Tuesday, October 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ይሰጥ!

አገር የምትለማውና የምታድገው ሕዝብና መንግሥት እየተናበቡ ሲሠሩ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሲናበቡ የሚታቀዱ የልማት ፕሮጀክቶች ሰው ተኮር ስለሚሆኑ፣ ከአለመግባባት ይልቅ በጋራ ለውጤታማነታቸው አብሮ መልፋት የተለመደ ባህል ይሆናል፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ከታችኛው መዋቅሩ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚታወቁ ሲሆኑ፣ ሕግ አውጭው አካል ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ምንም አያዳግተውም፡፡ ሕግ ተርጓሚው የዳኝነት አካል ደግሞ እያንዳንዱ ሥራ ሕግና ሥርዓት ይዞ እየተመራ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እነዚህ ሦስቱ የመንግሥት አካላት በእርስ በርስ ቁጥጥርና ሚዛናዊ ግንኙነት በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሲወጡ፣ የሚታቀዱም ሆኑ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በሙሉ ሰው ተኮር ይሆናሉ፡፡ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅትም መፍትሔ ለመፈለግ አይከብዱም፡፡ ይህ በየትም አገር ሕዝብና መንግሥትን የሚያስማማ የተለመደ አሠራር ስለሆነ፣ በኢትዮጵያም ተግባራዊ እንዲሆን ቁርጠኝነት መኖር አለበት፡፡ የመንግሥት አሠራር በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ ሲመራ ለጭቅጭቅም ሆነ ለተቃውሞ የሚያነሳሱ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ሰው ተኮር የልማት ዕሳቤዎች ላይ ይተኮር፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከተሞች ውስጥ የሚስተዋለው ችግር በጣም መረር ያለ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በዋና ዋና መንገዶችና በየጥጋጥጉ በተለያዩ ምክንያቶች ኑሮ ያዘነበለባቸው በርካታ ሰዎች ምፅዋት ጠባቂ ሆነዋል፡፡ ሕፃናት ያዘሉና የተሸከሙ እናቶች፣ አዛውንቶች፣ አቅመ ደካሞችና ኑሮ የከበዳቸው በርካታ ሰዎች ምፅዋት ፍለጋ እጃቸውን እየዘረጉ ነው፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች በብዛት ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ሕፃናትና ታዳጊዎች ጎዳናዎችን እያጨናነቁ ነው፡፡ እነዚህ ሕፃናትና ታዳጊዎች ለሕይወታቸው አደገኛ የሆነውን ማስቲሽ  እየማጉ ተስፋቸው እየጨለመ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ጥቃቶች፣ ግጭቶችና ድርቅ ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖች ሜዳ ላይ ፈሰው የዕርዳታ ያለህ እያሉ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ሸገር ከተማ ቤቶቻቸው ፈርሰው የተፈናቀሉ ወገኖችም በየሥርቻው ወድቀዋል፡፡ የብዙኃኑ የከተማ ነዋሪዎችም ኑሮ ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለ ነው፡፡ እንደ ሰደድ እሳት ሊቆም ያልቻለው የኑሮ ውድነት የብዙኃኑን ሕይወት እንደ እሬት እያመረረው ነው፡፡ መንግሥት ይህንን አስቸጋሪ ፈተና ለመቋቋም የሚያስችሉ መፍትሔ አመንጪ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያድርግ፡፡

ልማቱም ሆነ ሌላው ጉዳይ ሰው ተኮር እንዲሆን ካልተደረገ በስተቀር እያጋጠመ ያለውን ፈተና ማለፍ አይቻልም፡፡ አዲሱ የበጀት ዓመት ሊጀመር ሁለት ሳምንታት የቀሩት ስለሆነ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቀው ረቂቅ የበጀት አዋጅ ሰው ተኮር እንዲሆን የሚመለከታቸው ሁሉ ያስቡበት፡፡ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 20 ሚሊዮን ያህሉ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የሚሰጡት ዕርዳታ ለሌላ ዓላማ እንዲውል ተደርጓል በማለት በቅርቡ ድጋፋቸውን ማቋረጣቸው ይታወሳል፡፡ እነሱ በጊዜያዊነትም ሆነ ለዘለቄታው ዕርዳታ ሲያቋርጡ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚፈልጉ ወገኖችን መታደግ ያለበት ከመንግሥት በስተቀር ማንም አይኖርም፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብም ማቆሚያ ባላገኘው የኑሮ ውድነት ምክንያት መሠረታዊ ፍጆታዎችን በአግባቡ ማግኘት ስላልቻለ በሰፊው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የምግብና የምግብ ነክ ቁሳቁሶች ዋጋ በጭራሽ ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ መንግሥት አዋጭ ስትራቴጂዎችንና ፖሊሲዎችን ቀይሶ ይህንን ከባድ ጊዜ ማለፍ አለበት፡፡

ከሰው ሕይወት በፊት የሚቀድም ምንም ነገር ስለሌለ ሕይወት አድን ሥራዎች ላይ በመረባረብ፣ እየከበደ ያለውን የኑሮ ሁኔታ ማርገብ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የአዲሱ ዓመት በጀት ሲፀድቅም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሙሉ ትኩረት ሕይወትን መታደግ ላይ ሊሆን የግድ ይላል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ታጥፈው በጀቱ ለሌላ ዓላማ ይውላል ሲባል፣ ከምንም ነገር በላይ መቅደም ያለባቸው ግን  ሕይወት አድን ሥራዎች ሊሆኑ እንደሚገባ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉና ሜዳ ላይ የወደቁ ወገኖችም ሆኑ፣ ከአቅማቸው በላይ በሆነ የዋጋ ንረት የሚሰቃዩ በሙሉ ሰው ተኮር በሆኑ አሠራሮች የሕይወታቸው ተስፋ መለምለም ይኖርበታል፡፡ ዜጎች በኑሮ እየተጎዱና ተስፋ እየቆረጡ አገር ማደግ አትችልም፡፡ እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ለአገር ልማትና ዕድገት መሠረት የሚጥሉ ፕሮጀክቶች ግንባታ አስፈላጊነት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የፕሮጀክቶቹ አስፈላጊነት የሚወሰነው ከሚኖራቸው ፋይዳና የወደፊት ጥቅም አኳያ ሲሆን፣ ከግለሰባዊ ፍላጎት በላይ ብሔራዊ መግባባት መኖር የግድ መሆን አለበት፡፡

እንደሚታወቀው በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሰበብ በደረሱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራዎች አገር ከባድ ፈተና ገጥሟታል፡፡ በቅርቡ በግጭቱ ለተጎዱ ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም ይፋ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ፕሮግራሙ ይፋ ሲደረግ በግጭቶቹ ሳቢያም 28.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመትና ኢኮኖሚያዊ ድቀት መድረሱን፣ ለመልሶ ግንባታ ደግሞ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተነግሯል፡፡ ይህንን ግዙፍ ውድመት መልሶ ለመገንባት በመንግሥት አቅም ብቻ የማይሞከር በመሆኑም፣ ባለድርሻ አካላትና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፋቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ በአምስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ለሚጠበቀው ለዚህ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላትና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትብብር ሲጠየቅ፣ መንግሥትም በራሱ በኩል የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ድርጊቶችን በማቆም ሰው ተኮር ሥራዎች ላይ ማተኮር ይጠበቅበታል፡፡ አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዳሉት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት እያሉ፣ የቅንጦት ፕሮጀክቶችን ሙጥኝ ማለት ከሰብዓዊነት አኳያ ተገቢ አይደለም፡፡ የሕግ አውጭውም ሆነ የአስፈጻሚው አካል ኃላፊነት ሕዝብን መታደግ ይሁን፡፡

መንግሥት ሕዝቡን ለልማት በማነሳሳት ከጎኑ ማሠለፍ የሚችለው፣ ፕሮጀክቶቹ ሰው ተኮር መሆናቸው እምነት ሲጣልባቸው ነው፡፡ ለታይታም ሆነ የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚጠቅሙ የሚመስሉ ስሜቶችን የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች፣ ከቃል በላይ ተግባራዊ በሆነ ሁሉን አቀፍ ዕሳቤዎች ፈር ሊይዙ ይገባል፡፡ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አማካይነት በየዓመቱ ችግኞች ሲተከሉ ለአገር ጠቃሚ የሆኑትን ያህል፣ የሌሎች ፕሮጀክቶች ጠቀሜታም እንዲሁ ሕዝብን አሳማኝ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ ከመጠን በላይ እየተስፋፋ የመጣው ሙስናም በአጭሩ መቀጨት አለበት፡፡ በየቦታው ቁጥራቸው በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው ሕገወጦች መሬት በስፋት እየወረሩ፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት እየዘረፉና አገሪቱን የሥርዓተ አልበኝነት መናኸሪያ እያደረጉ ጠያቂ ሲጠፋ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን አይኖርም፡፡ ሌላው ደግሞ የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ምርቶችና አቅርቦቶች በበቂ ሁኔታ ገበያ ካልደረሱ የኑሮ ውድነቱን ለመግታት አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ይሰጥ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...