Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአሜሪካና ቻይናን ውጥረት ያረግባል የተባለው ውይይት

የአሜሪካና ቻይናን ውጥረት ያረግባል የተባለው ውይይት

ቀን:

አሜሪካና ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የገቡበት የቃላት ጦርነት ውጥረትን አንግሦ ከርሟል፡፡ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ምኅዳሮች የሚገዳደሩት አገሮቹ፣ ጎራ ለይተው መሠለፍ ከጀመሩም ቆይተዋል፡፡ ይህም በአገሮቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻከሩ አልቀረም፡፡ ውጥረት ውስጥም አስገብቷቸዋል፡፡

በዋሽንግተንና ቤጂንግ መካከል ያለው ግንኙነት እያሽቆለቆለ የመጣው በተለይ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመን ከተጀመረው የንግድ ጦርነት ጋር ተያይዞ ቢሆንም፣ ቻይና በታይዋን ላይ ባላት አቋም፣ ከሩሲያ ጋር ባላት ግንኙነት፣ የቻይና የስለላ ባሉን በአሜሪካ ግዛት መንሳፈፍና ተመትቶ መውደቅ ግንኙነቱን ካሻከሩት ይጠቀሳሉ፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለሁለት ቀናት ጉብኝት ወደ ቻይና ቤጂንግ ያቀኑትም፣ ይህንኑ ውጥረት ለማርገብ ያስችላል የተባለውን ውይይት ለማድረግ ነው፡፡

በሳምንቱ መጀመርያ ቤጂንግ የገቡት ብሊንከን፣ ከቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ጋር መምከራቸው በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ በር ከፋች እንደሚሆን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በተቀናቃኞቹ ኃያላን መንግሥታት ከፍተኛ መሪዎች መካከል የተጀመረው ውይይት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉ ዋና ዋና ልዩነቶችን በአሁን ወቅት መፍታት ባያስችልም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት የተሞላበት ግንኙነት ለማርገብ ያስችላል፡፡

ብሊንከን ከፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ውጥረት የተሞላበት ግንኙነት ለማርገብ አገሮቹ ቃል መግባታቸውን አስታውቀው፣ ይህም በቀጣይ ያሉ ልዩነቶችን እያጠበቡ ለመሄድ ያስችላል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዢ ውይይታቸው ለውጥ እንደሚያመጣ ሲገልጹ፣ ብሊንከን በበኩላቸው ወደፊት ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚኖሩ አስታውቀዋል፡፡

ብሊንከን ለ35 ደቂቃ የቆየውን ውይይት አስመልክተውም ‹‹በከፍተኛ ኃላፊዎች ደረጃ ውይይትን አስጠብቆ መቆየቱ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ ለማስተዳደርና ውድድሮች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ለማስቻል ተመራጭ መንገድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገው ውይይት በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ በታይዋን ቀውስ፣ አሜሪካ በቻይና ድጋፍ አስቀለብሳለሁ ብላ ተስፋ የጣለችበት የፌንተኔል ዕፅ ሕገወጥ ዝውውር፣ በሰሜን ኮሪያ እንዲሁም በቻይና አለ ስለሚባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ያጠነጠነ እንደነበር ኤምኤስኤን አስፍሯል፡፡

በአሜሪካና ቻይና መካከል ከፍተኛው የውዝግብ መነሻ ታይዋን ናት፡፡ ቻይና፣ ታይዋን ከቻይና የተገነጠለች አገር ናት ብላ ትናገራለች፡፡ ፕሬዚዳንት ዢ በሥልጣን ዘመናቸው ከሚመኙዋቸው ነገሮችም ታይዋንን በቻይና ሥር ማስገባት የሚለው ይገኝበታል፡፡

ታይዋን ራሷን በበኩሏ ከቻይና የተገነጠለች የራሷ ሕገ መንግሥትና መሪ ያላት አድርጋ ትቆጥራለች፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ታይዋን ከቻይና ጥቃት ከደረሰባት አሜሪካ ልትከላከልላት እንደምትችል ዓምና መናገራቸው በቤጂንግ ተወግዞ ነበር፡፡

ሆኖም ብሊንከን በቻይና በነበራቸው ቆይታ ዋሽንግተን ታይዋን ነፃ አገር መሆኗን ባትደግፍም፣ ቻይና የዜጎችን መብት ከምትጥስ ይልቅ በኢኮኖሚው እንዲታቀፉ እንደታደርግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

ብሊንከን የታይዋንን ራስ ገዝነት አገራቸው እንደማትደግፍ ሲገልጹ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትጠቀመውን ጦር መሣሪያ ቻይና እንዳታቀርብ ማረጋገጫ እንድትሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ቻይና በበኩሏ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ውይይት ዳግም እንዲጀመር በር መከፈት እንዳለበት ገልጻለች፡፡ የውይይቱ ዋና አጀንዳም በዩክሬንና ሩሲያ መካከል ውይይት እንዲደረግ ማስቻል የሚለው ላይ ያተኮረ እንደነበር ቢቢሲ አስፍሯል፡፡

የብሊንከን የቻይና ጉብኝት አሁን ትልቅ ለውጥ ባያመጣም፣ ወደፊት የተሻለ ውይይት ለማድረግ ምልክት የታየበት መሆኑን ብሊንከን ገልጸዋል፡፡

‹‹ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የአንድ ጉብኝት፣ የአንድ ጉዞና የአንድ ውይይት ውጤትም አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...