Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት ለማድረስ የተጀመረው ውጥን

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በ2015 እና በ2016 በጀት ዓመት ብቻ 12.8 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚያስፈልግ ግብርና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ውስጥ እስከ ግንቦት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ተገዝቶ ለአርሶ አደሩ እየተደረሰ መሆኑን ሚኒስቴሩ ቢገልጽም፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የማዳበሪያ እጥረት መኖሩ ይስተዋላል፡፡

በዚህ ዘርፍ ከአቅርቦት በተጨማሪ የዋጋው መናር ለአርሶ አደሩ ራስ ምታት ከመሆኑ ባሻገር፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለአፈር ማዳበሪያ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡

በተጨማሪም፣ ዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጣሪያ በነካ ቁጥር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ፣ መተዳደሪያቸው በግብርና ለሆኑ አገሮች ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፈ›› ሆኖባቸዋል፡፡

ከዋጋ ጭማሪ፣ ከአቅርቦት እጥረትና በወቅቱ ካለመቅረብ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ተግዳሮቶች ደግሞ እንደ ኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ለሚያቀርቡ ድርጅቶች ትልቅ የገበያ ዕድል ይዞ መጥቷል፡፡

ለአሥር ዓመታት የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ሲያመርት የዘለቀው ኢኮ ግሪን ማዳበሪያ፣ በተለይም የማዳበሪያ አቅርቦት ሲዘገይ ትልቅ መፍትሔ እንደነበረ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ኢርጳ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊው ይህንን የተናገሩት ኢኮ ግሪን ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ምርቱን የሚጠቀሙ ሞዴል አርሶ አደሮችንና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዕውቅና በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ፣ የአፈር ማዳበሪያ ሳይመጣ የምርት ወቅት እንዳያልፍ የኢኮ ግሪንን የተፈጥሮ ፍሳሽ ማዳበሪያ ተጠቅመው የነበረውን ችግር መቅረፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም አርሶ አደሮች ውጤታማ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ደረጀ፣ ከአካባቢ ጥበቃና አፈር መልሶ እንዲያገግም ከማገዝ አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል፡፡

አቶ ከበደ ላቀው የኢኮ ግሪን ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ኢኮ ግሪን ከተመሠረተ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ምርቱን በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ፣ በፈሳሽ መልክ የተዘጋጀው ማዳበሪያ ለሰብል ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች እንዳሉበት ገልጸዋል፡፡

የፈሳሽ ማዳበሪያውን የሚጠቀሙት ትልልቅ የአበባ እርሻዎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ የሚመርቱ ድርጅቶች መሆናቸውን አቶ ከበደ ተናግረዋል፡፡

ኢኮ ግሪን የሚያምርተው የፈሳሽ ማዳበሪያ በአሁኑ ጊዜ በዓመት ስምንት ሚሊዮን ሊትር መድረሱን፣ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ መጠን የማምረት ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ከበደ ገለጻ፣ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ በመደበኛው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት የምርት ጊዜ ለሚያልፍባቸው አርሶ አደሮች ትልቅ እፎይታ እየሰጠ መሆኑንና መንግሥት በስፋት እያለማመደ ለሚገኘው የከተማ ግብርና ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ምርቱ በስፋት እየቀረበ መሆኑን፣ በዚህም አርሶ አደሮቹ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ምርቱን በስፋት እየተጠቀሙ የሚገኙት መካከል አገረ ማርያም፣ ሸዋ ሮቢት፣ ደራ፣ ጎዘመን፣ ፎገራና ራከምከም ሲሆኑ፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ባቱ (ዝዋይ)፣ ድዳ፣ ቦራ፣ ሉጫና ኢተያ የተሰኙ አካባቢዎች ምርቱ በብዛት እየቀረበ ይገኛል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሥራ አመራርና ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሸምሱ እንደተናገሩት፣ የፈሳሽ ማዳበሪያ በተለይም የቡና አምራቾች እንዲጠቀሙ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል፡፡

ሰፊ የሆነ የቡና አምራች አደረጃጀቶች መኖራቸውን የገለጹት አቶ መሐመድ፣ በአሁኑ ሰዓት በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጁ በማኅበራት ይህንን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ፣ ባለሥልጣኑ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ ስድስት ማዕከላት በክልሎች እንደሚያቋቁም ገልጸው፣ የቡና ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ 70 የሚደርሱ ቅመማ ቅመሞች መኖራቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ 50 የሚሆኑት በኢትዮጵያ የሚገኙና አገር በቀል መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህንን የቅመማ ቅመም ዘርፍ በተፈጥሯዊ የፈሳሽ ማዳበሪያ በመደገፍ፣ ዘርፉ ትልቅ ደረጃ የሚደርስ መሆኑን አክለዋል፡፡ በዚህ ዓመት ወደ ቅመማ ቅመም ዘርፍ ለመግባት የግብይት መመርያዎችና የተለያዩ መተግበሪያዎች ተዘጋጅተው መውረዳቸውን፣ ይህንን በማስተዋወቅና በመደገፍ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል፡፡

የኢኮ ግሪን የፈሳሽ ማዳበሪያ ተጠቃሚ ከሆኑት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መካከል የጋይት ኅብረት ሥራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ ፈንታሁን በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡

ማኅበሩ ከ76,000 በላይ አባል አርሶ አደሮች እንዳሉት፣ የኢኮ ግሪን ፈሳሽ ማዳበሪያ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካይነት 340,000 ሊትር ለመጠቀም ዕቅድ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም የሚሆን ከአርሶ አደሮቹ ቅድሚያ ገንዘብ በመሰብሰብ ወደ 80,000 ሊትር ግዥ መፈጸማቸውን፣ ነገር ግን ከተገዛው ላይ ማግኘት የተቻለው ከታቀደው በታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የማዳበሪያ እጥረት በማጋጠሙ፣ ለሁሉም አካባቢዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ለማዳረስ የምርት እጥረት መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ማኅበሩ ያቀደው 340,000 ሊትር የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ማግኘት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

ማኅበሩ በሚሠራባቸው አካባቢዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያው እጥረት ስለገጠመው፣ ከአርሶ አደሮች የተሰበሰበው ገንዘብ መመለሱን ነገር ግን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያውን ማግኘት የቻሉት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ከበደ እንደገለጹት የፈሳሽ ማዳበሪያው ሙሉ ለሙሉ በተፈጥሮ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ በሰውና በእንስሳት፣ እንዲሁም በአካባቢ ጤና ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም፡፡

የኢኮ ግሪን ፈሳሽ ማዳበሪያ በስፋት ከተሠራበት ከውጭ የሚገባው ማዳበሪያን በመተካት የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

የፈሳሽ ማዳበሪያው የመሬት ለምንነት የሚያሳድግ በመሆኑ ማዳበሪያ በብዛት የሚጠቀም መሬትን መቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡

የመሬት ለምነትን በመጨመር ከአፈር ማዳበሪያ የመጠቀም መጠን እየቀነሰ እንደሚመጣና ይህም የውጭ ምንዛሪ ከማዳን አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የሚመረተውን ፈሳሽ ማዳበሪያ ለሁሉም የሰብል ዓይነቶች የሚያገለግል መሆኑን፣ በተለይም ለስንዴና ለሌሎችም ሰብሎች ምርታማነትን ከመጨመር አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ከበደ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡናና የአበባ እርሻም ጭምር ፈሳሽ ማዳበሪያውን እየተጠቀሙ ናቸው፡፡

ኢኮ ግሪን የሚያመርተው ፈሳሽ ማዳበሪያ ዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑን፣ በአንድ ሊትር 60 ብር እንደሚሸጥም ገልጸዋል፡፡

ኢኮ ግሪን ለአገር ውስጥ ከሚያቀርበው ምርት በተጨማሪ በኬንያና በሌሎች አፍሪካ አገሮች ምርቱን ለመላክ በሒደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ምርቱን በስፋት ለማቅረብ ከአዲስ አበባ 60 ኪሎ ሜትር ደብረ ብርሃን መስመር የሚገኘው ፋብሪካውን ለማስፋፋት ዕቅድ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች