Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ትኩረት ይሰጠው!

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ባለ106 ገጽ የ2015 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርቱ፣ ቀዳሚ ትኩረቱ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆኑ የሥር መንስዔዎችን መፍታት ሊሆን እንደሚገባ ማሳሰቢያ አቅርቧል፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችን፣ ዕገታዎችን፣ ማፈናቀሎችን፣ እንዲሁም በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር ከማቅረቡም በላይ በዜጎች ሰላምና በአገር ደኅንነት ላይ የተደቀነውን አደጋ በሚገባ የተነተነ ነው። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመቆሙ በፊትና ከዚያ በኋላ በነበሩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የተፈጸሙ የተባሉ ሕገወጥ ድርጊቶችን የዘረዘረው ሪፖሪቱ፣ በትጥቅ ትግል ተሰማርተናል በሚሉና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጭምር ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማካተት በርካታ ጉዳቶችን አመላክቷል። የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በምርመራ ይፋ ካደረጋቸው በርካታ የመብት ጥሰቶች በተጨማሪ፣ ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሐሳብ በማቅረብ የዜጎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ያደረጋቸው ጥረቶች መክነው እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሪፖርት ሲቀርብ ያስደነግጣል፡፡ የንፁኃን ሕይወት ለአደጋ ተጋልጦ መሠረታዊ መብቶቻቸውን ተነፍገው ለአደጋ ሲዳረጉ፣ የሚመለከተው አካል ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ዝምታን መምረጥ የለበትም፡፡ 

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ካለፈው ዓመት አንፃር ግጭቶችን በሰላም በመፍታት ረገድ አበረታች ጅማሮዎች መስተዋላቸውን፣ በሪፖርት ዘመኑ ተለዋዋጭና ዘርፈ ብዙ የመብቶች ጥሰቶች በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮችና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት መፈጸማቸውን ማስታወቁ ያስደነግጣል። የዘፈቀደ እስርና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም፣ በሚዲያና ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ላይ የተጣለ የዘፈቀደ ገደብ፣ ሕጋዊ ሒደትን ያልተከተለ የቤቶች ማፍረስ፣ በግዳጅ ማስነሳትና በኑሮ ውድነት የተነሳ የደረሰው እንግልት፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥሰቶች፣ እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም አሳሳቢነታቸው ከቀጠሉ ጉዳዮች ውስጥ እንደሚገኙ መግለጹ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. የተጀመረው የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ በተለይም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችና የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር፣ በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ መምጣት፣ እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ዘላቂ መፍትሔ ባለማግኘታቸው በተደጋጋሚ በሚያገረሹ ግጭቶች ሳቢያ የሚደርሰው ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል፣ የመሠረተ ልማቶችና የንብረት ውድመቶች አሁንም አሳሳቢነቱ መቀጠሉ ምን ጉድ ነው ያሰኛል፡፡

እንዲሁም በትጥቅ ግጭት ዓውድ ውስጥ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ኃይሎች ከሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪ፣ በፀጥታና በደኅንነት አካላት የሚፈጸሙ አስገድዶ የመሰወር፣ የዘፈቀደና ሕገወጥ እስር፣ በሰላማዊ ሕዝባዊ ስብስባዎች ወቅት ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በመጠቀም የሚደርሱ ጥሰቶች በሰዎች ላይ አስከፊ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸው የመንግሥት ያለህ የሚያሰኝ ነው። በሚዲያ፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ በማኅበረሰብ አንቂዎችና በሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ያነጣጠሩ ወከባና እስሮች፣ የፀጥታ ችግሮችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶችና አካባቢዎች ጊዜያዊም ሆነ ረዘም ያለ ጊዜ የቆዩ የመንቀሳቀስ ገደቦች በራሳቸው የመብት ጥሰቶች ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በሰዎች ላይ እያደረሱ ያሉት ሥጋት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች አገራዊውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ አሳሳቢ ካደረጉ ሁኔታዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ሲባል ደንገጥ ማለት ተገቢ ነው፡፡ 

