Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ለኤክስፖርት የተዘጋጀ ስንዴ በኩንታል 50 ዶላር መሸጡ ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ዘንድሮ ለኤክስፖርት ያዘጋጀውን አንድ ኩንታል ስንዴ በ50 ዶላር መሸጡ ታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት 160 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ወይም 1.6 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ መላኳ የታወቀ ሲሆን፣ የተሸጠበትም ዋጋ በአንድ ሜትሪክ ቶን 500 ዶላር፣ ወደ ኩንታል ሲቀየር ደግሞ አንዱ ኩንታል 50 ዶላር መሆኑን ተረጋግጧል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (World Food Program – WFP) እና የዓለም ባንክ (World Bank) ኢትዮጵያ ለኤክስፖርት ያቀረበችውን ስንዴ የገዙ ተቋማት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በጠቅላላው ለሁለቱ ተቋማት ካቀረበችው 160 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በኩንታል ሲሠላ 80 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ መገኘቱ ታውቋል፡፡

ሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከዚህ ቀደም ከሩሲያና ከዩክሬይን ስንዴ ይገዙ እንደነበር፣ ሆኖም በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያን ስንዴ መግዛታቸውን ሚኒስትር ደኤታው አክለዋል፡፡

‹‹የስንዴ ኤክስፖርት መጀመሩ በራሱ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ዘንድሮ ስንዴ የሚያመጣው የዶላር መጠን የአኩሪ አተርና የጥራጥሬ ምርቶችን ያህል ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ኤክስፖርት የጀመርነው ዘንድሮ ነው፡፡ ወደ ኤክስፖርት ሲገባ መንገራገጮች አሉ፣ እንደተፈለገው አይሆንም፤›› ሲሉ አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

‹‹በሚቀጥለው ዓመት ከስንዴ ኤክስፖርት ቡናና ሰሊጥ የመሳሰሉ ምርቶች የሚያመነጩት ገቢ ይገኝበታል፤›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ ከስንዴ የሚገኘው ገቢ ሊያድግ እንደሚችልና ዘንድሮ ትልቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍጆታዋ አልፋ ትርፍ ምርት ያገኘች ቢሆንም የአገር ውስጥ የስንዴ ዋጋና የዓለም አቀፍ ዋጋ ያለመመጣጠን ችግር እንዳለበት፣ የአገር ውስጥ ዋጋ በጣም ከፍ ያለና ሲሸጥም ከተመረተበት ዋጋ (Production Cost) ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

አንድ ኩንታል ስንዴ በማምረት ወጪው 1,900 ብር አካባቢ ቢሆንም፣ ነገር ግን በአገር ውስጥ ገበያ ከስድስት እስከ ሰባት ሺሕ ብር እንደሚሸጥ፣ ይህ በራሱ የስንዴ ኤክስፖርትን ‹‹ምቹ›› አያደርገውም ሲሉ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

‹‹ሁልጊዜ የዓለም ገበያ ከአገር ውስጥ ገበያ በላይ ሲሆን ነው ኤክስፖርት የሚሳለጠው፡፡ ነገር ግን በገፍ ስናመርት ዋጋው ይወርዳል፡፡ የበለጠ ፍጥነት መጨመርና በደንብ ማምረት ስንጀምር እየተስተካከለ ይሄዳል፤›› ሲሉ አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡

በቀጣዩ ዓመት ኤክስፖርት ለማድረግ የታሰበው የስንዴ መጠን ዕቅድ እስካሁን አለመፅደቁን ገልጸው፣ ብሔራዊ የኤክስፖርት ኮሚቴው ካፀደቀው በኋላ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው የስንዴ ምርት ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ፣ ከአማራና ከሶማሌ ክልሎች የሚሰበሰብ እንደሆነ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵን የስንዴ ምርት ወደ ውጭ የመላክ መርሐ ግብር በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በተካሄደበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የስንዴ ምርትና የምግብ ፍጆታ ሚዛን ታይቶ ከአገሪቱ ፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ እንደሚኖር በመረጋገጡ በዚህ ዓመት ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ መወሰኑን፣ ለዚህም ዘንድሮ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ካላቸው ስድስት አገሮች ጋር የሦስት ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት መፈረሙን፣ በየካቲት ወር በተደረገው የኤክስፖርት ማስጀመርያ መርሐ ግብር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ግርማ ብሩ (አምባሳደር) ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች