Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ መልሶ ግንባታ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዳንኤል ንጉሤ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ መልሶ ግንባታ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለሪፖርተር አስታወቁ።

ወቅቱ ክረምት በመሆኑ በመጪው ዓመት መስከረምና ጥቅምት አካባቢ፣ የመልሶ ግንባታ ሥራውን ለማስጀመር መታቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ከባድ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ይታወሳል። መልሶ ግንባታው በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጀመር የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የኮንትራክተር መረጣ ሒደት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያው መልሶ ግንባታ ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ የኮንትራክተር መረጣ ሒደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ይታወቃል ብለዋል፡፡  

የኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስክንድር ዓለሙ፣ የመልሶ ግንባታው ፕሮጀክት የተለያዩ የኤርፖርት መገልገያዎችን ማደስ ያካትታል ብለዋል። አክለውም በጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን የአውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ተርሚናል ሕንፃዎችን መልሶ መገንባት ላይ ዋናው ትኩረት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ እንደገና የሚታደሰው አውሮፕላን ማረፊያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ጥረት እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነቱ ሲፈረም መቀሌ፣ ሽሬ፣ እንዲሁም አክሱም በረራ እንዲጀመር ታስቦ እንደነበር የተናገሩት አቶ መስፍን፣ የሽሬው በመለስተኛ እንዲሁም የአክሱም ሙሉ በሙሉ ውድመት ምክንያት ሥራ እንዳልጀመሩ ገልጸው፣ ሆኖም የሽሬ አውሮፕላን መንደርደሪያና ጥቃቅን ጉዳቶች ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

አክለውም የመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ ምንም ዓይነት ጉዳት ስላልደረሰበት ወደ ሥራ ወዲያውኑ መግባቱንም አስታውሰው፣ የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ግን በከፍተኛ ደረጃ የአውሮፕላን መንደርደሪያው ስለተጎዳ ለጥገና ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ መልሶ ግንባታ በአካባቢው ማኅበረሰብና በክልሉ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። የአውሮፕላን ማረፊያውን መልሶ ለመገንባት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት፣ ቱሪስቶችን ለመሳብና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያስችል ተገልጿል። በተጨማሪም በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችንና ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችለውን የአቅርቦት ሰንሰለት ወደ ነበረበት ለመመለስ ዕገዛ ያደርጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን መልሶ ለመገንባት ቁርጠኝነት በማሳየቱ፣ ለአካባቢው መነቃቃት የሚፈጥር በመሆኑ ደስታ እንደፈጠረላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች