Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት በፓርቲ መስመር እንዳይደፈጠጥ ትኩረት እንዲደረግ ተጠየቀ

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት በፓርቲ መስመር እንዳይደፈጠጥ ትኩረት እንዲደረግ ተጠየቀ

ቀን:

የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች እንዲሁም በክልሎች መካከል የሚደረገው የመንግሥታት ግንኙነት፣ በፓርቲ መስመር እንዳይደፈጠጥ ትኩረት እንዲደረግ ጥያቄ ቀረበ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ከክልሎች ጋር  ለሚያደርገው  የምክክር መድረክ የሚያግዘው የግብዓት ማሰባሰቢያ  ስብሰባ፣ ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም.  በአዲስ አበባ አካሂዷል።

‹‹የመንግሥታት ግንኙነት ለጠንካራ ፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ያለው ሚና›› በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሰሎሞን ንጉሤ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፣ በመንግሥታት መካከል የሚደረጉ ግንኙነቶችና መድረኮች የሚመሩበትን ሥርዓት ማበጀት ይገባል ብለዋል።

የፓርቲ መድረክ ምንም እንኳ አንዱ የግንኙነት መፍጠሪያ መንገድ ቢሆንም፣ ፓርቲዎች የተቋማትን ሚና ሸፍነው የመንግሥታት ግንኙነትን በመርህ፣ በተጠያቂነትና በውጤታማነት መለካታቸውና መመዘናቸው ቀርቶ የፓርቲ ፎረም ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ በዚህም የተነሳ የፓርቲ ፎረም ለሕዝብ የሚኖረው ግልጽነት አጠያያቂ እንደሚሆን አስረድተዋል።

በአንድ አገር ውስጥ  አንድ አውራ ፓርቲ የሚኖር ከሆነና  በመንግሥታት መካከል የሚደረገው ግንኙነት በፓርቲ የሚመራ ከሆነ፣ የታሰበው ውጤት መልኩን እንደሚያጣ ተናግረዋል። 

በፓርቲ አሠራር በመንግሥታትና በክልሎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ለመምራት መሞከር ደግሞ፣ በቀጣይ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመንግሥት መዋቅርና ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ሲኬድ የተቋማትን ሚና እንደሚያደበላልቅና ተዓማኒነት እንደሚያሳጣ አስረድተዋል።

‹‹መንግሥታት ግንኙነት በኢትዮጵያና ቀጣይ አቅጣጫ›› በሚል ርዕስ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የፌደሬሽን ምክር ቤት  ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ምክትል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ወዲሻ፣ በፓርቲ በኩል ችግርን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በራሱ ችግር ባይኖረውም ይህ ዓይነቱ አሠራር መርህንና ሕግን የተከተለ ተቋማዊ ግንባታና አሠራር ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ወደፊት የፌዴራል ሥርዓቱን የሚረብሹ ጉዳዮች ይሰፋሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት መድረኮች አስፈላጊ በሆኑት ልክ የትኩረት ማነስ ችግር አለ የሚሉት አቶ በላይ፣ የመንግሥታት ግንኙነት አስፈላጊነት ችግር ከተፈጠረ በኋላ የመሰብሰቢያ ሳይሆን ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ሳይንሳዊና ጥናታዊ የሆኑ መፍትሔዎች የሚዘጋጁበት መድረክ መሆን አለበት ብለዋል።

ለኅብረ ብሔራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የመንግሥታት ግንኙነት መድረኮች አስፈላጊ  ቢሆኑም ሒደቱ በሥርዓቱ ካልተመራ ግን የፖለቲካ ዋልታ ረገጥነት እንደሚበራከት፣ በጥባጭ ኃይሎች እንደሚፈጠሩና የመንግሥትን የመፍረስ አደጋ ያስከትላል ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህ የአንድ ቀን መድረክ የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

   
 
     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...