Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ከሁለት ሳምንታት በፊት ረፋድ ላይ ከቤቴ ወጥቼ ትራንስፖርት ሳጣ ‹ልወዝወዘው በእግሬ› ብዬ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ እንደ እኔ ቆሞ ታክሲ መጠበቅ የሰለቻቸው ወገኖቼ የመንገዱን ግራና ቀኝ ይዘው ወሬያቸውን እየሰለቁ ይጓዛሉ፡፡ ከፊቴ ሁለት ወጣት ሴቶች የምሽት ክለብ ውስጥ የገጠማቸውን ጉድ እያነሱ በሳቅ ይፍለቀለቃሉ፡፡ አንዷ፣ ‹‹ናይት ክለብ ከሚሉት የወፈፌዎች መሰባሰቢያ ቢሉት ይቀላል፡፡ እነዚያ ዳያስፖራዎችና እዚህ ያሉት ቢጤዎቻቸው እንደዚያ ያበዱ መስለው በየአጥሩና በየግንቡ ሥር ሲላላሱ…›› እያለች ስትስቅ፣ ‹‹አንቺ እሱ ይገርምሻል ያቺ… እና ጓደኛዋን በነጋታው ጠዋት ብታያቸው እኮ ኩሽና ውስጥ ያደሩ ይመስሉ ነበር…›› ብላት ዞር ስትል እኔ ከኋላ አለሁ፡፡

እኔ እንዳልሰማ ለማስመሰል ብሞክርም ሁለቱም እንደማፈር ብለው፣ ከእኔ በተቃራኒ ባለው የመንገድ ጠርዝ አቅጣጫ ቀይረው ቆም አሉ፡፡ የሚያወሩትን እንድሰማባቸው እንዳልፈለጉ ስለገባኝ እኔም በተወራው እየተገረምኩ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ በእርግጥ በዚህ ጊዜ በየምሽት ክለቡ የሚታየው ቅጥ አምባሩ የጠፋበትን አስቀያሚ ተውኔት በየፈርጁ እኔም ዓይቻለሁ፡፡ በጣም ጥቂት ከሚባሉት በስተቀር በየቦታው የሚስተዋለው ቅጥ ያጣ ብልግና ያሳዝናል፡፡ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ታዳጊ ሴቶች ሳይቀሩ አጭር ቀሚስ ከቆራጣ አላባሽ ጋር ለብሰውና በስካር እንዳይሆኑ ሆነው ለተመለከተ፣ ይህችን አገር ወዴት እየወሰድናት ነው ያሰኛል፡፡ የእኔ ጉዳይ ከዚህ በኋላ ይቀጥላል፡፡

ወደ ሜክሲኮ አደባባይ የሚያመራውን ሚኒ ባስ ታክሲ ተሳፍሬ ጉዞው ከመጀመሩ አንድ ተሳፋሪና ወያላ ጠብ ጀምረዋል፡፡ ተሳፋሪው በሞባይል ስልኩ ላይ ያስጫነውን ሙዚቃ ድምፅ ከፍ አድርጎ ከፍቶታል፡፡ አጠገቡ ያሉትም ሆኑ ሌሎች ተሳፋሪዎች ዝም ብለዋል፡፡ ወያላው ግን፣ ‹‹ወንድም የጆሮ ማዳመጫህን በመጠቀም ሙዚቃህን ስማ፡፡ የእኔንም ሆነ የሌሎችን ተሳፋሪዎች መብት አክብር…›› ይለዋል፡፡ ተሳፋሪው፣ ‹‹የአማርኛ ዘፈን ቢሆን ኖሮ ምንም አትልም ነበር፡፡ የብሔሬን ሙዚቃ በመናቅህ ነው እንዲህ የምትንጨረጨረው…›› እያለ ሲውረገረግ እኔ በበኩሌ በጣም ደነገጥኩ፡፡

ይኼን ጊዜ ሌሎችም በድንጋጤ ተናጋሪውን በተረበሸ ስሜት ማየት ጀመሩ፡፡ ወያላው በንዴት ጦፎ፣ ‹‹ስማ አንተ እዚያው በጠበልህ፡፡ እኔን ብሔር ምናምን እያልክ አታነካካኝ፡፡ ይኼንን ቆሻሻና የወረደ ንግግርህን አርም፡፡ አለበለዚያ ታክሲውን አስቁሜ ትወርዳለህ፡፡ አሁንም በጆሮ ማዳመጫ የማታዳምጥ ከሆነ ትወርዳለህ…›› ብሎ አፈጠጠ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ነገር ለማብረድ ‹አንተም ተው፣ አንተም ተው…› ማለት ቢጀምሩም፣ ተሳፋሪው ግን ሙዚቃውን ዘግቶ ቡጢ ለመሰንዘር ተዘጋጀ፡፡ ወያላው ተንደርድሮ ሲመጣ ትርምስ ተጀመረ፡፡ ሾፌሩ ታክሲውን ጥግ አስይዞ አቆመ፡፡

ወያላው ከወንበር ሥር ሌባ ጎማ ይዞ ወርዶ፣ ‹‹ና ይለይልን…›› እያለ ሲፎክር ተሳፋሪው፣ ‹‹ምን ታመጣለህ…›› በማለት ሲያቅራራ ሰዎች መሀል ገብተው ለያዩዋቸው፡፡ በብልግና የታጀቡ ስድቦችንና እርግማኖችን እስኪበቃን ከሰማን በኋላ ጉዞ ልንጀምር ስንል፣ ወያላውና ሾፌሩ ተሳፋሪውን አንጭንም አሉ፡፡ ተሳፋሪው ደግሞ፣ ‹‹መብቴን ማንም አይቀማኝም…›› ብሎ ተንደርድሮ ገብቶ ወንበሩን ያዘ፡፡ ይኼኔ ወያላው ድንገት በያዘው ሌባ ጎማ ሲሰነዝር ለጥቂት ሳተው፡፡ የባሰ ትርምስ ተፈጠረ፡፡ በአካባቢው ጥበቃ የሚያደርጉ ፖሊሶች ወይም የትራፊክ ፖሊሶች ባለመኖራቸው፣ ደም ለመቃባት የፈለጉትን ሁለቱን ሰዎች መገላገል የእኛ ሥራ ሆነ፡፡ ወያላው ተው ሲባል ተሳፋሪው፣ ተሳፋሪው ተው ሲባል ወያላው እየባሱ መከራ አየን፡፡

በስንት ማባበልና ልመና ተሳፋሪው በሌላ ታክሲ እንዲሸኝ ተደርጎ ለበርካታ ደቂቃዎች የተቋረጠው ጉዞ እንደገና ቀጠለ፡፡ ሁሉም የመሰለውን እያነሳ ሲያወራ እኔ ግን አንድ ነገር ቆረቆረኝ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ አስቸጋሪ የሆንነው? ለራሳችን የማንፈልገውን ሌሎች ላይ ለምንድነው የምንጭነው? የሆነ ነገራችን ሲነካ ለምን ከብሔር ጋር እናገናኛለን? ችግር ሲያጋጥም መቻቻል አቅቶን ምንድነው የሚያባላን? እስኪ ፌስቡክና ቲክቶክን ተመልክቱ፡፡ በአገር ጉዳይ ዙሪያ የሚነሱ ውይይቶች መቋጫቸው ስድብ ነው፡፡ ዘለፋ ነው፡፡ ጥላቻ ነው፡፡ በመረጃ ላይ ያልተመሠረቱ የወሬ ጫፎችን ይዞ መባላት፣ ትልቅ አገርና ማንነት እያለን ወንዝ የማያሻግር ዘርና ጎሳ ላይ መጣድ፣ በሐሰተኛ የታሪክ ግምገማ የሌለ ነገር ማውራት፣ ወዘተ ምን ያደርግልናል? ይህንን ገጠመኜን ያጫወትኳቸው አንድ የታወቁ ምሁር እንዲህ አሉኝ፡፡

‹‹ከሌሎች አገሮች የተሻለ ታሪክና አኩሪ አገር እያለን እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ እየሆንን ነው፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በፖለቲካና በመሳሰሉት አመለካከቶች ልዩነት እንዳለ እየታወቀ፣ ልዩነትን ለማስተናገድ አለመፈለግ በብዛት ይታያል፡፡ አንድ ሰው የመሰለውን ሲናገር በመንጋ ተነስቶ ማውገዝ በርትቷል፡፡ የራስን ማንነት በድፍረት ሳይገልጹ በፌስቡክ የዋሆችን የማስፈጀት ዘመቻ ተበራክቷል፡፡ በየቦታው ወሬ ከመድራቱ የተነሳ የተማረውም ያልተማረውም ሐሜተኛና አሉባልተኛ ሆኗል፡፡ በዚህ መሀል የዋሆች እውነት እየመሰላቸው ይማገዳሉ፡፡ የራሳችንን ተምሳሌታዊ የሆኑ መልካም እሴቶችን ንደን፣ የባዕዳኑን የባህል ወረራ በተበላሸ ገጽታው ተቀብለን፣ ከዓለም ጋር እኩል መራመድ አቅቶን እያነከስን ነው፡፡ በየቀኑ የምንሰማቸው ነገሮች በሙሉ በሐሰት የተጀቦኑ ናቸው፡፡ አገር በውሸት የሚያድግ ይመስል ሁሉም የሐሰት ወሬ ላይ ተጥዷል፡፡ ወሬ ዕውቀት አይደለም፡፡ ወሬ የሚያስንቅ ወረርሽኝ በሽታ ስለሆነ ወደ ቀልባችን እንመለስ…›› ነበር ያሉት፡፡

(ኢዮቤድ ካሳ፣ ከሰሚት)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...