በመጪው ነሐሴ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ለሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሥር ሺሕ ሜትር በሁለቱ ፆታ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመለየት በስፔን ኔርጃ ከተማ የማጣሪያ ውድድር ይከናወናል፡፡
በውድድሩ የሚካፈሉ 26 አትሌቶች ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በወደ ሥፍራው ማቅናታቸው ታውቋል፡፡ አትሌቶቹ ሰኔ 16 ቀን የማጣሪያ ውድድሩን ካከናወኑ በኋላ በማግሥቱ ወደ አገር ቤት እንደሚመለሱ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥሩ ሰዓት ያላቸው በሁለቱም ፆታ የ14 አትሌቶች ስም ዝርዝር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ስማቸው ከተዘረዘሩ አትሌቶች በተጨማሪ ሌሎች የ10 ሺሕ ሜትር አትሌቶች ይካፈሉበታል ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም የመለያ ውድድሩን በኔዘርላንድ ሲያከናውን የነበረው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ የዘንድሮን ውድድር በሐዋሳ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር፡፡ ይም የሆነው ባለፉት ዓመታት የማሟያ ውድድሩን በኔዘርላንዳዊው ማናጀር ሔርመንስ አማካይነት በሄንግሎ ሲደረግ ቢቆይም፣ ዘንድሮ ማድረግ አለመቻሉን ፌዴሬሽኑ በመግለጹ የማሟያ ውድድሩን በስፔን ለማድረግ ከውሳኔ መድረሱ ይታወሳል፡፡
በቡዳፔስት የሚስተናገደው የዘንድሮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች በ10 ሺሕ ሜትር ርቀት ለመካፈል ወንዶች 27፡10፡00 ማምጣት የሚገባቸው ሲሆን፣ ሴቶች ከ30፡40፡00 በታች መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡
እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማብራሪያ ከሆነ ሰዓቱ ያላቸው በርካታ አትሌቶች ቢኖሩም፣ ወቅታዊ አቋም ከፍተኛ ግምት ስለሚሰጠው የማሟያ ውድድሩን ማድረግ አስፈልጓል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ በርቀቱ ስለሚጠበቁ የማሟያ ውድድሩ ከፍተኛ ግምት እንዲሰጠው አስችሏል፡፡
በማሟያ ውድድሩ በርካታ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተጠቅሷል፡፡ በውድድሩ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በቀጥታ የሚመረጡ ሲሆን አራተኛ የሚወጡት በተጠባቂነት ይያዛሉ፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ስም ዝርዝራቸውን ይፋ ካደረጋቸው አትሌቶች መካከል በወንዶቹ በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን ባረጋና ታደሰ ወርቁ ይገኙበታል፡፡ በሴቶች ሚዛን ዓለም፣ እጅጋየሁ ታዬና ቦሰና ሙላት ተጠቅሰዋል፡፡
ከሁለት ወራት በታች የቀረው የዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና የሚሳተፍ በርካታ አገሮች ተሳታፊ አትሌቶቻቸው ለይተው መደበኛ ዝግጅታቸውን ጀምረዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም የማራቶን አትሌቶች ጥሪ አድርጎ መደበኛ ልምምዳቸውን ጀምረዋል፡፡
ከነሐሴ 13 ቀን እስከ 21 በቡዳፔስት ከተማ የሚከናወነው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊካሄድ ሁለት ወራት ቀርተውታል፡፡ በሻምፒዮናው ከ200 በላይ አገሮች የተወጣጡ ከሁለት ሺሕ በላይ አትሌቶች ይጠበቃሉ፡፡ ቀሪ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ምርጫ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግና ብሔራዊ ቡድኑም ጥሪ ተደርጎለት በሆቴል ተቀምጦ መደበኛ ልምምዱን እንደሚጀምር ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
አዘጋጇ አገር ቡዳፔስት ዝግጅቷን አጠናቃ አትሌቶችን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