Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከመስከረም የመጨረሻ ሰኞ እስከ ሰኔ 30

ከመስከረም የመጨረሻ ሰኞ እስከ ሰኔ 30

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በኦፌሴል ቋንቋና ስያሜ ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛው ዓመት የሥራ ዘመን ሲባል እንሰማለን፣ እናውቃለን፣ እኛም እንላለን፡፡ ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማለት በአንድ ጠቅላላ ምርጫና በተከታዩ ጠቅላላ ምርጫ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ (እንደ ሕጉና እንደ ወጉ፣ እንዲሁም በአብዛኛው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ) በምርጫ የተደራጀውና ሥልጣን ላይ የሚቆየው ምክር ቤት ከዚህ በፊት በተደረጉ ምርጫዎች ቁጥር ስድስተኛው ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡  በጠቅላላው፣ የዚህኛው ፓርላማ የዚያኛው ፓርላማ ወይም የስድስተኛው ፓርላማ ዘመን ሲባል በአንድ ጠቅላላ ምርጫና በሚቀጥለው/በተከታዩ ጠቅላላ ምርጫ መካከል ያለው ፓርላማ ዘመን ነው፡፡ የአዲሱ ፓርላማ የሥራ ዘመን ጠቅላላ ምርጫው በተካሄደበት ዓመት ቀጥሎ ባለው መስከረም ወር ላይ ይጀምራል፡፡ እዚህ ውስጥ ብዙ አነጋጋሪ ነገሮች ቢኖሩ ነውርም፣ ክፋትም የለበትም፡፡ ለዴሞክራሲ ቆሜያለሁ ለሚል ሰውም ሆነ ቡድን ነውርና ክፋት የሚሆነው መነጋገርን አለማወቅ ነው፡፡ ለምሳሌ የአገሪቱ የመጀመርያው የተጻፈ ሕገ መንግሥት (1923) የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትና የሕግ መምርያ ምክር ቤት የሚባሉ ክፍሎች ያሉት ‹‹ፓርላማ›› በሕግ የተቋቋመውና የእነዚህ ምክር ቤቶች ሕንፃ (የአሁኑ አራት ኪሎ ባለ ሰዓት ሕንፃ) የማዕዘን ድንጋይ የተቀመጠው ጥቅምት 23 ቀን 1926 ዓ.ም. ከ90 ዓመት በፊት ነው፡፡

በዚያ ሕገ መንግሥት መሠረት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አማካሪዎችን የሚመርጣቸው ንጉሠ ነገሥቱ ነው፡፡ የሚመረጡትም በመሣፍንትነትና በሚኒስትርነትም፣ በዳኝነትና በጦር አለቅነትም መንግሥታቸውን ብዙ ዘመን ካገለገሉ መኳንንቶች ወገን ነውና፡፡ የሕግ መምርያ ምክር ቤት አማካሪዎችን ደግሞ ለጊዜው ሕዝብ መምረጥ እስኪችል እስከ ተወሰነው ዘመን ድረስ መኳንንቶችንና ሹሞች ይመርጧቸዋል ነው የተባለውና (አንቀጽ 31 እና 32) የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ፀንቶ በቆየበት ዘመን ‹‹ምርጫ›› አልነበረም፡፡ የሕግ መምርያ ምክር ቤት አማካሪዎች ምርጫ የተጀመረው በ1948 ዓ.ም. የተሻሻለ ሕገ መንግሥት ከፀና በኋላ በመሆኑ የ1949 ዓ.ም.፣ የ1953 ዓ.ም.፣ የ1957 ዓ.ም.፣ የ1961 ዓ.ም. እና የ1965 ዓ.ም. ምርጫዎች ያደራጇቸው ምክር ቤቶች ነበሩ፡፡ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 1/1967 ዓ.ም. ንጉሡን ከሥልጣን ሲያወርድ፣ የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥትንም ‹‹እንዳይሠራ ታግዷል›› ብሎ ሲወስን፣ ከዚሁ ጋር ‹‹የኢትዮጵያ የሕግ መምርያና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ፓርላማ) ሕዝብ በትክክለኛ የዴሞክራሲ ዘዴ ለሕዝብ ጥቅም የሚያገለግሉ እውነተኛ ወኪሎችን እስኪመርጥ ድረስ ተዘግቷል›› ሲል የበተነው/የዘጋው የ1965 ዓ.ም. ምርጫ ያቋቋመውንና በ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 77 እንደተደነገገው (‹‹የፓርላሜንቱ ደንበኛ የጉባዔ ወራት በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ዋና ከተማ በየዓመቱ በጥቅምት ሃያ ሦስት ቀን ተጀምሮ እስከ ሰኔ አንድ ቀን ድረስ ይቀጥላል››) ጥቅምት 23 ቀን 1966 ዓ.ም. ሥራውን ጀምሮ የነበረውን ምክር ቤት ነው፡፡

