Tuesday, September 26, 2023

የሱዳን ቀውስና የጎረቤት አገሮች የሰላም ጥረት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሱዳን ቀውሱ ተባብሷል፡፡ በሚያዝያ ወር በድንገት የፈነዳው ጦርነት ቀናትና ወራት መግፋቱን ቀጥሏል፡፡ በዋናነት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሱዳናዊያን የሚኖሩባትን ካርቱም ማዕከል ያደረገው ጦርነቱ፣ የከተማዋን 15 በመቶ ወይም 1.4 ሚሊዮን ነዋሪዎች ማፈናቀሉ ይነገራል፡፡

የሱዳን ሰቆቃ ግን ከካርቱም ከተማም የተሻገረ መሆኑ ይነገራል፡፡ በአጠቃላይ በመላው ሱዳን 25 ሚሊዮን ሱዳናውያን ለዕርዳታ ጠባቂነት ተደርገዋል ነው የሚባለው፡፡ የካርቱም ጦርነት ሳይበርድ በዳርፉር ዳግም አሰቃቂ ግጭት ማገርሸቱ እየተነገረ ነው፡፡ በምዕራብ ዳርፉር መዲና አልጀኒና እና በአካባቢው ዳግም ባገረሸው ጦርነት የሚቀጠፉ ዜጎች ቁጥር መጨመሩ ተሰምቷል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የቆየው የዳርፉር ግዛት አሁን መከላከያም ሆነ ሌላ የሚደርስለት የፀጥታ ኃይል የለም እየተባለ ነው፡፡ በሱዳን መከላከያ ሠራዊት፣ እንዲሁም በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተፋፋመው ጦርነት የበለጠ ተጋላጭ ያደረገው የዳርፉር ግዛት አሁን ከቀደመውም የከፋ ቀውስ ውስጥ ነው፡፡ ከሚያዝያ ወዲህ በጀመረው ግጭት ብቻ ከ180 ሺሕ በላይ ዜጎች ከዳርፉር ወደ ቻድ ተሰደዋል ይባላል፡፡

በሱዳን ያለው ቀውስ በሁሉም አቅጣጫ እየተባባሰ ቢሄድም፣ አገሪቱ የሚታደጋት መፍትሔ አፈላላጊ ማጣቷ ነው የሚነገረው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያት የሆነው የሁለቱ ተፋላሚ ጄኔራሎች ግትር አቋም መሆኑ ይነገራል፡፡

ሁለቱ ተፋላሚዎች ማለትም የሱዳን ጦር መሪ ጄኔራል አበዱልፈታ አል ቡርሃንና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ኃይል አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሃሜቲ)፣ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ፈጽሞ መቸገራቸው ይነገራል፡፡ ሁለቱ ሰዎች አንዱ ሌላኛውን ለማጥፋት ቆርጠው ተነስተዋል ነው የሚባለው፡፡ የሁለቱ ተፋላሚዎች ግጭት መቆም ያቃተው ብቻ ሳይሆን፣ አሰቃቂ ውድመት በሱዳን ላይ እያስከተለ የሚገኘው አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ባላቸው ፍላጎት መነሻነት ነው ይባላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ያላደረገ፣ ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ እየፈጠረ ያለ የውጊያ ታክቲክ ነው የሚጠቀሙት ይባላል፡፡ የካርቱሙ ውጊያ በአየር ድብደባ ጭምር የታገዘ መሆኑ የዕልቂቱን አሰቃቂነት ማሳያ ሆኖ ሆኗል፡፡

የሱዳንን ዕልቂት ለማስቆም በሚል እየተሞከሩ ያሉ ጥረቶች አብዛኞቹ መፍትሔ ሲያመጡ አልታየም፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ አስተናጋጅነት ከአንድም ሁለት ጊዜ የሰላም ጥረት ቢደረገም አልተሳካም፡፡ የእነ አሜሪካ ግፊት ታክሎበት ሁለቱ ወገኖች በተለያዩ ጊዜያት የተኩስ አቁም ለማድረግ ቢገደዱም፣ ነገር ግን ዘላቂ የሰላም ስምምነት ለመፍጠር የተቻለበት ዕድል እስካሁን አልተፈጠረም፡፡

ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተስተናገደው በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (IGAD) ዋና አዘጋጅነት የተካሄደው የሰላም ጥረትም ቢሆን ያለ ውጤት ነው የተጠናቀቀው፡፡ ኢጋድ አራትዮሽ (IGAD Quartate) በሚል የተጀመረው የሰላም ጥረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን የተካተቱበት ሰላም አፈላላጊ የአገሮች ስብሰባ ነው፡፡ ሰኞ ዕለት የተጠራው የኢጋድ አራትዮሽ ስብሰባ ደግሞ ሶማሊያና ኡጋንዳን የመሳሰሉ አገሮችን ጨምሮ አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያካተተ ትልቅ የሰላም ጥረት ነው፡፡ ይህ ኢጋድ መራሽ የሰላም ጥረት ከአገሮች በተጨማሪ የተመድ ሰብዓዊ ረድኤት ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ጨምሮ፣ ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ዓለም አቀፍ ተቋማትንም ያሳተፈ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ሰብስቦ ያሠለፈውና እጅግ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የተስተናገደው የሰኞው የአዲስ አበባው የሰላም ጥረት ግን የሚጠበቀውን ያህል ፍሬ አለማፍራቱ ነው የሚነገረው፡፡

የሰላም መድረኩ ሌላው ቀርቶ ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በተወካዮቻቸው ደረጃ እንኳን ፊት ለፊት አግናኝቶ ማነጋገር አለመቻሉ ነው የታወቀው፡፡ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተወካይ ቢገኙም የተቀናቃኙ የሱዳን ጦር ኃይል ተወካይ መቅረታቸው አነጋጋሪ ነበር፡፡

ኢጋድ የሰላም መድረኩን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ፣ የሱዳን ጦር ኃይል ተወካይ ለመገኘት ቃል ገብተውና ግብዣውን ተቀብለው መቅረታቸውን አሳዛኝ አጋጣሚ ሲል ነበር የገለጸው፡፡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የጂቡቲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር መሐሙድ ዓሊ የሱፍና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ተወካይ ቤንጃሚን ቦል ሜል የተካፈሉበት የኢጋድ የሰላም መድረክ፣ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተገኙበት ነበር፡፡

የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ሳዑዲ ዓረቢያና አሜሪካ ወኪል የላኩበት ብቻም ሳይሆን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተወካይ ዩሱፍ ኢዛት የተገኙበት ስለነበር የተሻለ ውጤት እንደሚገኝበት ተጠብቆ ነበር፡፡

የኢጋድ የማጠቃለያ መግለጫ እንዳመላከተው፣ መድረኩ ለሱዳን ሰላም ኢጋድ ባስቀመጠው ፍኖተ ካርታ ተፈጻሚነት ላይ በጥልቀት ለመወያየት የተጠራ ነበር፡፡

ኢጋድ በዚህ መግለጫው ለሦስት ወራት በቀጠለው የሱዳን ጦርነት 615 ሺሕ ሰዎች መሰደዳቸውና ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ከቀዬአቸው መፈናቀለቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው ጠቅሷል፡፡ ኢጋድ በመግለጫው በዋናነት ግጭቱ በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስቧል፡፡