በጦርነትና በትጥቅ ግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም፣ እንዲሁም ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ከመስጠት አስፈላጊነት በተጨማሪ፣ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣት በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ መብቶች ላይም ከፍተኛ ጫናና ጥሰት ማስከተሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸው፣ የጤናና የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተሟላ አቅማቸው አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአረጋውያንና በአካል ጉዳተኞች ላይ የደረሰው ጉዳት መቀጠሉ የሪፖርቱ አካል ሆኖ ሲቀርብ ያሳዝናል፡፡ በግብርናና በተያያዥ ሥራዎች የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደ ምርታማነት እንዳይመለሱ የማዳበሪያና የሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች እጥረት እንከን መፍጠሩን፣ በዚህም ሳቢያ የድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር መጨመሩ ተገልጿል፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልሎችና በአጎራባች አካባቢዎች ለበርካታ ወራት የቆየው ድርቅ አሁንም ዘላቂ ምላሽ የሚሻ መሆኑን፣ እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው መሠረታዊ በሆኑ የምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚታየው ዋጋ ንረትና በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሰዎችን ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረገ መሆኑ ኮሚሽኑን ብቻ ሳይሆን መንግሥትን ጭምር ማሳሰብ አለበት።

በተለይ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም በመፈናቀልና በስደት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት ተጋላጭነታቸው በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ያስታወሰው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት፣ በግጭትና በጦርነት ዓውድ ውስጥ ለደረሱ ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃቶች ተጠያቂነትን ለማስፈንና ለጥሰቱ ሰለባዎችም ተገቢውን መፍትሔ ከማስገኘቱ ጥረት ባልተናነሰ፣ የአካል ጉዳተኝነትና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጉዳይ የመንግሥትን ትኩረት እንዲያገኝ አሳስቧል። በተጨማሪም በሽግግር ፍትሕ ሒደቱም ሆነ በማናቸውም አገራዊ ሒደቶች የአካል ጉዳተኞችን፣ የሴቶችን፣ የአረጋውያንንና የተጎጂ ማኅበረሰቦችን ትርጉም ባለው መንገድ በማሳተፍ ረገድ አሁንም የረዥም ጊዜ ጥረት የሚፈልግ በመሆኑ፣ የመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን ዕገዛ እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጥሪ ሲያቀርብ ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል።

በአዲሱ በጀት ዓመት የኮሚሽኑንም ሆነ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ቀጣይ ክትትል የሚሹ ዋና ዋና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች የተመላከቱ ሲሆን፣ ለሰላምና ደኅንነት ዕጦትና ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የሥር መንስዔ ለሆኑ ጉዳዮች አሳሳቢነታቸውን የሚመጥን ጥረትና አፈጻጸም ከማድረግ በተጨማሪ፣ መንግሥታዊ በሆኑ መዋቅሮች የቅድመ ማስጠንቀቂያና የመከላከል አቅምን ማጠናከር የሚሉት ተካተዋል። በተጨማሪም በክልሎች መካከልና በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ አስተዳደራዊ፣ የመዋቅርና የድንበር መካለል ጥያቄዎች ለተጨማሪ ግጭትና የሕይወት መጥፋት ምክንያት እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ተጠቅሰዋል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በ2015 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ሰዎች በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ከቦታ ቦታ በነፃነት የመንቀሳቀስና የመሥራት መብቶቻቸው ባልተከበረበት ሁኔታ የተመዘገቡ መልካም ለውጦች ዘላቂነት አይኖራቸውም፤›› ብለው፣ የትጥቅ ግጭቶችን ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ለማስቆምና የሰዎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ መከናወን ካለባቸው ተግባራት በተጨማሪ፣ የፍትሕና የአስፈጻሚ አካላት ተቋማት በቁርጠኝነት የሕግ የበላይነትን ሊያስከብሩ እንደሚገባ ማሳሰባቸው ተነግሯል። መንግሥት ሆይ ለዚህ ሪፖርት ትኩረት ስጥ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...