Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተማሪዎችን ለውጭ ትምህርት ዕድል የሚያዘጋጅ ፕሮግራም ይፋ ሆነ

ተማሪዎችን ለውጭ ትምህርት ዕድል የሚያዘጋጅ ፕሮግራም ይፋ ሆነ

ቀን:

በድምፃዊት ቻቺ ታደሰ የሚመራውና ኢትዮጵያን በማስተዋወቅና የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ እየሠራ የሚገኘው ሩትስ ኢቨንት፣ ለውጭ አገር ትምህርት ወሳኝ የሆነውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ለማጠናከር ያግዛል ያለውን ‹‹ሶር ቱ ሰክሰስ›› [ወደ ስኬት ማማ] የሚባል ፕሮግራም ይፋ አደረገ፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴርና ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ከነሐሴ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ይሰጣል የተባለው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት፣ በውጭ አገር  ወይም በአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የሚፈልጉ ተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት ያስችላል ተብሏል፡፡

ተማሪዎችን ለውጭ ትምህርት ዕድል የሚያዘጋጅ ፕሮግራም ይፋ ሆነ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ድምፃዊት ቻቺ ታደሰ

ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ፕሮግራሙን አስመልክቶ በተዘጋጀው መድረክ ገለጻ ያደረጉትና ትምህርቱን በመሪነት የሚሰጡት መምህርት ማርገሬት ሆፈር እንዳሉት፣ ሥልጠናው  ለውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች መግቢያ ከሚያገለግሉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ሥልጠና በተጨማሪ፣ በውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅን ያካትታል፡፡

ለዓለም አቀፍ የትምህርት ሥርዓት፣ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ያዘጋጃል የተባለው ፕሮግራም፣ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ማመልከቻዎችን ለመሙላት በሚያስፈልጉ መሥፈርቶች ላይም የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ተማሪዎችን ለውጭ ትምህርት ዕድል የሚያዘጋጅ ፕሮግራም ይፋ ሆነ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
መምህርት ማርገሬት ሆፈር

ሥልጠናው በበይነ መረብና በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ በአካል የሚሰጥ ሲሆን፣ በሥልጠናው መሳተፍ የሚችሉትም ለመማር ዝግጁ የሆኑና የሚሰጡ መለማመጃዎችን በአግባቡ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡

ከምትኖርበት አሜሪካ ለ30 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያ በመመላለስ በጎዳና ልጆች፣ በትምህርትና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ስትሠራ የቆየችው ድምፃዊት ቻቺ ታደሰ፣ በኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያለውን እንግሊዝኛ የመረዳት ችግር መመልከቷን ገልጻለች፡፡

ችግሩን በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ከድምፃዊ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ጋር በመሆን በሳይንስ አፕቲትዩድ ቴስትና በቶፍል ተማሪዎችን ስታሠለጥን መቆየቷን የገለጸችው ድምፃዊት ቻቺ፣ ከራሷ ልምድ በመነሳት በ‹‹ሶር ቱ ሰክሰስ›› ፕሮግራም ተማሪዎችን ለማገዝ መነሳቷን ተናግራለች፡፡

‹‹ልጆቻችን ዩኒቨርሲቲ ሆነው ቶፍል (የእንግሊዝኛ ክህሎት ፈተና) ማለፍ ያልቻሉበት ምክንያት እንግሊዝኛን መረዳት ባለመቻላቸው ነው፤›› የምትለው ድምፃዊቷ፣ ይህንንና ዩኒቨርሲቲ ገብተው ቋንቋውን ባለመቻላቸው የሚደርስባቸውን ሥነ ልቦናዊ ጫና ለመቅረፍ ፕሮግራሙ እንደሚረዳ ጠቁማለች፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ክፍል የተገኙት አቶ ሙሉጌታ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በእንግሊዝኛ መሆኑን፣ ከተለዩ ችግሮች መካከልም እንግሊዝኛ ቋንቋን መረዳት እንደሚገኝበት ገልጸው፣ ለዚህም ሚኒስቴሩ ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች እንግሊዝኛ ቋንቋን ለመገንዘብ የሚችሉበት ፖርታል ጥቅም ላይ ማዋሉን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱትን ብቻ ለማብቃት ሳይሆን፣ ሰፋ አድርጎ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የሚያግዝ የትምህርት ክፍል መክፈቱንና በዚህም ከሶር ቱ ሰክሰስ ፕሮጀክት ጋር እንደሚሠራም አክለዋል፡፡

ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው ሆነ ተከፍሎ ውጭ ለመማር ሲሄዱ የማመልከቻ ቅፅ ከመሙላት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥማቸው፣ ከእነዚህ ውስጥ ለድባቴ፣ ለሱስ እንዲሁም ለሥነ ልቦና ጉዳት መዳረግ እንደሚገኝበት ከመድረኩ የተነሳ ጥያቄ ነበር፡፡

እነዚህ ችግሮች ከኢትዮጵያ ለሚሄዱት ብቻ ሳይሆን አሜሪካ ተወልደው ባደጉትም እንደሚከሰት፣ ተማሪዎች ከወላጆች ተለይተው ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ መጠጥ፣ ዕፅና ሌሎች ነገሮችን ለመልመድ ቅርብ እንደሚሆኑና ለዚህም ጠንካራ ክትትል እንደሚያስፈልግ ቻቺ ተናግራለች፡፡

በእነሱ በኩል ሥልጠናውን አግኘተው በአሜሪካ ነፃ የትምህርት ዕድል ለሚያገኙ ተማሪዎች፣ ከኢትዮጵያ ከመሄዳቸው በፊት ስለ አሜሪካ ኑሮ ማሠልጠንን ጨምሮ በአሜሪካ ቤተሰብ (ተንከባካቢ) እስከ ሚያገኙበት ድረስ እንደሚሠራ፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ እንደሚኖርም ጠቁማለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...