በወታደራዊ መንግሥት ዘመንም፣ በተለይም ወደ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ›› ምሥረታ ‹‹መዳረሻ›› አካባቢ ሕገ መንግሥት በውሳኔ ሕዝብ (ሪፈረንደም) ማፅደቅ፣ ወዘተ ‹‹የዕድገት ደረጃ›› ላይ ደርሰናል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ውሳኔ ሕዝብ (ከደርግ በኋላና ዛሬ ጭምር ‹ኮራፕት› ተደርጎ፣ ወይም አላዋቂ ስያሜውን አጠናግሮት ሕዝበ ውሳኔ የተባለው) የደርግ ዘመን የ‹‹አዕምሮ ሥራ›› ውጤት ነው፡፡

እና በየጊዜው ተደጋግሞ እንደተነገረው ደርግም ኢሕአዴግም ኢትዮጵያ ላይ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አቋቁመናል ቢሉም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈቃዱ ውጤት የሆነ ነፃ ምርጫ አካሄዶ አያውቅም ማለት አሁንም ድረስ እውነት ነው፡፡ ስድስተኛውም ምርጫ በአንፃራዊነት ሻል ያለ ሁኔታ ውስጥ ተካሄደ፣ ሰውም በ‹‹ፈለገው›› ኮሮጆ ውስጥ የከተተው ድምፅ በትክክል ተቆጠረለት ተባለ እንጂ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን (ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ ወዘተ) ሕይወት አግኝተው መኗኗሪያችን ሆነው፣ ሁሉም ነገር ተሳክቶ፣ አልቆ ደቅቆ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 እንደሚለው የአገራችን ሕዝቦች ልዕልና መወከል የሰመረለት ሪፐብሊክ አደራጅተን ‹‹ሞተን›› አይደለም፡፡

ብዙ እንቅፋት፣ ከዚያም የለየለት ጦርነት ቢጥመውም በዚህ ውስጥ ግን አሁንም ድረስ ለይቶለትና በቃኝ፣ በቃችሁ ብሎ ያልቆመ ገለልተኛ ተቋማት የመገንባት፣ የመንግሥት አውታራትን ነፃና ለማንም ያልወገኑ አድርጎ እንደገና አፍርሶ የመሥራት ጅምር ጉዞ ውስጥ ገብተናል፡፡ ይህ ሲጀመርም አሁንም በደረስንበት ሒደት ውስጥ፣ የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ አደራ አልሆነም እንጂ፣ ሁሉም ርብርብና ጥረት የተገናኘበት ግዳጅ አልሆነም እንጂ፣ ውጤት ያስመዘገበ የትግል ዘርፍ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይህ ለውጥ የተመሰከረባቸው ተቋማት ናቸው፡፡

የአገሪቱን የአገዛዝ አውታራት ታማኝ መጠቀሚያና የግል ‹‹ሀብት›› አይደሉም፡፡ ፌዴራላዊና አካባቢያዊ የሥልጣን መንበሮች የተወሰኑ ቡድኖች ወይም ፓርቲዎች ርስት መሆን አይገባቸውም፡፡ አጠቃላይ ሥልጣን ማለት የዝርፊያ ማዕድ፣ የምርኮ ሲሳይም አይሆንም ብሎ ወስኖና ቆርጦ የመነሳት ጉዳይ አንድ ነገር፣ አንድ አደራ ላይ አብሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ተቋማት ገለልተኛና ነፃ አድርጎ የማቋቋም፣ የተጀመረና ነገር ግን በእጅጉ የተወዘፈ፣ ከሁሉም በላይ ደግም የሁሉንም ቁርጠኝነትና ስምምነት ያላገኘ ዕዳ አለብን፡፡

የስድስተኛው ምክር ቤት ከመስከረም የመጨረሻ ቀን ሰኞ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ የሚቆየው ሁለተኛው ዓመት የሥራ ዘመን ባለፈው ሳምንት ሲጠናቀቅ፣ በሌላ የሕይወት/የኑሮ ዘርፍ (ለምሳሌ በዓል ተከብሮ ሲጠናቀቅ፣ ተማሪዎች ፈተና ተፈትነው ሲጨርሱ፣ ወዘተ) እንደለመድነው፣ እንደለመደብንና እንደምናደርገው በሰላም ተጠናቀቀ አላልንም እንጂ፣ በተለይ የዘንድሮ የምክር ቤቱ ‹‹የጉባዔ ወራት›› ሁለት ጊዜ አገርና ሕዝብ በማናውቀውና መኗኗሪያ አድርገን ባልለመድነው ፍርኃት ውስጥ አስገብቶን ነበር፡፡

ይህንን የስድስተኛው ፓርላማ የዚህ ዓመት የሥራ ዘመን የአሥራ አንደኛውና የሃያ ስምንተኛው መደበኛ ስብሰባ ገጠመኝ፣ እዚህ ገጠመኝ ውስጥ የተነሳውን ጭብጥ፣ ጭብጡንም የሚገዛውን የፖለቲካና የሕግ ማዕቀፍ ከመዳሰሴ፣ ወይም ከቻልኩ አገላብጬ ለማየት ከመሞከሬ በፊት አንዳንድ ሕገ መንግሥታዊ መነሻ መሠረቶችንና ሐሳቦችን ላንሳ፡፡

እየረሳነው እንጂ ወይም የጋራ መግባቢያ እያጣን እንጂ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በፊት በመላው የኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዴሞክራሲ ጎን ቆሞ፣ ለዴሞክራሲ ብሎ የመታገል ጉዳይ ባለው የአገር ሕግ፣ በፀደቀውና ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጡት መብቶችና ነፃነቶች ሕይወት እንዲያገኙ መታገል ነው፡፡ ለውጡም፣ ሽግግሩም ሕገ መንግሥቱን ካሰነካከለ አምባገነንነት ወደ ሕገ መንግሥታዊነት መሸጋገር ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ቁም›› የሚለኝ ድምፅ እሰማለሁ፡፡ ዋናውና መሠረታዊው ሕመማችን ሕገ መንግሥቱ ራሱ ሆኖ ሕገ መንግሥቱን መድን/መድኅን ማድረግ እንዴት ይሆናል? መጀመርያ ሕገ መንግሥቱን በሌላ መተካት አለብን የሚል መከራከሪያና አቋም እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን ይህ ሕገ መንግሥት ጥሩ ነው? ጥሩ አይደለም? በሌላ መተካት አለበት? የለበትም? አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለመሻርና በሌላ የተሻለ ለመተካት ራሱ ዴሞክራሲን ይጠይቃል፡፡ የመጀመርያው ከሁሉም በፊት የሚቀድመው የአገር አደራና ግዳጅ ይህ ወይም ያኛው ፓርቲ፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ቡድን የሥልጣን ፍላጎት ወይም አማራጭ ማሸነፉ ሳይሆን፣ አማራጮች በነፃ ቀርበው በዕርጋታና በደንብ ተገላብጠውና በሚገባ ተመክሮባቸው በሕዝባዊ አወሳሰን ዕልባት ማግኘታቸው፣ በተግባር ሲውሉም፣ ሲሠራባቸውም ሊነቀሱና ሊሻሻሉ የሚችሉበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታና አሠራር አብሯቸው እንዲኖር መደረጉ መዝለቁ ነው፡፡

