Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከችግር ያልተላቀቀው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

ከችግር ያልተላቀቀው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

ቀን:

በዓለም በየዓመቱ 2.78 ሚሊዮን ሠራተኞች በሥራ ላይ በሚፈጠሩ አደጋዎች ምክንያት ለሞትና ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ እንደሚሆኑ የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ሰዎች አደጋው ደርሶባቸው በበሽታ የሚያዙ ሲሆን፣ 374 ሚሊዮን ሠራተኞች ደግሞ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡

በተለያዩ የሥራ ገበታዎች የተሠማሩ ሠራተኞች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ባለመሆኑ የተነሳ በአካላቸው ላይ አደጋ ይደርስባቸዋል፡፡ ከሥራ ጋር የተያያዘ ውጥረትና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በዓለም ክፍሎች ላሉ በርካታ ሠራተኞች ችግሮች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያም በኮንስትራክሽን፣ በጤና ተቋማት እንዲሁም በሌሎች የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሠራተኞችም ደኅንነታቸው እየተጠበቀ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ በርካቶች ለአካል ጉዳተኛነት አሊያም ደግሞ ሕይወታቸው ሲቀጠፍ ይታያሉ፡፡

የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ባለፈው ሳምንት ‹‹ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ አካባቢ መሠረታዊ መርህና የሥራ ላይ መብት ነው›› በሚል መሪ ቃል በዘርፉ ያሉትን ችግሮች አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የውይይቱንም የመነሻ ሐሳብ በጽሑፍ ያቀረቡት የሙያ ደኅንነትና ጤንነት የሥልጠና ባለሙያ አቶ ማርቆስ አድማሱ እንደገለጹት፣ በኮንስትራክሽንና በጤና ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞች ደኅንነታቸው የተጠበቀ አይደለም፡፡  

በተለይ የሕክምና አገልግሎት በሚሰጡ ተቋሞች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ደኅንነት የተጠበቀ ባለመሆኑ ምክንያት የሕክምና ባለሙያውም ሆነ በሽተኛው ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ አቶ ማርቆስ ተናግረዋል፡፡

በጤና ተቋማት ውስጥ የሙያ ደኅንነት ጤንነት አመራር ሥርዓትን ዘርግቶ ተግባራዊ ያለማድረግና በዕቅድ ያለማካተት ችግር ስላለ፣ በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች ደኅንታቸው እየተጠበቀ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሕክምና ተቋማት ውስጥ ለሚቀጠሩ ሠራተኞች የሚቀርብላቸው ራስን ከበሽታና አደጋ የመከላከያ መሣሪያ ወይም ግብዓት ለሠራተኞች ተስማሚ መሆን እንዳለበት፣ ይህ ካልሆነ ግን በሠራተኞቹ ላይ የተክለ ሰውነት መዛባት ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡

ዕርድ በሚፈጸምባቸው ቦታዎች (ቄራ)፣ በባንኮች፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ በሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

በተለያዩ የሕክምና ተቋማት ውስጥ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ አለመጠናቀቅና የአየር ማቀዝቀዣ ባለመኖሩ የተነሳ በርካታ በሽተኞች ደኅንነታቸው እንዳይጠበቅና ለከፋ ችግር እንዲጋለጡ ሲያደርግ ይታያል ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትል ገልጸው፣ ይህንን በመረዳት መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች የሠራተኞቻቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ መሥራት እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል፡፡

የቢሮው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ምትኩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋሙ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ላቦራቶሪ በማደራጀትና በማጠናከር ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሙያ ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡

በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ ሠራተኞች ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀ አሠራርን እንዲከተሉ ቢሮው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሚሠራ፣ በየዓመቱ የተሠሩ ሥራዎችንም ተቋማቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ እንደሚያስገድድ  አስረድተዋል፡፡

ተቋማት የተሠሩ ሥራዎችን ሪፖርት ከማድረግ አኳያ ክፍተት እንዳለባቸውና በአብዛኛውም የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ ችግር የሚታየው በኮንስትራክሽንና በጤና ዘርፍ ውስጥ መሆኑን ገልጸው፣ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የተሻለ አሠራር እንዲኖር ከተቋማት ጋር ውይይት መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በደኅንነት ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ተቋሙ ምንም ዓይነት አገልግሎት እንደማይሰጥ፣ ነገር ግን ተበዳዮች በተፈለገው ልክ ካሳ እንዲያገኙ ከሕግ አካላት ጋር እንዲገናኙ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማትን ማፍጠንና ማስፋፋት ሲታሰብ፣ በቅድሚያ ለሥራ ላይ ደኅንነትና ጤንነት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል የሚሉት ኃላፊው፣ ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ቢሮ ወጥ የሆነ አሠራር ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...