የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለምታደርገው ሁሉን አቀፍ ዝግጅት፣ የ450,000 ፓውንድ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
የእንግሊዝ መንግሥት ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ የቴክኒክ ሥራዎችን ለማከናወን የሚረዳ መሆኑን፣ ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. የእንግሊዝ ኤምባሲ ውስጥ በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል፡፡
ለኢትዮጵያ የሰነድ ዝግጅት፣ ምን ዓይነት ምርት መላክ እንደሚገባ፣ ሥራውን ለሚያከናውኑት ሠራተኞች ሥልጠና መስጠት፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ማፋጠን፣ በፍጥነት አባል እንድትሆን የሰው ኃይል መመደብ፣ እንዲሁም የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ማድረግ በኢትዮጵያ ከሚከናወኑ የቴክኒክ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮጵያና እንግሊዝ በንግድና በኢንቨስትመት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ የመግባቢያ ሰነዱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላና የእንግሊዝ የንግድ ሚኒስትር ኒገል ሃድልስተን፣ የሁለቱ አገሮች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተፈርሟል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ እንድታሳድግ በእንግሊዝ በኩል ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን፣ የእንግሊዝ የንግድ ሚኒስትር ኒገል ሃድልስተን ተናግረዋል፡፡
አቶ ገብረ መስቀል በበኩላቸው፣ ስምምነቱ ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግና የንግድ ሚዛኑን ለማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው በዕለቱ ተገልጿል፡፡
በተያያዘ የታዳጊ አገሮች አምራቾች ምርቶቻቸውን ከታሪፍ ነፃ በሆነ መንገድ ለእንግሊዝ ማቅረብ የሚያስችላቸውን መርሐ ግብር፣ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተካሂዷል።
ይህ የታዳጊ አገሮች ነፃ የንግድ ፕሮግራም በ65 የዓለም አገሮችና በ37 የአፍሪካ አገሮች የሚጀመር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም በሌሎች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ምርት የተሰማሩ አምራቾች በእንግሊዝ ገበያ ውስጥ ምርቶቻቸውን በነፃ የሚያቀርቡበት መሆኑን በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የእንግሊዝ የንግድ ሚኒስትር ኒገል ሃድልስተን፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ንግዶች ለመሳተፍና ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በ2030 የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ በማሳደግ፣ ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አምስት ሚሊዮን የሥራ ዕድልና ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ለማሳካት አቅዶ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሲተገብር መቆየቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ ተናግረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፓሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ወ/ሮ ሌሊሴ ነሜና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