…… ከንፈረ ፍሕሶ፣ አባሌሎም ፀጉር፣
ዐይነ ባትሪዬቱ፣ የጥርስሽ ማማር፣
ነፀብራቅ ፈገግታ፣ የአልማዝ መደብር፡፡
አካሄደ ቆንጆ ስዕላዊ ቅርጽ፣
እንዲያው አካላትሽ፣ …
ሳያውቁት፣ ሳያውቁሽ፣
የሚያስደነግጥ፣
የተቀኘ አዕምሮን ያለፋል ውበትሽ፣
አቤት ግሩም አንቺ፣ ምን ይሆን ፍጥረትሽ!
ብዬ የነበርኩኝ፣…
የውበትሽ አድናቆት በቁሜ ጠምቆኝ፣
እጆችሽን ይዤ ጎርፍ ቢወስደኝ፣
እንዲህ ነው አዱኛ፣
ይህ ነው መንገደኛ፣
ይቃናል ጉዞው!
…. ብዬ የፀለይኩኝ፣…
ዛሬ ለመመለስ መጣሬን አይተሽ፣
ምን አጠፋሁ ስትይ እቱ አይጭነቅሽ፣
በማዕበሉ መሀል ለዕጣሽ ስተውሽ፡፡
ያ ሌላኛው ውበት ተደብቆ ኖሮ፣
ባውቀው አሳፈረኝ፡፡
በቃ፣ ደህና ሁኝ፣
ከቶ አታስታውሽኝ፣
ምድረ በዳ አንጎልሽ፣ ግዑዝ ነው ደንቆሮ!
ሥጋ ብቻ ሰውን፣ አይችል ሊያቆይ አሥሮ!
አይችል ሊያቆይ አሥሮ
- ደበበ ሰይፉ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› (1992)