Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ካፒታሉን ወደ 7.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያቀረበው ጥያቄ ይሁንታ ሊያገኝ ነው አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለግብርና ምርታማነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የእርሻና የአግሮ ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የተፈቀደ ካፒታሉን ወደ 7.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያቀረበው ጥያቄ ይሁንታ ሊያገኝ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የግብርና ግብዓት የሚፈልገው የሥራ ማስኬጃ ጥሬ ገንዘብ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ ካፒታሉ እንዲያድግ ከዚህ ቀደም ለመንግሥት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

ኮርፖሬሽኑ በ2008 ዓ.ም. ሲቋቋም በተፈቀደ 2.44 ቢሊዮን ብርና በተከፈለ 610 ሚሊዮን ብር እንደነበር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውሰው፣ በ2013 የበጀት ዓመት የተከፈለ ካፒታሉን 2.44 ቢሊዮን ብር እንዳሟላ ገልጸዋል፡፡

ካፒታል የማሳደግ ጥያቄውን ተጠሪ የሆነለት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ቦርድ እንደተመለከተው ያስታወቁት አቶ ክፍሌ፣ ከመፅደቁ በፊት ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲያየው የተፈለገ አንድ ጉዳይ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲመለከተው የተፈለገው ጉዳይ የበጀት አንድምታ (Fiscal Implication) የሚኖረው ከሆነ ታይቶ ይቅረብ ስለተባለ ምልክታ እየተደረገበት እንደሆነ ጠቁመው፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ማረጋገጫ ሲሰጥ ካፒታሉ እንደሚፀድቅ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

ካፒታል የማሳደግ ሒደቱ እየተጠናቀቀ ይገኛል ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል፣ ሒደቱም ሲጠናቀቅ የኮርፖሬሽኑ የተፈቀደ ካፒታል 7.5 ቢሊዮን ብር፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 2.44 ቢሊዮን ብር ሆኖ በመደበኛ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ካፒታል በማስያዝና በመበደር እየከፈለ አገልግሎቱን እንዲያስፋፋ የሚያስችለው እንደሚሆን ተብራርቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ካፒታል ለማሳደግ የሚያስችል ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት (IFRS) ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን፣ ወቅታዊ የሆነ የሒሳብ ሪፖርት ስላለው መንግሥት በቀላሉ ይህንን በመመልከት ገምግሞ በመፍቀድ ሒደት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ካፒታል የማሳደግ ጥያቄውን ወደ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከመጠቃለሉ በፊት ተጠሪ ለነበረበት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር አቅርቦ፣ አስተዳደሩ የድርጅቱን የስትራቴጂክና የቢዝነስ ዕቅድ ሲገመግም እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ ተጠሪነቱ ወደ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በመዘዋወሩ ምክንያት ጥያቄው ዳግም መቅረቡ ታውቋል፡፡

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተቀናጀ የሜካናይዜሽን አገልግሎትን ጨምሮ ምርጥ ዘር፣ ጠጣርና ፈሳሽ የአፈር ማዳበሪያ፣ የፀረ ተባይ ኬሚካሎችና የእንስሳት መድኃኒቶችን የሚያቀርብ መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡ የእርሻ፣ የኮንስትራክሽንና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎችን በማቅረብም ይታወቃል፡፡

26 የልማት ድርጅቶች አባል የሆኑበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አባል የሆነው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዘንድሮ አጠቃላይ ሽያጩን ወደ 10.8 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህም ከዚህ ቀደም የዓመቱ አጠቃላይ ሽያጭ ከነበረው አኃዝ ከፍተኛ ብልጫ ያለው መሆኑን አቶ ክፍሌ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ዓመታዊ ትርፉንም ከዚህ ቀደም ከነበረው 400 ሚሊዮን ብር በዘንድሮ የበጀት ዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ለማድረስ መታቀዱን፣ እስካሁን ያለው አፈጻጸሙ ሲገመገም አጥጋቢ ሊባል የሚችል እንደሆነና ዓመታዊ ጠቅላላ ትርፉ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አቶ ክፍሌ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች