቶች በተሳትፎ አመራር ላይ እንዲገቡ (ከሠፈር ዕድር አመራርነት እስከ ሰበካ ጉባዔ፣ ቀበሌ ጽሕፈት ቤትና ላይ የተለያዩ መዋቅሮች) ላይ እንዲገቡና የምርጫ ወቅት ላይ ደግሞ የሴቶችን ቅስቀሳ በመደገፍ ያደረጉ ይገኝበታል፡፡ የአማራ ሴቶች ማኅበር የሚደግፋቸው ቢያንስ 175 አካባቢ ሴቶች በእኛ ፕሮጀክት ምክንያት ወደሆነ ዓይነት አመራር መጥተዋል፡፡ ይኼ ትንሽ ቁጥር ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን መብታቸውን ሊያስከብር የሚችል መብታቸውን የሚያስከብሩ፣ ምን እንደሚሠሩ የሚያውቁ ሴቶች እየበዙ በመጡ ቁጥር 50 በመቶወን የህብረተሰብ ክፍል በመወከል የመሪነት ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ይሄ ከታች ጀምሮ እየተሠራ የመጣና በፍፁም ሊቆም የማይገባው ነው፡፡

ሌላው ለልቤ ቅርብ የሆነና እንደ መጨረሻ ምሳሌ የማነሳው‹‹የወጣቶች ድምፅ›› ብለን የጀመርነው ነው፡፡ ይኼ የወጣቶችን የፖለቲካና ማኅበራዊ እውነት፣ ማንነት ለወጣቶች በሚጠቅም መልኩ እንዲውል ማድረግ ነው፡፡ ወጣቶች በተለይ ባላቸው ብዛት ወንዶችም ሆነ ሴቶች በሥራና በትምህርት ምክንያት ያሉበት ማኅበራዊና ፖለቲካ ሁኔታ ካልተቀየረ ኢትዮጵያ የምንፈልጋትን ዓይነት የሰውን መብት የምታከብር፣ ዜጎቿ ተደስተው የሚኖሩበት መሆን ትችላለች ወይ? የሚለውን ነገር እኔ በግሌ ያሳስበኛል፡፡ ወጣቶች ዕድል ሲያገኙ በጣም ጥሩ ዓቅም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‹‹በወጣቶች ድምፅ›› ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች የሠራነው ሥራ አለ፡፡የመንግሥት ተቋማትን ተጠያቂ ማድረግ ሐዋሳና አዲስ አበባ የወጣቶች ድምፅ እንዲሰማ በተለያዩ ድርጅቶች ላይ ያደረግነው ነገር የሚያስደስተኝና መቀጠል አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ 

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስመልክቶ ያለው ዕድልና ተግዳሮት ምንድነው? በተለይም በሁለተኛው ምዕራፍ የፕሮጀክት ትግበራችሁ የተቋማት አቅም ግንባታ ላይ እንደ መሥራታችሁ ሦስተኛው ምዕራፍ የፕሮጀክት ትግበራ ዕድል ብታገኙ ትኩረታችሁ የሚሆነው ምን ላይ ነው?

ሰላማዊት፡- ዕድሎች ብዬ የምገልጸው ለምሳሌ ሰው ተኮር አገልግሎት መብት ትግበራ ረዥም ጊዜ ከተረሳ በኋላ ድርጀቶች ፕሮጀክቶች ሲቀርፁ ያንን እያሰቡ መሥራታቸው ነው፡፡ ዜጎች ማንኛውም ሥራ መስክ ላይ ይሰማሩ መብታቸው ስለሆነ ነው ያንን የሚያገኙት፡፡ ስለሆነም ያንን ማግኘት አለባቸው በሚል ዕሳቤ ሥራ መጀመሩ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ዜጋው መብቴ ነው ብሎ መጠየቅ እንዲችል አቅም ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ተጠቅሞ በሰላማዊ መንገድ ማኅበራዊ ተግባቦትንና ዴሞክራሲን ሊያመጣ በሚችል መልኩ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በተግዳሮትነት የሚነሳው ነገር በተለይም የድጋፍ ክፍትት (Funding Gap) ከኖረ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ሠራተኞች ይለቃሉ፡፡ ከዚያ አዲስ ክህሎት የሌለው ሠራተኛ ነው የሚቀጥሩት ስለዚህ በዚህ ላይ ዕውቀት ማስገንዘቢያ እስኪሠራ የሚባክን ጊዜ አለ፡፡ በመንግሥት በኩል ያለውን ስገልጽ፣ አሁን ያለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ለአገር ይጠቅማል የሚለው ላይ ከተሠራ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ መሄድ ይችላል፡፡

ለድጋፍ አድራጊ የልማት አጋር ተቋማትም ሆነ ለመንግሥት ማሳየት የምፈልገው አንድ ነገር የተሠራን ሥራን ትቶ ወይም ረስቶ እንደ አዲስ መሥራት ማለት የባከነ ጊዜና ገንዘብ እንዲሆን አድርጎ ማስቀረት ነው፡፡ ግለቱ እንዳለ፣  የጀመርነውን ነገር ዳር እናድርሰው በሚለው ስሜት ከቀጠልን ግን አሁን ያለው ነገር ጥሩ ነው፤ይጠቅማል፡፡፡፡ ተግዳሮቱ ከጊዜና ከሁነት ጋር ወደ ኋላ የመመለስ ነገር እንዳይኖር፣ መንግሥትም አሁን ላይ አገሪቱ ውስጥ ባለው የተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ምኅዳሩን የማጥበብ ፍላጎት ውስጥ እንዳይገባ ቶሎ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ደግሞ እስካሁን የተገነባው አቅም ፈርሶ፣ ተበታትነው ወይም አቅም አጥተው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንዳይሆኑ መነቃቃቱና ግለቱ መቀጠል አለበት፡፡

ሲኤስኤስፒ-2 በተያዘው የፈረንጆች ዓመት እንደመጠናቀቁ በቀሩት ወራቶች ላይ የምትሠሯቸው ቀሪ ሥራዎች ምንድን ናቸው?

ሰላማዊት፡- ጥቂት የሚቀሩ ተግባራት አሉን፡፡ አንደኛው በሚቀጥሉት ሳምንታት በድርጅቶቹ የሠራናቸውን ሥራዎች ሰብስበን አጠናቀን ሪፖርት የምናዘጋጅ ይሆናል፡፡ ከሥልጠና አኳያ ደግሞ የምንሰጠው ሦስት ሥልጠናዎች ይኖሩናል፡፡ አንደኛው ሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት እናገለግለዋለን ብለው ለተነሱበት ኮንሲቲዌንሲ ግንባታ  ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ አንዳንዶቹ ጉዳዩን ለይተው ቢያውቁትም መቀራረቢያ መንገድ ላይ ምንም አልሠሩም፡፡ ይህም የሆነው ክህሎቱ ስለሌላቸው ነው፡፡ በዚህ ላይ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ሁለተኛው የድጋፍ ማሰባሰብና ብዝሃነት ላይ የሚሰጥ ሥልጠና ነው፡፡ እኛ እየወጣን ስለሆነ ተቋማቱ ሌሎች ድጋፎችን እያዩና እየተወዳደሩ የተለያዩ ክህሎቶችን አዳብረው ፕሮጀክቶችን መሳብ የሚችሉበትን ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ሦስተኛው በሰላም ዙሪያ አገር በቀል የምክክርና ዕርቅ ባህሎችን እነሱን የሚያሰባስብ መዝገብ (Booklet) እያሠራን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከተሠሩት ላይ የተዘለሉትን በማምጣት አንድ መዝገብ ሠርተን ማጣቀሻ እንዲሆን በማድረግ ስለ ሰላም ጉዳይ መሥራት የሚፈልግ አካል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲሄድ በየአካባቢዎቹ ምንድነው ያለው? የሚለውን ለማጣቀስ የሚያስችል ነው፡፡ በዚህ ላይ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በተለይ አሁን ላይ አገሪቱ ካላት የሰላምና ግጭት ሁኔታ አንፃር ትንሽ ሚና ይጫወታል ብለን ያሰብንበት ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ባህሎች ውስጥ ሰላምን ለማምጣት የሚያግዙ እሴቶችን የሚያይ፣ መደማመጥን የሚወድ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ትንሽ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

በመጨረሻም የምገልጸው የትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል፣ የትኛውም ዓይነት ድርጅት አደረጃጀት ሲቪል ማኅበረሰብም ሆነ መንግሥትና የግል ተቋማት ሚዲያን ጨምሮ የሚሠራው ሰላማዊ፣ ዘላቂ የሆነ፣ ለዜጎች ምቹ የሆነ አገር ለመፍጠር ነው፡፡ የተፈጠረ ከሆነም ያ እንዲቀጥል ነው፡፡ በዚህ የጋራ ግብ ውስጥ ሁሉም አካላት ሚናቸውን ካልተጫወቱ ትክክል አይሆንም፡፡ ‹‹ቼክ ኤንድ ባላንስ›› የሚመጣው፣ ያልተሰማው ድምፅ የሚሰማው፣ የተሰማው ድምፅ ማብራሪያ የሚያገኘው ሁሉም ሚናቸውን መጫወት ሲችሉ ነው፡፡ 

ሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ሊጫወቱ በሚያስቡት ሚና ውስጥ የግሉ ዘርፍና ሚዲያው ተባብረው ካልሠሩ ለውጥ አይመጣም፡፡ እንደ ቡድን መሪ በመጨረሻ የማስተላልፈው ተባብረን ካልሠራን የሚፈለገው ዘላቂ ለውጥ አይመጣም፡፡ ይህ ተፈላጊው ለውጥ በኢኮኖሚ፣ በሰብዓዊ መብት መከበርና በሌላም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይኼ ለውጥ የሚመጣው ተናበንና ተነጋግረን ስንሠራ ነውና በሚዲያ፣ በግሉ ዘርፍና በሲቪል ማኅበረብ ተቋማት የሚሠሩ መሪዎች በየተቋማቸው ይህንን ዕድል ቢፈጠርና መተባበርንና ቅንጅትን የሚያበረታታ ሥራ ቢሠራ የምንወዳት አገራችን አድጋ መብቶች የሚከበሩባት ግጭትና ስደት የማንሰማባት አገር መሆን ትችላለች፡፡ ስለሆነም እነዚህ አካላት አብረው እንዲሠሩ አደራ እላለሁ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...