ይህን የመሰለ ነገር መጀመርያ ሳይኖር፣ ሁሉንም ዓይነት አስተሳሰብና የሥልጣን ፍላጎት ሁሉ በውድድር የሚያስተናብር ዴሞክራሲ ውስጥ መኖር ሳይጀምሩ፣ ወይም እንዲህ ያለ ዋስትና በእጅ ሳይጨብጡ እንዴት አድርጎ ሕገ መንግሥት ወደ ማሻሻል ግዳጅ ይገባል?

ከዚህ ጋር የተያያዘ ሌላም ጥያቄ ይነሳል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለመለወጥ ያስፈልጋል የሚባለው ዴሞክራሲ በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ ይገኛል ወይ? የሚል፡፡ ይህም ሕገ መንግሥት፣ ከእሱም በፊት የነበሩት ሕገ መንግሥቶች፣ ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ከተደረገ በኋላ ኢትዮጵያን የበላይ ሕግ ሆነው የ‹‹ሠሩት›› ሕጎች ሁሉ፣ መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶቻችን በመሰደርና በመደንገግ ረገድ ብዙ ችግር ያለባቸው አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ትግል ሲያጎለው የኖረው የመንግሥት አውታራትን ፓርቲያዊነት ማፅዳትና ነፃ ማድረግ አለመቻላችን ነው፡፡ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችን ከፓርቲ/ከአንድ ወይም ከሌላ ቡድን ቁርጠኝነት፣ ፈቃደኛነት ከፍ ባለና ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኖር ላይ ባለመድረሳችን ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከጥቂት ‹‹ማስተካከያ›› ጋር ‹‹የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች››፣ ‹‹የኢትዮጵያ… ሕዝቦች ናቸው›› ይላል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መግለጫ ነው፣ ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረተ በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ነው ይላል (አንቀጽ 8)፡፡ ዕውን ይህ ነገር እውነት ነው? ይህ ነገር ይሆናል ወይ? በሌላ አነጋገር ዕውን የመንግሥት ሥልጣን በሕዝብ ባለቤትነት ውስጥ ሊገባ ይችላል ወይ? እንዲህ ያለ ነገር መሬት ሊይዝ ይችላል ወይ? አጠቃላይ እምነት ሆኗል ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱን ሕዝቦች ልዕልና መወከል የሰመረለት የተሳካለት ሪፐብሊክ ማደራጀት ይቻላል ወይ? ብሎ መጠየቅም የአባት (የእናትም ጭምር) ነው፡፡ የገዥዎች ሹመትና ሽረት በሕዝብ ድምፅ መዳፍ ውስጥ የገባበት/ገባ የተባለበት ታሪክ ከጀመረ ከፈረንሣይ አብዮት ጀምሮ (1789 ዓ.ም.) ከሁለት መቶ ሰላሳ ዓመት በላይ አለፈ፡፡ ፓርቲዎችን ከፓርቲ አማርጦ፣ ገዥዎችን ለተገደበ የሥልጣን ጊዜ በሕዝብ መሾም አብሮ የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ የተለመደ ነገር ከሆነ ቆይቷል፡፡ የምክር ቤቶችን በሕዝብ ምርጫ መደራጀት የሚወስነው፣ እነዚህ በምርጫ የተደራጁት በየደረጃ የተደራጁ ምክር ቤቶች በሚያቋቁሙት መንግሥት/ሥራ አስፈጻሚ ላይ ያላቸውን ሻሚነትና ተቆጣጣሪነት ከስምና ከመልክ ያለፈ እውነት የሚያደርገው መንግሥታዊ አውታራት የሥልጣን መንበሮች ሁሉ፣ በተለይም የፀጥታ አውታራት ከፖለቲካ ቡድን መዳፍ ነፃ ሲሆኑ ነው፣ የማንም ፓርቲ ርስት መሆናቸው ሲቀር ነው፡፡

በአገራችን የኢትዮጵያን የሥልጣን ዓምዶች አውታራት ከፓርቲ ታማኝነትና መዳፍ የማላቀቅ ከእነሱ ገዥነትና የሞኖፖል ባለቤትነት ነፃ የማድረግ የማሻሻያ ሒደት ውስጥ መግባት፣ እውነቱን ለመናገር ከዚህ በፊት በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ፣ እንዲያውም ኢትዮጵያን ሲያጎድላት የኖረ፣ ሕዝብ በድምፅ ሻሚና ሻሪ የሚሆንበትን ሥርዓት የሚያመጣ ነው፡፡

ያንኑ ያህል ግን ለዴሞክራሲ እታገላለሁ፣ የሕግ የበላይነትን (ማለትም ሕግ መንግሥትን ራሱን የሚገዛ፣ የሚያስገድድ፣ የሚያስገብርና የሚያስርበትን ሥርዓት) አሰፍናለሁ ብለው የሚነቃነቁ ሁሉ የሚገናኙበት፣ በጋራ የገጠሙበት የወል አደራ የጋራ አቋም አልሆነም፡፡ አዎ! በአገሪቱ የሚገኙ ኃይሎች ሁሉ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ይላሉ፣ ስለዴሞክራሲ ይናገራሉ፣ ዴሞክራሲን ይወዳሉ፣ እንወዳለን፣ ለዴሞክራሲ እንታመናለን ይላሉ፡፡ ወገናዊ ባልሆነ ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን ማደላደል፣ ማቋቋም ማለት ድረስ ግን አይሄዱም፡፡ ትልቁ ጉድለታችን፣ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ትግልም ያጎደለው ይኼው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው፣ መጀመሪያና ከሁሉም አስቀድሞ ይህንን ጎዶላችንን እናሟላ፣ ይህንን የመቀመጫችንን እናደላድል፣ እናንጥፍ ማለት፣ ወይም ሁሉንም ዓይነት አስተሳሰብና የሥልጣን ፍላጎትና ትግል በውድድር የሚያስተግድና የሚያስተናብር ዴሞክራሲ የሚመጣው መጀመሪያ ወገናዊ ያልሆኑ ገለልተኛና ነፃ ተቋማት ሲገነቡ ነው ማለት የየትኛውንም አመለካከት/አስተሳሰብ ወገኖች፣ ቡድኖች ፓርቲዎች፣ ወዘተ ድጋፍ ከለውጡ ጋር መቆየት ግድ የሚያደርገው፡፡