‹‹ጦርነቱን በአስቸኳይ በማቆም ያለ ቅድመ ሁኔታ ግጭት የማቆም ስምምነት እንዲፈረም አናሳስባለን፤›› በማለት ነው ኢጋድ ጠንከር ያለ አቋም ያንፀባረቀው፡፡ የድርጅቱ መግለጫ አያይዞም ነገ ሐሙስ በግብፅ ካይሮ የሚስተናገደውን ተጨማሪ የሰላም ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡ ግብፅ በሱዳን ጦርነት የራሷን ጥቅም ለማካበት ስትል በተናጠል የሰላም ጥረት ብላ የፈጠረችው መድረክ ነው እየተባለ የሐሙሱ ስብሰባ ሲተች ቆይቷል፡፡ ኢጋድ ባወጣው መግለጫ ግን የግብፅን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲን፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያን መፍትሔ አፈላላጊ አገሮች ብሎ የሰየመው ኢጋድ በአዲስ አበባው ስብሰባ የተካፈሉ መሪዎችና ተወካዮች ጠንከር ያሉ መልዕክቶችን ያስተላለፉበት መድረክ ነበር፡፡

‹‹የሱዳንን ግጭት ማስቆም ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የሰላም መፍትሔ ለማፈላለግ ነው የተሰባሰብነው፤›› ሲሉ ጠቅላይ ማኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) አያይዘውም፣ የሱዳን ጦርነት በቀጣናው አገሮችና በአፍሪካ ላይ የጋረጠውን አደጋም አውስተዋል፡፡ ‹‹የሱዳን ጦርነት ከኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ ላላገገመው፣ እንዲሁም በሽብርተኝነትና በፀጥታ ሥጋት ለሚማቅቀው የአፍሪካ ቀንድና የሳህል ቀጣና ተጨማሪ ዕዳ ነው፤›› ሲሉ ያስረዱት፡፡

ሱዳናዊያን በራሳቸው ችግራቸውን መፍታት እንደሚችሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ግጭቱን ለሚያባባብሱ ችግሮች ወይም ወገኖች በር እንደማይከፍቱ አምናለሁ፡፡ ከዚያ ይልቅ በራሳቸው ችግሩን እንዲፈቱ ለማድረግ የተጀመሩ ቀጣናዊ ጥረቶችን እንደግፋለን፤›› ብለዋል፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ በበኩላቸው፣ የሱዳኑ ጦርነት እያስከተለ ስላለው ሰብዓዊ ቀውስ በማስመልከት፣ ‹‹የእኛ ስብሰባ እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ የሚገኘውና በዳርፉር፣ በተለይም በሱዳን ያለው ጦርነት ያስከተለውን ቀውስ ለመፍታት መፍትሔ የሚሰጥ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹በቀይ ባህር እንዲሁም በሳህል ቀጣና የሚደረገው የረድኤት አቅርቦት ሥራ በዋናነት የግጭት ተጎጂ የሆኑ ሴቶች፣ ሕፃናትና አቅመ ደካማ ወገኖችን ያስቀደመ ሊሆን ይገባዋል፤›› ሲሉ ነው ፕሬዚዳንት ሩቶ የተናገሩት፡፡

ኢጋድ በአዲስ አበባው ስብሰባው ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎም በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የረድኤት ኮሪደር ለመፍጠር እንዲተባበሩ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በካርቱም መውጫና የሚላስ የሚቀመስ ላጡ ወገኖች የሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረብ እንዲቻል፣ 30 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ያለው የሰብዓዊ ረድኤት ዞን እንዲፈጠር ከባድ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ግን የችግሩን አሳሳቢነት ታሳቢ በማድረግ በጎረቤት አገሮች ጭምር ሱዳናዊያን ተጠልለው የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሱዳን ቀውስ የሰብዓዊ ረድኤት አቅርቦት የሚውል እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንዲያቀርብ ጥሪ ቀርቦለታል፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት 446 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ብቻ ነው መገኘት የቻለው፡፡ የሱዳን ወቅታዊ ቀውስና ነባር ችግሮች ተደራርበው ለሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂነት የተዳረገው ሕዝብ 25 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡

የኢጋድ የአራትዮሽ መፍትሔ አፈላላጊ አገሮች ጉባዔ ላይ ለሱዳናዊያን የረድኤት ኮሪደርና የስደተኞች ማስተናገጃ ይዘጋጅ ተብሏል፡፡ ሱዳናዊያን የሚጠለሉበት ቢያገኙም ሆነ ከግጭት ቀጣና ነፃ ቢወጡ፣ በሚፈለገው ደረጃ የረድኤት አቅርቦቱን ማካሄድ ይቻላል የሚለው ሐሳብ ግን እርግጠኝነት ያጣ ይመስላል፡፡

ኤርትራ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ለማስታረቅ በግል ጥረት ስታደርግ ቆታይታለች፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያም በተለያዩ ጊዜያት በግል ልታስታርቅ ሞክራለች፡፡ ከዚህ ከፍ ያለ ጥረት ችግሩ እንደሚጠይቅ የተረዳችው የሱዳን ጎረቤት ኢትዮጵያ፣ በኢጋድ አራትዮሽ የአገሮችና የተቋማት ቡድን በኩል ግፊት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ በሱዳን ጦርነት ዋና ተጎጂ ከሚሆኑ አገሮች አንዷ እንደ መሆኗ፣ በተናጠልም ሆነ  በቡድን የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ለማስታረቅ ጥረት ማድረጓ የሚመሠገን እንደሆነ ይነገራል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ የሱዳንን ጦርነት ለፖለቲካ ትርፍ እንደማትጠቀም አረጋግጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የምትወዛገብበትና በሕገወጥ መንገድ በሱዳን ጦር የተያዘ የድንበር መሬት ያላት አገር ናት፡፡ ይህም ቢሆን ግን አሁን የድንበር ጥያቄዋን ወደ ጎን ብላ ለሱዳን ሰላም በተናጠልም በቡድንም እየሠራች ነው የምትገኘው፡፡

ከሱዳን ጋር በድንበር ብቻ ሳይሆን በባህል፣ በቋንቋ፣ በንግድ፣ በታሪክና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የረዥም ጊዜ ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያ ራሷ በቅጡ ከጦርነት ተፅዕኖ ሳታገግም በሱዳን ዕርቀ ሰላም እንዲፈጠር ጥረት ማድረጓ በታሪክ ሊያስወድሳት እንደሚችል የሚናገሩ አሉ፡፡

በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብቻ ሳይሆን፣ የአርበኞች መጠለያ በመሆን ሱዳን የማይዘነጋ ውለታ ለኢትዮጵያ መዋሏ ይነገራል፡፡ ሁለቱ አገሮች በጉርብትናቸው ቀውስ በገጠማቸው ጊዜ ሁሉ አንዱ የሌላውን ዜጋ በመቀበል ሲያስተናግዱ መኖራቸው በተደጋጋሚ ይውሳል፡፡

ይህ በውጣ ውረድ የተሞላ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ዛሬም ቢሆን ፈታኝ ሁኔታዎች እንዳላጣ ይነገራል፡፡ ከድንበር ውዝግብ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የተነሳ ሱዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቅሬታ እንደምታነሳ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች አንዴ ከግብፆች ሌላ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር ሲወግኑ የቆዩት የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች፣ አሁን እርስ በእርሳቸው እየተገዳደሉ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሱዳን ስትረጋጋ የሚደርስና ሊቆይ የሚችል ጉዳይ መሆኑ የገባት የምትመስለው ኢትዮጵያ፣ ሱዳኖቹን ማሸማገልን ቅድሚያ እንደሰጠች ነው በተደጋጋሚ ያሳወቀችው፡፡ ይህ ሁሉ መስዋዕትነት እየተከፈለላቸው ያሉት የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ጦር መሣሪያቸውን ጥለው ወደ ዕርቀ ሰላም ይመለሳሉ ወይ የሚለው ጉዳይ የብዙዎች መነጋገሪያ ከሆነ ሰንብቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -