Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መግለጫውን በተቃወሙ ፓርቲዎች ላይ የዲሲፕሊን ምርመራ ጀመረ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መግለጫውን በተቃወሙ ፓርቲዎች ላይ የዲሲፕሊን ምርመራ ጀመረ

ቀን:

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ የከፋ ቀውስ ውስጥ መሆኑን በመግለጽ የሰጠውን  መግለጫ ተቃውመው ሌላ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡ ፓርቲዎች ላይ፣ የቅጣት ዕርምጃ የሚያስከትል የዲሲፕሊን ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰጠውን መግለጫ በመቃወም ባለፈው ሳምንት በሸራተን አዲስ  መግለጫ የሰጡት ፓርቲዎች ቁጥራቸው 32 እንደሆነ ቢያሳውቁም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስማቸው ይፋ እንዲደረግ ከጋዜጠኞች ተደጋጋሚ  ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ዝርዝራቸውን ማቅረብ አልቻሉም ነበር።

የጋራ ምክር ቤቱን ተቃውመው መግለጫ የሰጡት ፓርቲዎች ካቀረቧቸው ምክንያቶች መካከል፣ መግለጫው የምክር ቤቱን አባላት እምነት የሚሸረሽርና ምክር ቤቱ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመወጣት በፓርቲዎች መካከል አለመተማመን ፈጥሯል የሚሉት ይገኝበታል።

ይሁን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መግለጫ የሰጡት ፓርቲዎች ሕገወጥ ድርጊት ከመፈጸማቸውም  በተጨማሪ ቁጥራቸውም 32 ሳይሆን ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹እነሱም አገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ ህዳሴ ፓርቲና  የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

መብራቱ (ዶ/ር) ሦስት ፓርቲዎች የገዥው ፓርቲ ድጋፍ እንዳላቸው ገልጸው፣ ለዚህም እንደ ማሳያ ያቀረቡት ምክር ቤቱ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ መግለጫ ሲሰጥ እንዲገኙ ጠርቷቸው አለመገኘታቸውን ነው፡፡ ሦስቱ ፓርቲዎች ግን  በሸራተን አዲስ በነበረው መግለጫ መገኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ  ላይ ምንም ዓይነት ቅሬታ ቢኖራቸው ወይም ስህተት ቢገኝ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ወይም ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ እንዲታይ ማድረግ እንጂ፣ በሚዲያ ወጥቶ ለሦስተኛ ወገን መግለጫ መስጠት የምክር ቤቱን አሠራርና ሕግ የጣሰ መሆኑን ሰብሳቢው አብራርተዋል።

የሦስቱን ፓርቲዎች ድርጊት የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች የፈረሙትን የውል ቃል ኪዳን የጣሰ ከመሆኑም በላይ፣ የሰጡት መግለጫ ሌላ ዓላማ ያዘለ ነው ብለውታል።

ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. የጋራ የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ  በምክር ቤቱ የሕግ ቋሚ ኮሚቴ  በፓርቲዎቹ ላይ የዲሲፕሊን ምርመራ ጀምሮ፣ በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርግ ትዕዛዝ መተላለፉን መብራቱ (ዶ/ር) አክለዋል።

በምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያዎች አማካይነት በሕግ ኮሚቴው የሚቀርበውን የውሳኔ ሐሳብ ተከትሎ በቀጣይ ፓርቲዎቹን ከምክር ቤት አባልነት በጊዜያዊነት ማገድ ወይም በቋሚነት ማሰናበት፣ ወይም የፈጸሙትን ጥፋት በሚዲያ እንዲገለጽ ማድረግ፣ የመጀመሪያ ወይም የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠትና መሰል ዕርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ መብራቱ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...