ስድስተኛው ፓርላማ ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን በሰላም አጠናቀቀ ስንል፣ ሕጉ እንደሚለው ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመርጠው ለአምስት ዓመት ነው፣ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል›› በሚለው በሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 58/3 ጭምር) አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ከየትኞቹም ያለፉት አምስት ምርጫዎች የተለየና የበለጠ ጠንቅና ውዝግብ አጋጥሞት የነበረው ምርጫ 2013 ያደራጀው ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት ስንል፣ በቃ በዚህ ምርጫ የአገሪቱን ልዕልና መወከል የተሳካለትና የሰመረለት ሪፐብሊክ አደራጀን! መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሻሚነትና ጠያቂነት ጋር ተገናኘ! እያልን አይደለም፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ዴሞክራሲን ያየነው ገና በጅምር ምዕራፉ በመከራ ገጽታው ማለትም አፈናውና ጥርነፋው ላላ ሲል፣ ይፈለጉ የነበሩና እንዲሁም ይጠበቁም፣ ያልተጠበቁም ዕርምጃዎች ሲወሰዱና የፖለቲካው ምኅዳር መከፋፈት፣ መፍታታት ሲጀምር ነው፡፡ በዚህም አማካይነት የተቃውሞ ኃይሎች በነፃ መንቀሳቀስ መብትና ነፃነት ሲነቃነቅ ነው፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችን፣ የሐሳብ ውድድሮችን የማስተናገድ ልምምድ ቀርቶ ‹‹ወሬ›› እና ወጉ ያልነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ግን ይይዘው ይጨብጠው አጣ፡፡ ደንብ ማክበር እንኳን ችግር ሆነ፡፡ ፓርቲዎች፣ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ ተፎካካሪነት መለወጥ፣ ይህም የሚጠይቀውን ምግባርና ባህርይ መያዝ አቃታቸው፡፡ ግብግብ ውስጥ የገቡ ኃይሎች ወይም ነገ የምናማርጣቸው ፓርቲዎች የተወሰነ መንዕስ ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና ዴሞክራሲያዊ የድርጅት ባህልና አኗኗር መለኪያን ማለፍ ያለባቸው ስለመሆኑ እንግዳና ባዳ ነገር ነበር፡፡ ይህን የመሰለ መነሻና አነሳስ የነበረው ዴሞክራሲ የግርግርና የቀውስ መደገሻ ሆነ፡፡ የተጀመረው ለውጥ፣ የነባርም የአዲስ ገብ ፓርቲዎችንም ርብርብን መጎናፀፍ ዕድል አጣ፡፡ ፀጥታና ሰላም ሕግ ማስከበር አበሳ እየሆነ መጣ፡፡ በዚህ ላይ ጦርነት ውስጥ ገባን፡፡ ጦርነት ውስጥ ደግሞ በታወቀ ምክንያት፣ እንኳን ያኔ ዛሬም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ከስድስት/ሰባት ወራት በኋላ ከሞላ ጎደል ጅምሩን የዴሞክራሲ ግንባታ እንኳንስ እያፋፋምን፣ ቀስ በቀስ እያፋፋን ለመሄድ የማንችልበት ዝብርቅርቅ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ጦርነቱ ውስጥ ምን ዓይነት ፈተናና አደጋ ውስጥ እንደነበርን ያኔም ጦርነቱን እየተዋጋ፣ ጦርነቱ ትጋት ውስጥ ብዙ ርብርብ በነበረበት ወቅት፣ በተለይም ደግሞ ከጦርነቱ በኋላና ጦርነቱ በመንግሥት ዙሪያ አሰባስቦ የነበረው ድጋፍ በሚያሳዝን ሁኔታ ከተበተነ በኋላ፣ የነበርንበት ፈተናና አደጋ በደንብ አልገባንም፡፡ እንኳንስ ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችሉ ለውጦች ውስጥ በአንድ ልብ ልንገባ፣ በሚገርም ‹‹አጋጣሚ›› የአንድ ክልል/ክፍለ አገር ገዥው ቡድን ክልሉን አገር ብሎ ‹‹መከላከያ ሠራዊት›› ገንብቶ አገርን ከውስጥ የወረረበት፣ የአገር መንግሥታዊ ዓምዶች ስብርብራቸው የወጣበት፣ ፀሐይ የሞቀው አገር ያወቀው የኢትዮጵያ እውነት ላይ አድማ የተመታበት ቀውስ ውስጥ ነበርን፡፡

‹‹በሰላም ተጠናቀቀ›› ብዬ ስለጀመርኩት የስድስተኛው ፓርማ የሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጉዳይ እንመለስ፡፡ ከመስከረም የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚዘልቀው በዚህ ሁለተኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ የፓርላማው/ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ መጀመሪያ አሥራ አንደኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ አሁን ደግም በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ፣ መንግሥት/ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቅ/እንዲለቁ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡

ጥያቄዎቹ በጠያቂዎቹ የተገለጹትን የአገሪቱን ችግር፣ አገሪቱ አጋጠማት ያሉትን ‹‹ፍዳ›› እና ‹‹መከራ›› ይዘረዝሩና የሚከተለውን ይጠይቃሉ፡፡

የበርካታ አገሮች መሪዎች መሰል ኃላፊነትን በወጉ ያለመወጣት ጉድለት ሲያሳዩ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀው ሥልጣናቸውን ሲለቁ ይታያሉ፡፡ በአገራችንም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተመሳሳይ ሕዝባዊ ተጠየቅ ሲቀርብባቸው ሥልጣን መልቀቃቸውን እናስታውሳለን፡፡ እርስዎም ወደ ሥልጣን የመጡት በዚሁ ተጠየቅ ምክንያት ነው፡፡ እርስዎስ ሥልጣንዎን በመልቀቅ የመፍትሔው አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ?

እንደ እኔ እንደ እኔ እንደ እንደ የሕዝብ ተወካይነቴ ብልፅግና ፓርቲ መራሹ መንግሥትም ሆነ ፓርላማው አገራችን ከገባችበት የፖለቲካ ቀርቃብ (ዴድ ሎክ) ማውጣት ስለማይችሉ ሥልጣኑን ለጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክቡ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 60 (1) መሠረት በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱን እንዲበትኑና ለአዲስ ምርጫ መንገዱን እንዲጠርግ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡   

ቀደም ሲል እንደተገለጸው የአንድ ‹‹ፓርላማ›› ዘመን ከአንድ ጠቅላላ ምርጫ እስከ ተከታዩ/ቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ ይዘልቃል ማለት፣ የግድ አምስት ዓመት መደፈንና ማጠናቀቅ የለበትም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 60 እንደደነገገው በሁለት ምክንያቶች ፓርላማው/ምክር ቤቱ ሊበተንና ሌላ አዲስ ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል፡፡ አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሱ በራሱ ምክንያት በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱን እንዲበተን ሲያደርግ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት አገራችን ውስጥ ባለፉት ስድስት ፓርላማዎች ወይም ምክር ቤቶች ቅንብር/ስብጥር ውስጥ ኖሮም ታቶም የማያውቅ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጣምራነት ሲፈርስ የሚከሰት ነው፡፡ ሌላም የአሠራር ዓይነት አለ፡፡ አይታወቅም፣ ብዙ አይነገርለትም እንጂ ጥያቄዎቹን ያነሱት ሁለቱም እንደራሴዎች ይህንን የአሠራር ዓይነት አልጠቀሱትም እንጂ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 በአንቀጽ 93 እና 94 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ላይ እምነት አጥቻለሁ፣ የሚል ሞሽን ስለሚቀርብበት ሁኔታ ይደነግጋል፡፡ ሞሽን በአንድ ጉዳይ ላይ ውይይት እንዲደረግበትና ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚቀርብ ሐሳብ/ጥያቄ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማለት መስተዳደሩ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የአስፈጻሚና አስተዳደራዊ አካል ነው፣ መንግሥት ነው፡፡ በመንግሥት ላይ እምነት አጥቻለሁ የሚል ጥያቄ ለውይይት የሚቀርብበት ውሳኔ የሚያገኝበት የምክር ቤቶች የራሱ ደንብ ተሞክሮ የማያውቅ፣ ቢሞከር ምን ‹‹ሊል›› እና ‹‹ሊሆን›› እንደሚችል የማይታወቅ፣ እንዲሁም የተለያዩ ፌርማታዎች ያሉት ቢሆንም፣ ሥርዓት ወይም ተቋም የመገንባት አንዱ ቦታና መድረክ ይህንን የመሰሉ ሕጎችን ‹‹ተፈጻሚነት› መምከርና መፈተሽ ነው፡፡

በሕዝብ አስተዳደር ግንባታ ሒደት ውስጥ የሕዝብ እንደራሴ ለመሆን የበቁ ተመራጮች በተልዕኳቸው ውስጥ የሕዝብን ተስፋና አመኔታ የማግኘትና የማሸነፍ ከባዱንና ረዥሙን መንገድ የተያያዙት (አደጋችም ቢሆን) መሆኑን የሚያሳዩት ሜዳው ውስጥ ሲሮጡ፣ ሲጫወቱ፣ ጨዋታውም፣ የጨዋታውም ሕግ ምን ያህል ከባድ ወይም ባዳና እንግዳ መሆኑን ቢያሳዩ ነው፡፡    

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...